ኮሮናቫይረስ ለምን ጥቁሮች ላይ እንደሚበረታ ሊጠና ነው

የሕክምና ባለሙያዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዩናይትድ ኪንግደም ሳይንቲስቶች ኮሮናቫይረስ ለምን ከነጮች ይልቅ ጥቁሮችንና ሌሎች የእስያ ዘር ያላቸውን በይበልጥ እያጠቃ እንደሆነ ለማጥናት ተነስተዋል።

ለዚህ ጥናታቸው የሚሆን በሚሊዮን ፓውንድ ገንዘብ ከመንግሥት ሊለቀቅላቸው መሆኑም ተሰምቷል።

ጥናቱ በስድስት ግዙፍ ፕሮጀክቶች የተከፋፈለ ነው።

ዘረመል ከቫይረሱ ጋር የተለየ ቁርኝት ይኑረው አይኑረው የሚጠና ሲሆን፣ ዕለታዊ እንቅስቃሴ፣ የሥራ ባህሪ፣ የኑሮ ሁኔታና ሌሎችም በጥናቱ ትኩረት ይደረግባቸዋል።

ከስድስቱ የፕሮጀክቱ ክፍሎች አንዱ ፕሮጀክት ብቻውን 30 ሺህ የጤና ባለሙያዎችን ለአንድ ዓመት እየተከታተለ ጥናቱን ያገባድዳል ተብሎ ይጠበቃል

ውጤቱ እንደታወቀ መንግሥት በጥናቱ ግኝት ላይ ተመስርቶ እርምጃ ይወስዳል።

በሌስተር ዩኒቨርስቲ የኅብረተሰብ ጤና ፕሮፌሰር ካምሌሽ ኩንቲ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የጥናት ውጤቱ በቶሎ ጥቁሮችን፣ እስያዊያን እና ሌሎች ቡድኖችን ለመታደግ እንደሚውል ተስፋ ያደርጋሉ።

የዚህ ግዙፍ ጥናት ውጤት ለጥቁር ማኅበረሰብ መሪዎችና ለእስያ ማኅበረሰብ የሚጋራ ሲሆን በቀጣዩ ስለሚወሰዱ እርምጃዎችም ምክክር ይደረጋል።

"ለምሳሌ ተሰባስቦ በአንድ ላይ መኖር ለኮሮናቫይረስ አጋልጧቸዋል የሚል ውጤት ካገኘን ወይም ደግሞ የሰውነት እንቅስቃሴ አለማድረጋቸው ነው የጎዳቸው የሚል ውጤት ካገኘን ይህን ተመስርተን መፍትሄ እናበጃለን።"

በተለያዩ አካባቢዎች እየወጡ ያሉ ጥናቶች እንዳሳዩት ጥቁሮችና እስያውያን ከአገሬው ሰዎች ይልቅ ለኮቪድ-19 ተጋላጭ ሆነዋል።

ይሁንና ጥቁሮችና እስያዉያን ከነጮች የበለጠ ለምን ተጎጂ ሆኑ ለሚለው ከመላምት ያለፈ አስተማማኝ መንስኤ እስከዛሬ በጥናት ተደግፎ አልወጣም።

እስካሁን እየተሰጡ ያሉ መላምቶች የሚከተሉትን ነጥቦች የያዙ ናቸው፡-

• ጥቁሮች በአኗኗራቸው ብቻም ሳይሆን የሚሰሩት ሥራ ከብዙ ሰዎች ጋር የሚያገናኝ ስለሆነ ለተጋላጭነት የቀረቡ ናቸው፤ ለምሳሌ በጽዳት፣ በሾፌርነት እና በጤና ረዳትነት መሰማራታቸው።

• ለመሰረታዊ የጤና ምርመራ ቅርብ አለመሆናቸው

• በስኳር፣ በደም ግፊት በአስም የሚሰቃዩ መሆናቸው እና አለቅጥ ውፍረት በብዛት ስለሚያጠቃቸው

• ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ስለማያዘወትሩ

በዩናይትድ ኪንግደም የሕክምና ጉዳዮች አማካሪ ፕሮፌሰር ክሪስ ዊቲ ይህንን ጥናት በበጎ ተመልክተውታል። "ትክክለኛ እርምጃ እንድንወስድ ትክክለኛ ጥናት ማድረግ ይኖርብናል። ይህ ጥናት ትክክለኛ ውጤት ላይ ያደርሰናል" ይላሉ ፕሮፌሰሩ።

ይህ ጥናት ጥቁሮችንና ሌሎች የእስያ ዝርያ ያላቸውን እንግሊዛውያን በጾታ፣ በዕድሜ፣ በገቢ መጠን ከፋፍሎ የሚያጠና ሲሆን 30 ሺህ ሐኪሞችን፣ ነርሶችንና ሌሎች የጤና ባለሙያዎችን በቅርብ ሆኖ ለአንድ ዓመት ክትትል ያደርግባቸዋል።

ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲና ሳውዝሃምፕተን ዩኒቨርስቲ ያዋቀሯቸው የጥናት ቡድኖች ደግሞ ጥቁሮችና እስያዊ ዝርያ ያላቸውን ታማሚዎች በተለየ ይከታተላሉ፣ ያጠናሉ። የሞቱትንም ቢሆን ሰነዳቸውን ከሆስፒታሎች ወስደው ይመረምራሉ።

ጥናቱ ከዚህ በፊት በዩናይትድ ኪንግደም ባዮባክን ፕሮጀክት የተወሰዱ የግማሽ ሚሊዮን ሰዎችን የዘረመል ናሙና፣ የሽንትና የምራቅና ደም ቅንጣቶች በስፋት ይመረምራል፣ ውጤቱንም ይተነትናል ተብሏል።

ኮሮና
Banner