ኮሮናቫይረስ፡ ሁለት ጊዜ ከቡራዩ የኮቪድ-19 ህክምና ማዕከል ያመለጡት እስረኞች እየተፈለጉ ነው

ጭምብል ያጠለቀ ወጣት በአዲስ አበባ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስራቅ ሸዋ ቦራ ወረዳ የሕግ ታራሚዎችና በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጠ ሁለት ወጣቶች ቡራዩ ወደሚገኘው የኮቪድ-19 የህክምና ማዕከል ከተወሰዱ በኋላ፤ ከህክምና ማዕከሉ ለሁለተኛ ጊዜ ማምለጣቸው እና ፖሊስ እየፈለጋቸው እንደሆነ ተነገረ።

ሻሎ ፊታላ እና ኢሳቾ አበበ የተባሉት ሁለት ወጣቶች እና ሌሎች 3 ታራሚዎች በምስራቅ ሸዋ ዞን ቦረ ወረዳ ባለ በእስር ቤት ሳሉ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው መረጋገጡን ተከትሎ ለህክምና ወደ ቡራዩ ከተማ መወሰዳቸውን የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ሚሊዮን ታፈሰ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ከላይ ስማቸው የተጠቀሰው ሁለቱ ወጣቶች፤ ወደ ቡራዩ በተወሰዱ በጥቂት ቀናቶች ውስጥ ከለይቶ ህክምና ማዕከሉ ማምለጣቸውን ኢንስፔክተር ሚሊዮን ተናግረዋል።

ሁለቱ ወጣቶች ከለይቶ ህክምና መስጫ ማዕከሉ ካመለጡ በኋላ ወደ ቤተሰቦቻቸው መኖሪያ ቀዬ መመለሳቸውን ኢንስፔክተሩ ተናግረዋል።

"ወጣቶቹ ከህክምና መስጫው አምልጠው ወደ ወረዳችን ነው የመጡት። በደረሰን ጥቆማ መሠረት ህዝቡን አስተባብረን አንድ የገጠር መንደር ውስጥ ከያዝናቸው በኋላ ወደ ቡራዩ መልሰናችዋል" ብለዋል።

ወጣቶቹ ወደ ለይቶ ማቆያ ማዕከሉ እንዲመለሱ ከተደረጉ ከአራት ቀናት በኋላ ማለትም ቅዳሜ ነሐሴ 2 ለሁለተኛ ጊዜ ከማዕከሉ ማምለጣቸውን የፖሊስ አዛዡ ተናግረዋል።

"ለሁለተኛ ጊዜ ማምለጣቸውን ከሰማን በኋላ ፍለጋችንን አጠናክረን እየሰራን ነው። ቤተሰቦቻቸው ጋር የሉም። ገጠር ድረስ የህብረሰብ ክፍል መረጃ አድርሰናል። እስካሁን ግን አለገኘናቸውም። ምናልባት ወደ ሌላ ወረዳዎች ውስጥ ተደብቀው ሳይቀሩ አይቀርም" ብለዋል።

የቦራ ወረዳ ምክትል የጤና ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ፍጹም ወርቅነህ፤ በኮሮናቫይረስ ተይዘው "ከለይቶ ማከሚያ ማዕከል ያመለጡት ወጣቶች ጉዳይ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሮብናል" ብለዋል።

ኮሮና
Banner