ኮሮናቫይረስ፡ ዓለም አቀፉ የኮሮናቫይረስ ሟቾች ቁጥር ከ1 ሚሊዮን በለጠ

ኢንዶኔዥያ፣ ጃካርታ ቀብር ላይ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የዓለም ስጋት ሆኖ በቀጠለው ኮሮናቫይረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሆኗል። በተለያዩ አገራትም ወረርሽኙ እንደ አዲስ እያገረሸም ነው ተብሏል።

በሞት ቀዳሚ የሆኑት አሜሪካ፣ ብራዚልና ህንድ በዓለም አቀፍ ደረጃ በቫይረሱ የሞቱትን ግማሽ እንደሚይዙ ከጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።

የሟቾቹ ቁጥር ከዚህም የላቀ እንደሆነ በዘርፉ ያሉ ልሂቃን ይናገራሉ።

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ቁጥሩን "አስደንጋጭ" ነው ያሉ ሲሆን "በቫይረሱ ህይወታቸውን የተነጠቁት አባቶች፣ እናቶች፣ ሚስቶች፣ ባሎች፣ እህቶች፣ ወንድሞችና የስራ ባልደረቦች ነበሩ። ሁልጊዜም ቢሆን ልናስታውሳቸው ይገባል" በማለትም በቪዲዮ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኮሮናቫይረስ በቻይናዋ ግዛት ውሃን ከአስር ወራት በፊት ተነስቶ ዓለምን አጥለቅልቋል።

በአሁኑ ወቅት በ188 አገራት የኮሮናቫይረስ ሪፖርት የተደረገ ሲሆን 32 ሚሊዮን ህዝብም ተይዟል።

አገራት የኮሮናቫይረስን ስርጭት ለመግታት ያወጧቸው መመሪያዎችም በርካቶችን ሥራ አልባ አድርጓል፤ ምጣኔ ኃብቱን አሽመድምዷል።

በዚህም ሁኔታ አገራትም ሆነ የምርምር ማዕከላት የኮሮናቫይረስ ክትባትን ለማምረት እየተሽቀዳደሙና እየተሯሯጡ ቢሆንም ክትባቱ ከመገኘቱ በፊት የሟቾቹ ቁጥር 2 ሚሊዮን እንደሚደርስም የዓለም ጤና ድርጅት አስጠንቅቋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ 240 የሚሆኑ ክትባቶች ምርምር እየተደረገባቸው ሲሆን 40 የሚሆኑትም በክሊኒካል ሙከራ አሉ። ዘጠኝ ያህል ክትባቶች ደግሞ በሺዎች በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ሙከራ እየተደረገባቸውና መጨረሻ ደረጃ ላይ ናቸው።

ክትባቶችን ለማምረትና ለሰዎችም ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ እንዲሰጥ ለማድረግ አመታት ቢፈጅም ባለው የወረርሽኙ ጊዜ የማይሰጥና አጣዳፊ መሆን ሳይንቲስቶች ቀን ተሌት ሳይሉ እየተጣደፉም ይገኛሉ።

በዓለም ላይ አሜሪካ በቫይረሱ በተያዙም ሰዎች ቁጥርም ሆነ በሟቾች ቀዳሚ ስትሆን 205 ሺህ ዜጎቿንም ተነጥቃለች። በመቀጠልም ብራዚል 141 ሺህ 700 ሰዎች በቫይረሱ ሲሞቱ በህንድ ደግሞ 95 ሺህ 500 ሰዎች ህይወታቸው በቫይረሱ አልፏል።

ኮሮና
Banner