ኤርትራውያን ስደተኞች በድንበር በኩል ምዝገባ ተከልክለናል አሉ

እኤአ በ2017 በእንዳባጉና ከተማ ኤርትራውያን ስደተኞች ሲመዘገቡ

የፎቶው ባለመብት, IOM

ሠሞኑን በድንበር አካባቢ የተሰማውና ተግባራዊ እየሆነ ያለው የኤርትራ ስደተኞችን ያለመመዝገብ ሂደት ቢቢሲ ያነጋገራቸው ስደተኞችን አስጨንቋል።

ኤርትራውያን ከሀገራቸው ወጥተው ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ በድንበር አካባቢ ምዝገባ እንደሚደረግ ይታወቃል። ከዚያ በኋላም ወደ ምዕራብ ትግራይ እንዳ'ባጉና ከተማ ይመጡ ነበር።

እዚህ ስፍራም ስለግለሰቦቹ አስፈላጊው መረጃ ከተጠናቀረ በኋላ ወደ ስደተኞች መጠለያ እንዲገቡ የሚደረግበት አካሄድ ነበር።

ዛላንበሳ ድንበር ፋፂ ከተማ እስካሁን ኤርትራውያን ስደተኞችን እየመዘገቡ ሲያስገቡ የነበሩ የፌደራል መንግሥት የስደተኞችና የስደት ተመላሾች ተቋም ሠራተኞች 'አንመዘግብም' ማለታቸውን ቢቢሲ ከስደተኞቹ መረዳት ችሏል።

ስሟ እንዳይጠቀስ የጠየቀችና በኤርትራ ወታደር የነበረች ስደተኛ ከጓደኛዋ ጋር በመሆን የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጣ ከገባች ስድስት ቀን እንደሆናት ለቢቢሲ ተናግራለች።

ነገር ግን ፋፂ አካባቢ የሚገኙ ስደተኞችን የሚመዘግቡ አካላት ግን ሊመዘግቧቸው ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ታስረዳለች "ወታደሮች እንደነበርንና ለድንበር አሻጋሪ ደላሎች 40 ሺህ ናቅፋ ከፍለን እንደመጣን ነገርናቸው። 'የመጣችሁበትን ቦታ ግልጽ ተናገሩ' አሉን። ምን ያህል ቀን እንደተጓዝን እና ሠንዓፈ ከተማ እንደደረስን አስረዳን። ' ቦታውን በግልጽ አላወቃችሁትም። ሁለታችሁ የምትናገሩት ሠዓት የተለያየ ነው። ስለዚህ አንመዘግብም' አሉን" ብላለች።

አክላም ስለ ጓደኛዋ ስታስረዳ፣ ወታደር እንደነበረች፣ የነበረችበትን አሃድ ጨምሮ የሚያስረዳ መታወቂያ ብታሳይም ሊመዘግቧት ፈቃደኞች ሳይሆኑ መቅረታቸውን ትናገራለች።

ቢቢሲ ባደረገው ማጣራት ፋፂ ላይ ወታደር የነበሩ ኤርትራውያን ስደተኞች ተመዝግበው መግባት እንዳልቻሉ እና መቆያ አጥተው መቸገራቸውን መረዳት ችሏል።

የፋጺ ከተማ

እነዚህ ወታደር የነበሩ ስደተኞች በአሁኑ ሰዓት በፋፂ በግለሰቦች ቤት ለመቆየት የተገደዱ ሲሆን፣ ወደ ኤርትራ መመለስ ስለማይችሉም እግራቸው ወደመራቸው የትግራይ ከተሞች ለመሄድ ተገደናል ይላሉ።

ቢቢሲ በድርጅቱ ከሚሰሩ ግለሰቦች መረዳት እንደቻለው በይፋ አይነገር እንጂ የፌደራል መንግሥት ከኤርትራ የሚመጡ ስደተኞች አቀባበል ላይ አዲስ መመዘኛ መስፈርት ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው እነዚህ በፋፂ የሚገኙ የፌደራል መንግሥቱ ሠራተኞች ግን ይህንን መረጃ ሊያረጋግጡ አልፈለጉም።

ይሁን እንጂ ወታደሮችና የመንግሥት ሠራተኞች ከነበሩ ስደተኞች ውጪ ሌሎች እንዳይመዘገቡ ትዕዛዝ መሰጠቱን ቢቢሲ ከቅርብ ምንጮቹ መረዳት ችሏል። ይህ አሰራር በቃል የተላለፈ እንጂ በጽሑፍ የተሰጠ ነገር አለመሆኑንም ምንጮቹ አክለው አስረድተዋል።

በአሁኑ ጊዜ የስደተኛ መጠለያዎች ባይዘጉም አሁን ባለው ሁኔታ ግን እንደማይቀጥሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ከዚህ በፊት ድንበር አቋርጠው ቤተሰቦቻቸው ወደሚገኙባቸው የተለያዩ የትግራይ ከተሞች ያቀኑ ስደተኞች ወደ ስደተኞች መጠለያ ሄደው ለመመዝገብ ሲጠይቁ ወደ ድንበር ተመልሰው ይመዘገቡ ነበር።

በአሁኑ ወቅት ግን መዝጋቢዎቹ 'የት ቆይታችሁ ነበር? እና በየት በኩል አልፋችሁ?' በሚል ጥያቄ እንደማይመዘግቧቸው ስደተኞቹ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

በአካባቢው ነዋሪ የሆኑ እማኞችም ይህንኑ ያረጋግጣሉ። ከነዚህም መካከል የፋፂ ከተማ ነዋሪ የሆኑትና በንግድ ስራ የሚተዳደሩት አቶ ደጀኔ ሐጎስ ናቸው።

" ብዙ ኤርትራውያን ልጆች ይዘው፣ ለደላሎች ገንዘብ ከፍለው፣ ከድንበር ጠባቂዎች ተደብቀው፣ እዚህ ከደረሱ በኋላ አንመዘግባችሁም በመባላቸው ሲቸገሩ አይቻለሁ። ለምሳሌ በቅርቡ ከ40 በላይ ስደተኞች አዝነው እያለቀሱ ወደ ኤርትራ ሲመለሱ ተመልክቻለሁ" ሲሉ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ወደ ኤርትራ መመለስ ከባድ የሆነባቸውም እግራቸው ወደመራቸው የትግራይ ከተማ እንደሚያቀኑም ጨምረው ይናገራሉ።

በዚህ ጉዳይ ላይ ምላሽና ማብራሪያ ለማግኘት ወደ የፌደራል የስደተኞችና የስደት ተመላሾች ስልክ ደጋግመን ብንደውልም መልስ የሚሰጥ አካል ማግኘት አልተቻለም።

ቢቢሲ ከድርጅቱ "በአዋጅ ቁጥር 1110/2019 መሰረት እየሰራን ነው" የሚል አጭር የጽሑፍ መረጃ ያገኘ ሲሆን ላሉን ተጨማሪ ጥያቄዎች ግን ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

አዋጅ 1110/2019 የተሻሻለው ባለፈው ዓመት ሲሆን በኤርትራውያን ላይ ስለተደረገው አዲስ የምዝገባ አሰራር ግን የሚለው ምንም ነገር የለም።

ቢቢሲ ከተቋሙ መደበኛ ባልሆነ መልኩ ባገኘው መረጃ መሰረት ከሆነ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ኤርትራውያን ስደተኞችን የመመዝገቢያ አዲስ አሰራር ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል።

ይሁን እንጂ ይህ አሰራር በይፋ ለተገልጋዮች አልተገለጸም።

በአሁኑ ወቅት በትግራይ በዋናነት ኤርትራውያን ስደተኞችን ተቀብለው የሚያስተናግዱ አራት ጣቢያዎች ይገኛሉ።

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ኤጀንሲ በ2019 መጨረሻ ላይ ባወጣው ሪፖርት እንዳስታወቀው በትግራይና በአፋር ክልል በሚገኙ የስደተኛ ጣቢያዎች 140 ሺህ ገደማ ኤርትራውያን ስደተኞች ይገኛሉ።

ከእነዚህ መካከል ግማሽ ያህሉ ወደ ኢትዮጵያ የገቡት በዚያ አመት መሆኑን ሪፖርቱ ጨምሮ ያስረዳል።