ክትባት፡ ተመራማሪዎች ያልደረሱበት አነጋጋሪው የክትባት ምስጢር

የምትከተብ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ክትባት ባይኖር ኖሮ ምን ይውጠን ነበር? ምናልባት የዓለም ሕዝብ 4 ቢሊዮን ብቻ ይሆን ነበር። ወይም ከዚያ በታች።

ማን ስለ ክትባት ይጨነቅ ነበር? እድሜ ለኮሮናቫይረስ።

በእርግጥ ኮቪድ-19 ብዙ ስለ ክትባት እንድናስብ አድርጎናል።

ይህ ትውልድ በጉጉት የሚጠብቀው ክትባት የኮሮናቫይረስን ነው። ቻይና ክትባቱን አግኝቼዋለሁ ማለት ጀምራለች። አንዳንዶች 'አንቺው ታመጪው አንቺው ታሮጪው' ሲሉም ቀልደዋል።

ሩሲያም ክትባቱ በእጄ ነው ካለች ሰንብታለች። አንዳንድ የምዕራቡ አገራት 'ሩሲያን ማን ያምናል' ብለዋታል።

ክትባት የዓለምን ሕዝብ ለሁለት ከፍሎታል።

ፀረ-ክትባት የሆኑ ቡድኖች ከወዲሁ ክትባት ይቅርባችሁ እያሉ ነው። ለምን ሲባሉ፣ ቢልጌትስን ከማበልጸግ ያለፈ ትርፍ የለውም ይላሉ።

ለመሆኑ ክትባት በጥቅሉ መጥፎ ነገር ነው?

ይህ ዘገባ ስለክትባት በረከቶች ያሉ እውነታዎችን በሳይንስ አስደግፎ ያቀርብልናል። እንደ ጠብታ ክትባት ይቺንም ጽሑፍ ዋጥ ማድረግ ነው እንግዲህ።

በጊኒ ቢሳው አስደናቂ ነገር ተከሰተ።

ከጊኒው ቢሳው ሆኖ ለቢቢሲ በስካይፕ ቃለ ምልልስ የሰጠው ዴንማርካዊ ተመራማሪ ፒተር ኤቢ፤ ከ40 ዓመታት ውስጥ ብዙ ዘመኑን ያሳለፈው በጊኒ ቢሳው ነው። ለመጀመርያ ጊዜ ጊኒ ቢሳው የሄደው በ1978 ዓ.ም ነበር። ድሮ!

በአፍሪካዊቷ ድሀ አገር ውስጥ ለዚህን ያህል ዘመን ይሄ ዴንማርካዊ ምን ይሠራል?

እየተመራመረ ነበር። ክትባት በዚያች አገር አንድ አስደናቂ ውጤት ካመላከተው በኋላ እዚያው በምርምር ሰምጦ ቀረ።

ፒተር ጊኒ ቢሳው በሄደ ጊዜ ገዳይ የኩፍኝ ወረርሽኝ ነበረ። ብዙ ልጆችን ቀጥፏል። ህጻናቱ በበሽታው እንደ ቅጠል ረገፉ። ከዚያ እነ ፒተር የክትባት ዘመቻ ጀመሩ።

ልክ ይህን ዘመቻ ባደረጉ በዓመቱ አስደናቂ ነገር ታየ። ክትባት ከወሰዱት 50 ከመቶዎቹ የመሞት ዕድላቸው ክትባት ካልወሰዱት ይልቅ በግማሽ አንሶ ተገኘ።

ይህን ስታነቡ "ልጆቹ ክትባት ወስደው ሊሞቱ ነበር እንዴ፣ታዲያ?" ትሉ ይሆናል። ነገሩ ወዲህ ነው።

እናንተ ልጆቹ በኩፍኝ ሳይሞቱ የቀሩ ነው የመሰላችሁ። አይደለም። አስደናቂው ነገር ይህ ነው። ክትባት የወሰዱ ልጆች በሌላ በሽታም የመሞት እድላቸው በግማሽ ቀንሶ ነው የተገኘው።

ከክትባቱ በኋላ እንዴት በጊኒ ልጆች ዘንድ ሞት በዚያ ደረጃ ሊቀንስ ቻለ ብለው መመራመር ጀመሩ፤ እነ ፒተር።

ለካንስ የኩፍኝ ክትባቱ ሳይታሰብ ልጆቹን በሌሎች የማይታወቁ በሽታዎችም እንዳይሞቱ አድርጓል። ክትባቱ ለዚያ ዓላማ ባይሰራም ሰውነታቸው ውስጥ ሲገባ ግን የሆነ ያሻሻለው ነገር ነበረ።

ሳይንቲስቶቹን ያስደነቀውም ይኸው ነው።

የክትባት መርፌና ብልቃጥ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሰውነታችን እንዴት ነው የሚሰራው?

ለዘመናት ክትባቶች ለአንድ በሽታ መከላከያ ብቻ ነበር ሲሰጡ የነበሩት። ነገር ግን ሰውነታችን ክትባቶችን እንደዚያ አይደለም የሚረዳቸው።

ባልታሰበ ሁኔታ አንድ ክትባት በርካታ በሽታዎችን ሊከላከል ይችላል። ካልታሰበ በሽታ ይከላከላል። ይህ የተደረሰበት ግን ዘግይቶ ነው።

በጊኒ ቢሳው የተደረገ ሌላ ምርምር ለፈንጣጣ በሽታ ክትባት የወሰዱ ልጆች 80 ከመቶ በሕይወት የመኖር ዕድል ጨምሮላቸዋል።

የምናወራው በፈንጣጣ ምክንያት ሳይሞቱ የቀሩትን አይደለም። ያ ሲጀመርም የክትባቱ ዓላማ በመሆኑ አይደንቅም። በሌላ በሽታም የመሞት እድላቸው መቀነሱ ነው አስደናቀው።

በዴንማርክ ሳይንቲስቶች የሳንባ ነቀርሳ ክትባት የወሰዱ ልጆች በሌላ ተፈጥሯዊ በሽታ የመሞት እድላቸው በ42 ከመቶ ያህል ቀንሶ አግኝተውታል፡፡

ይህም ልጆቹ ክትባቱን ወስደው እስከ 45 ዓመታቸው ክትትል ተደርጎላቸው የተገኘ አስደናቂ ውጤት ነው።

በደቡብ አፍሪካ ደግሞ ውሾች ላይ የተሰራ ጥናት ተመሳሳይ ውጤትን አሳይቷል። ከእብድ ውሻ በሽታ (ሬቢስ) ክትባት የተወጉት ውሾች በሌላ የውሻ በሽታ ጭምር የመሞት ዕድላቸው ቀንሶ ተገኝቷል።

ከዚህ በላይ የተዘረዘሩት አንቀጾች አንድ ነው ነጥባቸው።

ክትባት ከታሰበለት ዓላማ ውጭም ይሰራል። ያልታሰቡ፣ የማይታወቁ፣ ያልተደረሰባቸውን በሽታዎችንም ይከላከልልናል።

እንዴት? ለሚለው ግን ሳይንቲስቶቹም መልስ የላቸውም። መገመት ብቻ ነው የቻሉት።

የአንድ በሽታ ክትባት እንዴት ሌላ በሽታን ሊከላከል ቻለ?

አንድ ሰው አንድ ክትባት ወስዶ ካልታሰበ አለርጂ (ብግነት)፣ ካልታሰበ ካንሰር፣ ካልተጠበቀ አልዛሚር ሊፈወስ ይችላል ማለት ነው። ለዚህም ነው የሳምባ በሽታው [ቲቢ] ክትባት ምናልባት ኮቪድንም ሊከላከል ይችል ይሆን እየተባለ ሙከራው የቀጠለው።

ነገር ግን በቲቢና በኮቪድ-19 ደቃቃ አካላት (ማይክሮኦርጋዝምስ) መካከል ምንም የሚያመሳስላቸው ነገር የለም። ኧረ እንዲያውም አይገናኙም። አንዱ በባክቴሪያ ሌላው በቫይረስ ነው የሚመጣው።

ሆኖም ግን ክትባቱ የሆነ ተአምር ሰውነታችን ላይ እንዲፈጠር ሲያደርግ ታይቷል። ጭላንጭል ነው ለጊዜው የታየው። ለዚያም ነው ሳይንቲስቶች ተስፋ ያልቆረጡት።

ይሁን እንጂ ሁለቱን በሽታዎች የሚያስከትሉት ደቂቀ አካላት ባክቴሪያና ቫይረስ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፤ በዝግመተ ለውጥ ራሱ በአፈጣጠራቸው 3 ቢሊዮን ተኩል ዓመታት ይለያያሉ። አንዱ የሌላው ታላቅ ነው። አንዱ ለሌላው ታናሽ ነው።

አሁን ትልቁ ጥያቄ የሆነው እንዴት ለአንድ በሽታ የታሰበ ክትባት ሌሎች ያልታሰቡ ውጤቶችን አውንታዊ ውጤትን ያስከትላል የሚለው ነው።

ሳምባ በሽታን [ቲቢ] እንውሰድ፤ ይህ በሽታ ለዘመናት የሰው ልጅ ጠላት ሆኖ የቆየ ነው።

በአንድ ዘመን ይሄ የፈረንሳይ የባክቴሪያ ሳይንስ ተመራማሪ አልበርት ካልሜት እና ካሚል ጉሪን ክትባት አገኙለትና የሰው ልጅን ከፍጅት ታደጉት። እንጂ ይሄን ጊዜ 1 ቢሊዮን ሕዝብ እንኳን በምድር ላይ አይቀርም ነበር።

ይሄ ጠምዛዛ ባክቴሪያ ከሰው ልጅ ጋር ለ40ሺህ ዓመታት አብሮ ነበረ። ሰው በሳምባ በሽታ ሲለከፍ የሞት ፍርድ ማለት ነበር።

የጥንት የግብጽ ሕዝቦች ባደረቋቸው ሬሳዎች ውስጥ በአንድ ሦስተኛው አስከሬኖች ላይ ይህ የሳምባ በሽታ ባክቴሪያ ተገኝቶበታል። በዚያ ዘመን ሕዝቡን የፈጀው ይኸው በሽታ ነው። ከምድረ ገጽ ሊያጠፋን የደረሰ ባክቴሪያ ነበር።

ምን ያኔ ብቻ! በ20ኛው ክፍለ ዘመን ራሱ የሳምባ በሽታ ባክቴሪያ ያልፈጀው የሰው ዘር አለ እንዴ?

የፖለቲካ አዋቂውን ኤሊኖር ሩዝቬልትን ማን ገደለው? ገራሚውን ደራሲ ጆርጅ ኦርዌልን ማን ነጠቀን? ወጣ ያለ የምንግዴ ሕይወት የኖረውን ፍራንዝ ካፍካን ማን ወሰደው? የሳምባ በሽታ አይደለምን?

እነዚህ ሁለት ፈረንሳያውያን ነፍሳቸውን በአጸደ ገነት ያኑርልንና ቢሲጂ (BCG) የተባለውን ክትባትን ፈጠሩ። ይኸው ምድር ላይ ቢሊዮኖች ከቲቢ እልቂት ተረፉ።

እነ አልበርት ካልሜትና ካሚሎ ጓሪን ክትባቱን እንዴት አገኙ? እንዴት ክትባቱን ደረሱበት? ቲቢ ያን ጊዜ ልክ የኤችአይቪ ወይም የኮሮናቫይረስ ክትባት ከማግኘትም በላይ ነበር። አሁን ክትባቱ እጃችን ላይ ስላለ ነው የማይደንቀን።

ክትባቱን ያገኙት ከላም ነው። ድሮም ላም የዋህ ናት። ላም ውስጥ ያገኙትን ክትባት ቀስ በቀስ እየቀየሩ ነው ፈውስ ያገኙት። በ1921 ዓ. ም ላይ በአንድ ልጅ ተሞከረና በ1950ዎቹ ታሪክ ተለወጠ።

ክትባቱ ከ70-80 በመቶ ፈውስ የሚሰጥ ነበር። ችግር ተቀረፈ። ብዙዎች ዳኑ። ለቲቢ መከላከያ ተበጀለት።

እስካሁን ያወራነው የክትባት ታሪክ ነው። ምኑም አስደናቂ ላይሆን ይችላል።

አሁን አስደናቂው ሳይንቲስቶች ለሳምባ ነቀርሳ ሲሰጥ የነበረው ቢሲጂ የተባለው ክትባት ስንትና ስንት በሽታን ሲከላከል እንደነበረ ስለደረሱበት ነው። ደግና ቀና ክትባት ነበር።

ልጆች እንደተወለዱ በጥቂት ወራት ውስጥ በበሸታው ይቀጠፉ ነበር። ከክትባቱ በኋላ ግን ይህ ቀረ። ለካንስ ይህ ክትባት በሳምባ እንዳይሞቱ ብቻ አልነበረም የሚያደርገው።

ከዚህ ክትባት በኋላ በሌላ በሽታም የሚሞቱት ህጻናት ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ቀነሰ። በቁጥር ማስቀመጥ ካስፈለገ የልጆች ሞት በ70 ከመቶ ቀነሰ። በዚህ ክትባት ምክንያት ብቻ።

የጠብታ ክትባት የሚሰጠው ልጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በኋላ እንደተደረሰበት የሳምባ በሽታ ክትባት ከጉንፋን፣ ሴፕቲሴሜያና ከሄርፒስ በሽታዎች ይከላከላል። ይህ ተጠንቶ የተደረሰበት ብቻ ነው። ያልተደረሰበት ስንት ይሆን?

ያልተመለሰው ጥያቄ

እንዴት ነው አንድ ክትባት ከታሰበለት በሽታ ውጪ ላሉ በሽታዎች ፈውስ ሊሆን የሚችለው? ይህ የአንባቢ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የሳይንቲስቶችም ጥያቄ ነው።

አንዱ ትንታኔ ደቂቀ ህዋሳት (ማይክሮኦርጋዝምስ) ቢለያዩም የሆነ አይነት አንቲጂን ይጋሩ ይሆናል የሚለው ነው።

አንቲጂንስ ማለት ሞሎኪዮሎች ናቸው። ሞሎኪዮሎቹን የተፈጥሮ የበሽታ መከላከያ ሠራዊታችን በሰላይነት ይጠቀማቸዋል። ባዕድ አካል ወደ ሰውነታችን ስለመግባቱ የሚጠቁሙት እነሱ ናቸው፤ አንቲጂኖች።

ለምሳሌ አንድ ህጻን የፀረ ሳምባ በሽታ ቢሲጂ ክትባት ብንወጋው መጀመርያ ያለቅሳል። ከዚያ ክትባቱ ሰውነቱ ውስጥ ይገባል። ከዚያ ሰውነቱ ከሆነ አንዳች አዲስ ዓይነት ፕሮቲን ጋር እውቂያ ይፈጥራል፤ እዚህ ጋ ነው ጨዋታው።

ሰውነት ያንን በዚያ ክትባት ውስጥ ያለን ፕሮቲን ሲያውቅ በሰበቡ ሌሎችንም ያውቃል? አንዴት ከተባለ ተመሳሳይ ፕሮቲኖቹ በሌሎች በማይታወቁና ባልታሰቡ የተህዋስም ሆነ የባክቴሪያ ቅንጣት ውስጥ መገኘታቸው ነው።

በዚህ የተነሳ አንድ ክትባት በፍጹም ላልታሰበ ቫይረስም ሆነ ባክቴሪያ መከላከያ በመሆን ሊሰራ ይችላል።

ሁለተኛው መላምት ደግሞ የሚከተለው ነው።

ሰውነታችን ክትባት ሲገባበት በጥቅሉ ተከላካይ ሠራዊቱ ይነቃቃል። በተጠንቀቅ ይሆናል። ልዩ ኃይልም፣ ተለዋጭ ሠራዊትም፣ ሁሉም በተጠንቀቅ ይሆናሉ። በዚህ የተነሳ ሌሎች ቫይረሶችና ባክቴሪያዎች ወደ ሰውነት ሲመጡ ከባድ ምት ስለሚያጋጥማቸው ይወገዳሉ።

ይህን ለማረጋገጥም የቢሲጂ ክትባት ለሆኑ ልጆች ተሰጣቸው። ከዚያ ለተለያዩ በሽታ አምጪ አቸንፍር (ፓቶጂኖች) እንዲጋለጡ ተደረገ። ከሳምባ በሽታ ብቻ አይደለም የተጠበቁት። ሰውነታቸው ሌሎችንም አቸንፍሮችን በጥንካሬ ሲዋጋ ተገኘ።

ሁለት ዓይነት በሽታን የመከላከያ ሠራዊት አለ። አንደኛው ለባዕድ ተንበርካኪ ነው። ባዕዱን ኃይል ተዋግቶ ሲረታ ይላመዳል። ከዚያ በኋላ ሺህ ክትባት ቢሰጥም አይዋጋም። ይለግማል። እንዳይላመድ በሚል ነው ክትባት ሲሰራ ራሱ በሽታውን አዳክመው የሚሰጡት። ደንብሮ እንዲነሳ። አለበለዚያ ይላመድና ይለግማል። እንዲያውም ከጠላት ጋር አብሮ ተስማምቶ ሊኖር ይችላል።

ሁለተኛው የበሽታን መከላከያ ሠራዊታችን ግን የተፈጥሮ ነው። ከእኛው ጋር የተፈጠረ (innate immune system) ነው። ይሄኛው አይዋጋም፤ ከተዋጋ ግን ድል አድራጊ ነው። አሁን ክትባቶች የሚያነቃቁት ክፍል ይህኛውን መሆኑ ነው ሌላው ሳይንቲስቶችን ያስደነቀው።

ዴንማርካዊው ሳይንቲስት እንደሚለው ቢሲጄ ክትባት ለምሳሌ የዲኤንኤ ጥልፍልፍን በአዲስ መልክ ነው የሚያዋቅረው። ይህም ማለት ቲቢን የሚከላከል ሠራዊትን ማዘጋጀት ብቻ ሳይሆን አዲስ በሽታ የመከላከል ዘዴን የተማረ ውቅር ሠራዊት ሰውነታችን ይፈጥራል።

"ይህ በመሆኑ ነው አንድ ተራ ክትባት አንዳንድ ሰዎችን ከካንሰርና ከእርጅና ጋር የሚመጣ የአንጎል ችግር [ዲሜንሺያ] ጭምር ሲከላከላቸው የምናየው።"

በሚደንቅ ሁኔታ የቲቢ ክትባት አሁን አሁን ለፊኛ ካንሰር እጅግ ወሳኝ መድኃኒት እየሆነ መጥቷል። ሁለቱን ምን አገናኛቸው?ነው ጥያቄው።

የፊኛ ካንሰር ታማሚዎች ደግሞ በዚህ መድኃኒት ከዳኑ በኋላ አልዛሚር ድርሽ አይልባቸውም። ይህም ሌላ አስደናቂ ነገር ነው።

አንድ አስደናቂ ውጤት እንጨምርና ይህን ነገር እንዝጋው።

ዴንማርካዊው ሳይንቲስት ፒተር እንደሚለው አንድ ጠብታ ክትባት በቂ ቢሆንም አንዳንድ ክትባቶች በርከት ተደርገው ሲወሰዱ ውጤታቸው በዚያ መጠን ሲያድግ ተስተውሏል።

ይህ ግን ክትባቱ ስለሚያስከትለው አሉታዊ ጎኑ የተጠኑ ጥናቶችን ሳያነሳ ነው። አንድ ክትባት ተደጋግሞ መወሰዱ ለሆኑ በሽታዎች ጠንቅ ሊሆንባቸው ይችላል። የሰውነት መከላከያ ሠራዊቱ አባላት ጡንቻ እንዲያወጡና እንዲጠነክሩ ያደርጋቸዋል።

በእርግጥ ይህ በክትባት ብቻ የሚመጣ ውጤት አይደለም። አንዳንድ ሰዎች በተፈጥሮ ከአንድ በሽታ ከዳኑ በኋላ መከላከያ ሠራዊታቸው ፈርጥሞ ይገኛል።

በኩፍኝ ተይዞ የዳነ ሰው ኩፍኝ ጭራሽ ካልያዘው ሰው ይልቅ ሌሎች በሽታዎችን ሊከላከል ይችላል።

ይህ በትክክል ለምን እንደሚሆን ባይታወቅም የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ተከላካይ ሠራዊት ጠላት አይቶ አንድ ጊዜ ከበረገገ በኋላ ያን ጠላቱን ታግሎ በመጣል ብርታቱን ስለሚያገኝ ነው የሚሉ ሳይንቲስቶች አሉ።

የመጨረሻው አስደናቂ የክትባቶች ትሩፋት

በ1980ዎቹ የዓለም ጤና ድርጅት ፈንጣጣ ከዓለም ጠፋ ብሎ አወጀ። ከዚያም ክትባቱ ራሱ ጠፋ። ስለዚህ ልጆች ይህን ክትባት መወጋት ቀረ ማለት ነው።

የሚደንቀው ይላል ሳይንቲስቱ ፒተር፤ በጊኒ ቢሳውም ሆነ በዴንማርክ የፈንጣጣ ክትባት ብዙ ትሩፋቶች እንዳሉት ይታወቅ ነበር። ስናቆመው ግን ፈንጣጣን ብቻ እያሰብን ስለ ሌሎች ትሩፋቶቹ ቸል ብለን ነበር።

አሁንም ተመሳሳይ ስህተት እየተሰራ ይመስላል።

ፖሊዮ ከምድረ ገጽ ጠፍቷል ተብሎ ታውጇል። አፍሪካም ባለፈው ወር ጠራርጌ አጥፍቼዋለሁ ብላ አውጃለች። አሁን ምናልባት ፖሊዮ በአፍጋኒስታንና በፓኪስታን ገጠሮች አልፎ አልፎ ሊያጋጥም ይችላል እንጂ ጠፍቷል።

ፖሊዮ ክትባት ሲሰጥ ግን ክትባቱ ሌሎች ያልታሰቡ በሽታዎችንም ይከላከል እንደነበር አልተጠናም። የፖሊዮ ክትባት በጊኒ ከፖሊዮ ሌላ ሞትን በ67 ከመቶ መቀነሱን አንድ ጥናት ደርሶበታል። ያን ጊዜ ፖሊዮ በጊኒ ጠፍቷል በሚባልበት ደረጃ ነው ታዲያ ይህ ውጤት የተመዘገበው።

ክትባቱ ምስጢራዊ ትሩፋት ነበረው ማለት ነው።

"አንድን በሽታ ከምድረ ገጽ ስናጠፋ ክትባቱን አብረን አሽቀንጥረን ስንጥለው ትልቅ ነገር ያሳካን ይመስለናል። ነገር ግን አንድን ክትባት ከድል በኋላ ስንጥለው ሞትን እየጨመርን እንደሆነ አናውቅም" ይላሉ ሳይንቲስቱ።

አዲስ የሚመጣልን የኮቪድ-19 ክትባት ምን ትሩፋት ይዞልን ይመጣ ይሆን?