የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ደብረፅዮን መግለጫ አንድምታ

ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረ ሚካኤል

የፎቶው ባለመብት, TMMA/FACEBOOK

የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረ ሚካኤል መንግሥት ከሰብዓዊ መብት ጥሰትና ከከፍተኛ ሙስና ጋር በተያያዘ የጀመረው ዘመቻ በማስመልከት በሰጡት መግለጫ ከድህነት አረንቋ ለመውጣት በትጋት እየሰራ ያለን ህዝብ ወደ ማንበርከክ አጀንዳ ዞሯል ብለዋል።

"ነገሩ ከሰብዓዊ መብትና ሙስና ጥያቄዎች ወጥቶ ይህንን ህዝብ ወደ መምታት የፖለቲካ እርምጃ ሄዷል፤ ለዚህም ነው አንቀበለውም ያልነው'' ሲሉ ምክትል ፕሬዝዳንቱ አቋማቸውን ገልጸዋል።።

የቀድሞ የፌደራል ስነ ምግባርና ፀሩ ሙስና ኮሚሽን አቃቤ ህግ ክፍል ሃላፊ የነበሩት አቶ ዮሃንስ ወልደ ገብርኤል የጠቅላይ አቃቤ ህግ በከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰትና ሙስና ጠርጥሬያቸዋለሁ ያላቸውን ግለሰቦች በቁጥጥር ስር የማዋል እርምጃ አንድ ብሄር ላይ ያነጣጠረ ነው ብለው አያምኑም።

''የፍትህ አሰራሩ ሁሉ አሁን ባለው የጎሳ ፖለቲካ አስተሳሰብ ቢቃኝ ለእኔ የሚደንቀኝ አይሆንም'' በማለት እነ አቶ ስዬ አብርሃ በሙስና የተከሰሱበትን ወቅት በምሳሌነት ያነሳሉ።

በወቅቱ በወሳኝ የስልጣን ማማዎች ላይ የነበሩትና እነ አቶ ስዬንም የከሰሷቸው ከትግራይ የሆኑ ሰዎች በመሆናቸው በዚያ ወቅት ምንም የተባለ ነገር እንዳልነበር ይናገራሉ።

''የዚያን ጊዜ ግን የትግራይ ማህበረሰብን ለማጥቃት ነው አልተባለም ነበር'' ይላሉ አቶ ዮሃንስ።

በተቃራኒው በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር የሆኑት አቶ የማነ ዘርአይ የፀረ ሙስና ዘመቻው የትግራይ ብሄር ላይ ያነጣጠረ ነው በማለት ይከራከራሉ።

አቶ የማነ አቃቤ ህግ መግለጫ አውጥቶ እስሮች ተፈጻሚ መሆን ከጀመሩ በኋላ ከመንግሥት ጋር ግንኙነት ያላቸውም ሆነ የሌላቸው የመገናኛ ብዙሃን 'አንድ ቡድን፣ አንድ ቦታ ላይ የተሰበሰቡ' በማለት ይዘግቡ የነበረበት መንገድ ወደ ትግራይ ያነጣጠረ መሆኑን የመጀመሪያ መከራከሪያቸው አድርገው ያስቀምጣሉ።

በሁለተኝነት ደግሞ እርምጃው ትኩረት ያደረገው በጣም ወሳኝ በሆኑ የመንግሥት ድርጅቶች እንደ መከላከያና ሜቴክ በመሰሉና በተጨማሪም ጨምሮ በንግድ ማህበረሰቡ ላይ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች በብዛት ያነጣጠሩት በአንድ ብሄር ላይ ብቻ ነው ይላሉ።

አክለውም ግለሰቦቹ አጥፍተው ከሆነ መታሰራቸው ምንም ችግር የለውም፤ ነገር ግን ለምሳሌ ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው በቁጥጥር ስር ሲውሉ ዜናው እና የምርመራ ዘጋቢ ፊልም የቀረበበት መንገድ ህግን የጣሰና አንድ ብሄር ላይ ያተኮረ ለመሆኑ ማሳያ እንደሆነ ይገልፃሉ።

በተጨማሪም ባለፉት ዓመታት የተሰሩትን ነገሮች ሁሉ መጥፎ እንደነበሩ አድርጎ ማቅረብም ሌላው ትልቅ ችግር ነው ብለው ያምናሉ።

''የደህንነትና የመከላከያ ኃይሉ የተሰበረ ተደርጎ ሲቀርብ ይህችን ሃገር በምን ሊያስተዳድሯት ነው በሚያስብል ደረጃ ነው።'' የሚሉት አቶ የማነ ''ኢትዮጵያ ውስጥ የዲሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ችግር እንደነበረ ሁላችን የምናውቀው ነገር ሆኖ ሳለ፤ ኢኮኖሚው፣ መከላከያውና የደህንነት ቢሮው ጥሩ ተብለው የሚጠቀሱ ናቸው።''

እነዚህን ሁሉ ምንም ጥሩ ጎን እንዳልነበራቸው አድርጎ ማቅረቡ ተገቢ አይደለም በማለት ሃሳባቸውን ያጠቃልላሉ።

በሌላ በኩል ለአቶ ዮሃንስ ትልቁ ጥያቄ በብዙ ችግሮች የተተበተቡት የአገሪቱ የፍትህ ተቋማት አቅመ ቢስነት እንደሆነ አፅንኦት ይሰጣሉ።

''የምርመራ፣ የአቃቤ ህግ፣ የፍርድ ቤትና የማረሚያ ተቋማት ብቃታቸውንና አቅማቸውን አጥተዋል፤ ተዳክመዋል። የማህበረሰቡን አመኔታ ያገኙ ተቋማት ናቸው ብዬ አላምንም።'' የሚሉት አቶ ዮሃንስ ተቋማቱ አቅም ስለሌላቸው ግን መጠየቅ ያለባቸው ሰዎች ሳይጠየቁ ዝም መባል እንደሌለባቸው ያስረዳሉ።

የፀረ ሙስና ዘመቻውን በሚመለከት የትግራይ ክልል ከፌደራል መንግስት የተለየ አቋም መያዙን እንዴት እንደሚረዱት የተጠየቁት አቶ ዮሃንስን ''ህገ መንግሥቱ ላይ ምንም የሚያምታታ ነገር የለም፤ ማንኛውም ሰው ተገቢውን ስርአት ተከትሎና የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ካሟላ፤ አይደለም የፌደራል መንግስቱ ሃይል፤ የራሱ የክልሉ መንግስት ያንን ተጠርጣሪ ያለ ምንም ጥያቄ ማቅረብ ይገባዋል።'' በማለት ይህ ካልሆነ ግን ህገመንግስቱን ላይ የተቀመጠው ነገር እርባና ቢስ ሆነ ማለት እንደሚሆነ ያስረዳሉ።