ኮሮናቫይረስ፡ በከፋ ዞን በሞቱ ግለሰቦች ላይ ኮቪድ-19 መገኘቱ ስጋት ፈጥሯል

ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ

የፎቶው ባለመብት, Bonga University/FB

በከፋ ዞን ሁለት ሰዎች ህይወታቸው ካለፈ በኋላ አስክሬናቸው ላይ በተደረገ ምርመራ ሟቾቹ በኮቪድ-19 ተይዘው እንደነበረ ተረጋግጧል።

ባሳለፍነው እሁድ በከፋ ዞን በሰው እጅ የተገደሉት ግለሰብ እስክሬናቸው ላይ በተደረገው ምርመራ ግለሰቡ በኮቪድ-19 ተይዘው እንደነበረ መረጋገጡን የቦንጋ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ዘሪሁን መንገሻ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ግለሰቡ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠው ድብደባውን ተከትሎ የአስክሬን ምርመራ ሲደረግ በዚያው ኮቪድ-19 ሲመረመር እንደሆነ ሥራ አስኪያጁ ነግረውናል፡፡

አስክሬኑ አሁንም ሆስፒታል እንደሆነ የገለጹት አቶ ዘሪሁን፤ ከግለሰቡ ጋር ንክኪ ያላቸው ቤተሰቦች፣ አስከሬን ያነሱ ሰዎች፣ አስከሬን የወሰዱ የፖሊስ አባላት፣ የወንጀል መርማሪዎች፣ አሽከርካሪዎች እና የአስከሬን መርማሪዎች ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ወደ ተዘጋጀው የለይቶ ማቆያ መግባታቸውን ገልጸውልናል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ከግለሰቡ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎች በጠቅላላ በአዴ ወረዳና በዴቻ ወረዳ ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አቶ ዘሪሁን እኚህ በድብደባ የተገደሉት ግለሰብ አርሶ አደር መሆናቸውን እና በሽታው ከየት ሊይዛቸው እንደቻለ አለማወቃቸውን ይናገራሉ፡፡

"ግለሰቡ ከሚኖርበት ቀበሌ እንኳን ወጥቶ አያውቅም ነው የሚባለው፤ ከየት እንደያዘው ለመደምደም አስቸጋሪ ነው" ብለዋል አቶ ዘሪሁን፡፡

ከዚህ ቀደምም ከዴቻ ወረዳ ባሃ መንደር አንድ የ55 ዓመት የጎዳና ተዳዳሪ ሕይወታቸው አልፎ ከተገኙ በኋላ የአስከሬን ምርመራ ተደርጎላቸው ኮሮናቫይረስ እንደተገኘባቸው አቶ ዘሪሁን አስታውሰዋል፡፡

ሥራ አስኪያጁ "የበሽታው ሥርጭት በማህበረሰብ ውስጥ እንዳለና ምልክት የሚያሳዩ ሰዎች እንደሌሉ፤ ነገር ግን የሚያስተላለፉ እንዳሉ ያመላክታል" ይላሉ፡፡

የወረርሽኙን ሥርጭት ለመግታት የተለያዩ የመከላከያ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ዘሪሁን፤ በአካባቢው የቫይረሱ ምንጭ ካልታወቀ ሥራቸውን አዳጋች እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጅ አሁንም የወረርሽኙን ሥርጭት ለመግታት ሥራዎች እየተሰሩ ነው ይላሉ፡፡

ከአቶ ዘሪሁን እንዳረጋገጥነው እስካሁን ድረስ በከፋ ዞን በቫይረሱ መያዛቸው በምርመራ የተረጋገጡት ሁለት ግለሰቦች ናቸው፡፡ እነዚህም ህይወታቸው ካለፈ በኋላ በተደረገ የአስክሬን ምርመራ ነው።

ይሁን እንጅ በዞኑ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ቢጨምር፤ በርካታ ታማሚዎችን ተቀብሎ ሊያስተናግድ የሚችል ማዕከል አለ ወይ ስንል የጠየቅናቸው አቶ ዘሪሁን ፤ በተለይ ንክኪ ያላቸውን ሰዎች ማቆያ በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ መዘጋጀቱንና ምልክት የሚያሳዩ ሰዎችንም ለማቆየት እዚያው ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የተዘጋጀ አንድ ህንጻ መኖሩን ገልጸውልናል፡፡

በሽታው የተገኘባቸው ሰዎችንም ለይቶ ለማከም በቦንጋ የህክምና ማዕከል እየተዘጋጀ ቢሆንም የምርመራ ውጤት መዘግየት ግን ተግዳሮት እንደሆነባቸው ያስረዳሉ፡፡

ከዚህም ባሻገር ለጤና ባለሙያዎች የቫይረሱ መከላከያ የህክምና ግብዓቶች እጥረት እንዳለባቸው ሥራ አስኪያጁ ለቢቢሲ ተናግረዋል፡፡

ኮሮና