ዶ/ር አንቶኒ ፋውቺ በአሜሪካ ኮሮና በአስደንጋጭ ሁኔታ ሊያንሰራራ እንደሚችል አስጠነቀቁ

Dr Fauci

የፎቶው ባለመብት, EPA

የአሜሪካንን የኮቪድ ወረርሽኝ ትግል የሚመሩት እውቁ ዶ/ር አንቶኒ ፋውቺ ለሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ቀርበው ለእንደራሴዎች ማብራሪያ በመስጠት ላይ ነበሩ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት አሁን አገራቸው አሜሪካ በድጋሚ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ በወረርሽኙ ሊያዝባት ይችላል ብለዋል፡፡

‹‹የሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ወሳኝ ናቸው፡፡ ምናልባት ወረርሽኙ በአዲስ መልክ ሊያንሰራራም ይችላል፤ አስፈሪ ምልክቶችን እያየን ነው›› ብለዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአሜሪካ በኮቪድ 19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በአንዳንድ ግዛቶች እየጨመረ መጥቷል፡፡

ከዶ/ር ፋውቺ ጋር ቃላቸውን እንዲሰጡ በምክር ቤቱ የተጠሩ ሌሎች አራት የጤና ባለሞያዎች በዶናልድ ትራምፕ ጉዳይ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል፡፡

‹‹ለመሆኑ ዶናልድ ትራምፕ ብዙ ምርመራ አታድርጉ ብሏችሁ ያውቃል ወይ›› ተብለው የተጠየቁት የጤና ባለሞያዎቹ ‹‹በፍጹም›› ብለዋል፡፡

ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ በኦክላሆማ ምርጫ ቅስቀሳ በሚያደርጉበት ወቅት የጤና ባለሞያዎችን ‹‹እባካችሁ ብዙ ሰው አትመርምሩ፤ ብዙ ሰው ከመረመራችሁ ብዙ ሰው በሽታው እንደያዘው ይታወቃል›› ብያቸዋለሁ ሲሉ ለደጋፊዎቻቸው ተናግረው ነበር፡፡

ኋላ ላይ ዋይት ሃውስ ፕሬዝዳንቱ እንዲያ ያሉት እኮ ለቀልድ ነው ሲል አስተባብሎላቸዋል፡፡

የጤና ባለሞያዎቹ ጥያቄው የቀረበላቸው ይህንን የትራምፕን የኦክላሆማ ምርጫ ቅስቀሳ ተከትሎ ነው፡፡

የጤና ባለሞያዎቹ ለሕግ መወሰኛው ምክር ቤት እንደመሰከሩት በሚቀጥሉት ወራት በወር ከ40 እስከ 50 ሚሊዮን ሰዎችን ለመመርመር እቅድ ተይዟል፡፡

በኦክላሆማው ንግግራቸው ዶናልድ ትራምፕ ‹‹ብዙ ሰው አትመርምሩ›› ስለማለታቸው ዋይትሃውስም ይሁን የጤና ባለሞያዎች ቢያስተባብሉላቸውም ማክሰኞ ለታ ትራምፕ ራሳቸው ‹‹እኔ እየቀለድኩ አልነበረም›› ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር ፋውቺ በቀጣይ ቀናት ወረርሽኙ በአስደንጋጭ ሁኔታ ሊያንሰራራባቸው ይችላል ካሏቸው አካባቢዎች መሀል ደቡባዊና ምዕራባዊ አሜሪካ ይገኙባቸዋል፡፡

ከቀናት በፊት በአንድ ቀን በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር 30ሺህ ደርሶ ነበር፡፡

‹‹ይህ አስደንጋጭ ቁጥር ነው›› ብለዋል ፋውቺ፡፡ ‹‹ይህ የሚያሳየው ወረርሽኙ በማኅበረሰቡ ውስጥ ዘልቆ መግባቱን ነው፡፡››

ዶ/ር ፋውቺ ለኮቪድ-19 ፍቱን ክትባት በዚህ የፈረንጆች ዓመት መጨረሻ እንደሚገኝለት ያላቸውን ተስፋ ለምክር ቤቱ አባላት ገልጸዋል፡፡

አሪዞና፣ ነቫዳ፣ ቴክሳስ በቀን የተያዦች ቁጥር እየገሰገሰባቸው ከሚገኙ ግዛቶች ይጠቀሳሉ፡፡

ካሊፎርኒያ፣ ሳውዝ ካሮላይና፣ ሚሲሲፒ እና ሊዊዚያናም እንዲሁ የተያዦች ቁጥር በአስደንጋጭ ሁኔታ እየጨመረባቸው ነው፡፡

አሁን 2.3 ሚሊዮን አሜሪካዊያን በኮሮና የተያዙ ሲሆን ከ120ሺህ በላይ ሞተዋል፡፡

ኮሮና