የኮሮናቫይረስ የዓለም ጤና ስጋት በሆነባቸው ባለፉት ወራት ወረርሽኙን በመፍራት በርካቶች በጣም አስፈላጊ ለሆኑ የቴና አገልግሎቶች ወደ ህክምና ተቋማት ከመሄድ እየተቆጠቡ መሆናቸው የጤና ባለሙያዎችን እያሳሰበ ነው። ከእነዚህም መካከል የእርግዝና ክትትል ለማግኘትና ለወሊድ ወደ ሐኪም ቤቶች መሄድ ያለባቸው እናቶች ስጋት ይጠቀሳል። ከእነዚህ ውስጥም ወ/ሮ መሠረት* ተመሳሳይ ስጋት ነበራት፤ ነገር ግን የሚጠበቅባትን ጥንቃቄ አድርጋ ከሳምንታት በፊት ሐኪም ቤት ውስጥ ወልዳለች። ነገር ግን ቀደም ሲል የምታውቃቸው ነገሮች በወረርሽኙ ምክንያት ተቀይሯል ስትል የገጠማትን ነገሮች ያሰፈረችበትን የግል ማስታወሻ ለቢቢሲ አጋርታለች።
ቀጥታ ዘገባ
የተጠቀሱት ሰዓቶቸ የዩናይትድ ኪንግደም ናቸዉ
በምዕራብ አፍሪካ አገራት ውስጥ ወረርሽኙ እየተስፋፋ ነው ተባለ
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በበርካታ አፍሪካ አገራት ውስጥ በፍጥነት እየተስፋፋ ይገኛል። በምዕራብ አፍሪካ ውስጥ የሚገኙ በርካታ አገራት ቫይረሱ የሚገኝባቸው ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን በሚያወጧቸው ሪፖርቶች እያመለከቱ ነው። ከእነዚህም መካከል፡
• ኮትዲቯር፡ አዲስ በበሽታው የተያዙ 402 ሰዎችን በማግኘት አጠቃላይ የህሙማኑ ቁጥር 7,276 ደርሷል። ከእነዚህ ውስጥም ሦሰት ተጨማሪ ሰዎች መሞታቸው በመመዝገቡ አጠቃላይ የሟቾች ቁጥር 52 ሆኗል።
• ሴኔጋል፡ 144 አዳዲስ ህሙማን ማግኘቷን ስታስታውቅ ተጨማሪ ሦስት ሰዎች ሞተዋል። አጠቃላይ የህሙማን ቁጥር 5,783 የደረሰ ሲሆን የሟቾች ቁጥር ደግሞ 55 ደርሷል።
• ኒጀር፡ ቅዳሜ ከሌላ አገር በመጡ ዘጠኝ ሰዎች ላይ ቫይረሱ ተገኝቷል። በአጠቃላይ ኒጀር ውስጥ 1,035 በሽታው ያለባቸው ሰዎች ተመዝግበው 67ቱ ህይወታቸው አልፏል።
• ቶጎ፡ አዲስ ስድስት በበሽታው የተያዙ ሰዎች ያገኘች ሲሆን በአጠቃላይ 561 ሰዎች ላይ ቫይረሱ መገኘቱን አስታውቃ የ13 ሰዎች ሞት ተመዝግቧል።
• ቤኒን፡ ውስጥ 53 አዳዲስ ህሙማን በመመዝገባቸው በአገሪቱ ያሉትን የበሽታው ተጠቂዎች ቁጥር ወደ 650 ከፍ አድርጎታል። እስካሁንም የ11 ሰዎች ህይወት አልፏል።
• ቡርኪናፋሶ፡ ውስጥ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በማኅበረሰብ ደረጃ እየተሰራጨ መሆኑን መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ነው። በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች ቁጥር 902 የደረሰ ሲሆን 53 ሰዎች ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ ምክንያት ህልፈት ተዳርገዋል።
በኢትዮጵያ ተጨማሪ 91 ሰዎች ከኮቪድ-19 ሲያገግሙ 63 አዲስ ህሙማን ተገኙ
ባለፉት 24 ሰዓታት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተሰባሰቡ 4 ሺህ 457 ናሙናዎች ላይ በተደረገ ምርመራ 63 ሰዎች ላይ የኮሮናቫይረስ መገኘቱ ተገለጸ።
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የሕብረተሰብ ጤና ተቋም ዛሬ ባወጡት ዕለታዊ የወረርሽኙ ሁኔታ ሪፖርት ላይ እንደተገለጸው በሽታው ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል 21ዱ ሴቶች ሲሆኑ 42ቱ ወንዶች ናቸው።
ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል 31 ከአዲስ አበባ፣ 9 ሶማሌ፣ 5 ከኦሮሚያ፣ 4 ድሬዳዋ፣ 4 አፋር፣ 3 አማራ፣ 3 ከጋምቤላ፣ 2 ደቡብ፣ 1 ከትግራይና 1 ሐረሪ ክልሎች ናቸው።
ዕለታዊው መግለጫ ከዚህ በተጨማሪም ከዚህ በፊት በወረርሽኙ መያዛቸው ተረጋግጦ የህክምና ክትትል ሲደረግላቸው ከነበሩ ሰዎች መካከል ተጨማሪ 91 ሰዎች ከበሽታው በማገገማቸው እስካሁን በኢትዮጵያ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥርን 1213 አድርሶታል።
በቫይረሱ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥርም በ2 የጨመረ ሲሆን በዚህም በአገሪቱ ከበሽታው ጋር በተያያዘ ለህልፈት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር 74 ደርሷል።
በኢትዮጵያ እስካሁን 216 ሺህ 328 ናሙናዎች ላይ ምርመራ በማድረግ በአጠቃላይ 4 ሺህ 532 ቫይረሱ ያለባቸውን ሰዎች አግኝታለች።
በእንግሊዝ ወደ መጠጥ ቤት ጎራ የሚሉ ሰዎች መመዝገብ ሊኖርባቸው ይችላል ተባለ
እንግሊዝ ውስጥ ያሉ መጠጥ ቤቶች የደንበኞቻቸውን አድራሻ መዝግበው የመያዝ ግዴታ ሊኖርባቸው እንደሚችል የአገሪቱ ጤና ባለስልጣን ገለጹ። የኮሮናቫይረስ ህሙማንን ለመለየት የሚደረገው ምርመራና ህሙማኑ በሽታውን ሊያስተላልፉባቸው ይችላሉ ከተባሉ ሰዎች ጋር የሚኖራቸውን ንክኪ ለይቶ ለማወቅ መጠጥ ቤቶች ደንበኞቻቸውን እንዲመዘግቡ ሊጠየቁ እንደሚችሉ የጤና ሚኒስትሩ ማት ሐንኮክ ተናግረዋል።
ተጨማሪ ያንብቡበሽታውን ለመቆጣጠር ችላለች በተባለችው ደቡብ ኮሪያ ቫይረሱ እያገረሸ ነው
የቫይረሱን ስርጭት እንደተቆጣጠረችው ሲነገርላት የነበረችው ደቡብ ኮሪያ በግዛቷ ውስጥ በኅብረተሰብ ውስጥ በነበረ ስርጭት የተያዙ ህሙማንን ማግኘቷ ተገለጸ።
ዛሬ በምርመራ እንደተረጋገጠው አብዛኞቹ የውጪ አገር ጉዞ ታሪክ የሌላቸው ሰዎች የሚገኙበት 48 አዲስ ሰዎች ላይ ቫይረሱን እንዳገኘች አረጋግጣለች።
የአገሪቱ ትልልቅ ከተሞች በሆኑት በዋና ከተማዋ ሴኡልና በዴጆን ውስጥ የተከሰተውን ወረርሽኝ ለመቆጣጠር ጥረት እያደረገች ሲሆን ቫይረሱ የሚገኝባቸው ከውጪ በሚመጡ ሰዎች ቁጥር ቀንሷል።
ደቡብ ኮሪያ የዛሬውን ጨምሮ በአጠቃላይ 12 ሺህ 421 ሰዎች ላይ በሽታውን ያገኘች ሲሆን 280 ሰዎች በወረርሽኙ ሳቢያ ሞተውባታል።
ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች በመመርመር በዓለም ደረጃ አድናቆትን ያገኘችው ደቡብ ኮሪያ ይህም የበሽታውን መስፋፋት መቆጣጠር በሚቻልበት ደረጃ ላይ እንዲቆይ ማድረግ ችላለች ተብሏል።
አገሪቱ ጥላው የነበረውን የእንቅስቃሴ ገደብ በሚያዚያ ወር ላይ ማላላት በጀመረችበት ጊዜ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ወረርሽኙ መስፋፋት ጀምሮ ነበር።
በግንቦት ወር መጨረሻ ላይ 10 ሚሊዮን ነዋሪ ባላት በዋና ከተማዋ የታየውን የህሙማን ቁጥር መጨመርን ተከትሎ ባለስልጣናት የእንቅስቃሴ ገደብ መልሰው ጥለው ባለፈው ሳምንት ነበር እንዲነሳ ያደረጉት።
"እንደ ቆሻሻ ነው አውጥተው የወረወሩን" ኢትዮጵያውያኑ በሊባኖስ
በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት እየተባባሰ የመጣውን የሊባኖስ ምጣኔ ሃብት ማሽቆልቆል የኢትዮጵያውያኑን የቤት ሠራተኞችንም ኑሮ አክፍቶባቸዋል። በርካታ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሊባኖሳውያንም ለቤት ሠራተኞቻቸው መክፈል አንችልም በሚልም እያባረሩ ይገኛሉ። በዚህ ሳምንትም 100 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የቤት ሰራተኞች በመዲናዋ ቤይሩት በሚገኘው የኢትጵያ ቆንስላ በር ላይ አሰሪዎቻቸው በትነዋቸው ሄደዋል።
ተጨማሪ ያንብቡአሜሪካዊው ኮሜዲያን በድንገት ኮሮናቫይረስ እንዳለበት አወቀ
አሜሪካዊው ኮሜዲያንና ተዋናይ ዳሪል ሊን ሃግሊይ በቴኒሲ ግዛት ናሽቪል ውስጥ አርብ ዕለት ትርኢት እያሳየ በድንገት ከወደቀ በኋላ በተደረገለት ምርመራ የኮሮናቫይረስ ተገኘበት።
የ57 ዓመቱ ሃግሊይ የኮሜዲ ሥራውን እያቀረበ በነበረበት ጊዜ “እራሱን ስቶ” መውደቁን በኋላ ላይ ተናግሯል። ከዚያም በኋላ ወደ ሆስፒታል ተወስዶ በተደረገለት ምርመራ ከፍተኛ ድካምና በሰውነቱ ውስጥ የፈሳሽ እጥረት እንዳለ ተገልጾ ህክምና አግኝቶ ቅዳሜ ወደ ቤቱ ተመልሷል።
ኮሜዲያኑ ጨምሮም ሆስፒታሉ ውስጥ የተለያዩ ምርመራዎች እንደተደረጉለት ገልጾ “የኮሮናቫይረስም እንደተገኘብኝ ሲነገረኝ በጣም ነበር ያስደነገጠኝ” ብሏል።
"ሐኪሞቹ እንዳሉት እኔ ምልክት ከማያሳዩት ህሙማን መካከል ነኝ” ሲል በትዊተር ገጹ ላይ ባስቀመጠው የቪዲዮ መልዕክት ተናግሯል።
ባለሙያዎች እንደሚሉት እንዲህ አይነቶቹ ህሙማን የበሽታውን ምልክቶች ሳያሳዩ ለብዙ ጊዜ መቆየት ይችላሉ።
ሃግሊይ ቫይረሱ እንደተገኘ ካወቀ በኋላ ለ14 ቀናት ራሱን ለይቶ በሆቴል ክፍሉ ወስጥ እንደሚቆይ ገልጾ በቶሎ እንዲሻለው የተመኙለትን አድናቂዎቹን አመስግኗል።
የአውስትራሊያዋ ግዛት ጥላው የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አራዘመች
የአውስትራሊያዋ ግዛት ቪክቶሪያ ከአንድ ወር በላይ በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ቁጥር በመጨመሩ ምክንያት ጥላው የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለተጨማሪ አንድ ወር ባለበት እንዲቆይ አራዘመች።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘም የግዛቲቱ ባለስልጣናት የኅብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ አስፈላጊ ነው ያሉትን እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ስልጣን ይሰጣቸዋል።
በአውስትራሊያ ደቡብ ምሥራቅ የምትገኘው የቪክቶሪያ ግዛት በቅርብ ቀናት ውስጥ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ አዳዲስ የኮሮናቫይረስ ህሙማን ማግኘታቸውን አሳውቀዋል።
የግዛቲቱ አስተዳዳሪ እንዳሉት የአዳዲስ ህሙማኑ ቁጥር እንዲጨምር ምክንያት የሆነው በቤተሰብ ውስጥ በሚከሰት የበሽታው መዛመት ምክንያት እንደሆነ ጠቅሰዋል።
በዚህም ሳቢያ ግዛቲቱ ቅዳሜ ዕለት እንዳስታወቀችው ቀደም ሲል ጥላቸው ከነበሩት ገደቦች መካከል የተወሰኑትን ለማንሳት ይዛው የነበረውን ዕቅድ አዘግይታዋለች።
በተጨማሪም በቤት ውስጥ የሚደረግ መሰባሰብን የተመለከተውን ጨምሮ አካላዊ ርቀትን ከመጠበቅ አንጻር አስፈላጊ ነው የተባሉ እርምጃዎች ተመልሰው ተግባራዊ ይሆናሉ ተብሏል።
በሕንድ በአንድ ቀን ከ15 ሺህ በላይ የኮሮናቫይረስ ህሙማን ተገኙ
ሕንድ በአንድ ቀን ውስጥ 15 ሺህ 413 በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎችን ማግኘቷን በምርመራ አረጋገጠች።
ይህም በአገሪቱ ወረርሽኙ መገኘቱ ከታወቀ ወዲህ በአንድ ቀን የተገኘው ከፍተኛው የህሙማን ቁጥር ነው።
በዛሬው ዕለት የተገኘው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ከፍተኛ ቁጥር እስካሁን በሕንድ ያለውን አጠቃላይ የህሙማን ብዛት ወደ 410 ሺህ 461 ያደረሰው ሲሆን ይህም ከአሜሪካ፣ ከብራዚልና ከሩሲያ ቀጥሎ ሕንድን በዓለም አራተኛ ደረጃ ላይ እንድትቀመጥ አድርጓታል።
ከዚህ በተጨማሪ በበሽታው ምክንያት 306 መሞታቸው በዛሬው ዕለት የተነገረ ሲሆን በአጠቃላይ በአገሪቱ የሞቱትን ሰዎች ብዛት ወደ 13 ሺህ 254 አድርሶታል።
እየተባለ እንዳለው ሕንድ ውስጥ የሚፈለገውን ያህል ምርመራ እየተደረገ ስላልሆነ በወረርሽኙ የተያዙና በበሽታው የሚሞቱ ሰዎች ትክክለኛ ቁጥር ከዚህም በታም ከፍ ያለ ሊሆን እንደሚችል ይታሰባል።
በአገሪቱ የተገኙት ህሙማን በአብዛኛው የሚገኙት በዋና ከተማዋ ዴልሂ እንዲሁም ማሐራሽትራና ታሚል ናዱ በተባሉት ግዛቶች ውስጥ ሲሆን፤ ይህም ከአጠቃላዩ በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 60 በመቶ የሚጠጋውን ይሸፍናል።
ስፔን ከወራት በኋላ በሯን ለቱሪስቶች ከፈተች
ስፔን ከአውሮፓና የሽንገን ቪዛ ተጠቃሚ ከሆኑ አገራትና ከዩናይትድ ኪንግደም በሚመጡ ጎብኚዎች ላይ ጥላው የነበረውን ዕገዳ በማንሳት ለቱሪስቶች በሯን ከፈተች።
በዚህም ሁሉም ወደ ስፔን የሚገቡ መንገደኞች በአየር ማረፊያ ውስጥ ሙቀታቸው የሚለካ ሲሆን በተጨማሪም ቀደም ብሎ በቫይረሱ ተይዘው እንደነበርና የሚቆዩበት አድራሻቸውን እንዲሰጡ ይጠየቃሉ።
ስፔን ይህንን እርምጃ የወሰደችው ለሦስት ወራት በአገሪቱ የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማብቃቱን ተከትሎ ነው። በዚህም በመላው ስፔን ውስጥ መንቀሳቀስ የተፈቀደ ሲሆን አካላዊ ርቀትን ለመጠበቅ በማይቻልባቸው ሕዝብ በሚበዛባቸው ስፍራዎች የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል መጠቀም ግዴታ ነው።
በአውሮፓ ውስጥ በወረርሽኙ ክፉኛ ከተጠቁት አገሮች አንዷ የሆነችው ስፔን የእንቅስቃሴ ገደቡን የጣለችው በመጋቢት ወር አጋማሽ ላይ ነበር።
በአገሪቱ ከ245 ሺህ ሰዎች በላይ በበሽታው መያዛቸው የተመዘገበ ሲሆን 28 ሺህ ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ሰበብ ህይወታቸውን አጥተዋል። ይህም ስፔንን በበሽታው በርካታ ሰዎችን ካጡ አገራት መካከል ያስመድባታል።
በደህናው ጊዜ ስፔንን በዓመት 80 ሚሊዮን ቱሪስቶች የሚጎበኟት ሲሆን ከዘርፉ የምታገኘው ገቢም ከአገሪቱ አጠቃላይ ዓመታዊ ምርት ከ12 በመቶ በላዩን የሚሸፍን ነው።
ትራምፕ የኮሮናቫይረስ ምርመራዎችን እንዲቀንሱ ለባለስልጣናት መልዕክት አስተላለፉ
በቱልሳ፣ ኦክላሃማ በተካሄደው የዳግም ምረጡኝ ቅስቀሳ ፕሬዚዳንት ትራምፕ የኮሮናቫይረስ ምርመራን አስመልክቶ አወዛጋቢ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በተለያዩ ግዛቶች የሚገኙ ባለስልጣናት ምርመራዎችን ከማካሄድ ገታ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። ብዙ ምርመራ በተደረገ ቁጥር በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችም ቁጥር እየጨመረ መሆኑን የገለፁት ፕሬዚዳንቱ "ምርመራ ማለት በሁለት በኩል ስለት ያለው ቢላ ማለት ነው። መጥፎው ነገር ይህ ነው። ብዙ ሰዎች ሲመረመሩ በቫይረሱ የተያዙ ብዙዎችን ታገኛላችሁ። ምርመራውን ገታ አድርጉ በተደጋጋሚ ብልም አሁንም በፍጥነት በመመርመር ላይ ናቸው" ብለዋል።
ተጨማሪ ያንብቡኢትዮጵያ እስካሁን በ211 ሺህ 871 ናሙናዎቸ ላይ የኮቪድ-19 ምርመራ አደረገች
የኮሮናቫይረስ የማኅበረሰብ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ እየገሰገሰ ባለባት ኢትዮጵያ በትናንትናው ዕለት ከፍተኛ የተባለው 399 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።
በአገሪቱም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 4469 አድርሶታል፤ ከእነዚህም ውስጥ 1122 አገግመዋል። በትናንትናው ዕለት ሞት ባይመዘገብም አገሪቱ በቫይረሱ ያጣቻቸው ሰዎች ቁጥር 72 ደርሷል፤ በፀና የታመሙ ሰዎች ቁጥርም 30 ነው።
ኢትዮጵያ ኦክስጂን ወይም የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያ እገዛ ለሚያስፈልጋቸው በጠና ለታመሙ የኮሮናቫይረስ ህሙማን ዴክሳሜታዞንን ለመጠቀም መወሰኗን ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
በአገሪቱ ወረርሽኙ መገኘቱ ከተወቀበት በኋላ እስካሁን የተከናወኑ የኮቪድ-19 የላብራቶሪ ምርመራዎችም 211 ሺህ 871 ደርሷል።
በኢትዮጵያ ዴክሳሜታዞን ጥቅም ላይ እንዲውል ተወሰነ
በቅርቡ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ጽኑ ታመው ለሚገኙ ሰዎች ተሰጥቶ ውጤት ማሳየቱ የተገለጸው ዴክሳሜታዞን የተባለው መድኃኒት በኢትዮጵያ ውስጥ ጥቅም ላይ እንዲውል ተወሰነ። የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ፌስቡካቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት እንዳስታወቁት በዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት በዴክሳሜታዞን የተባለውን መድኃኒት ለኮቪድ-19 ህሙማን ለመጠቀም የተደረገውን ጥናትና ሪፖርቱን በዝርዝር መሥሪያ ቤታቸው እንደተመለከተው ገልጸዋል።
ተጨማሪ ያንብቡየእሁድ ሰኔ 14/2012 ዓ.ም የቢቢሲ አማርኛ የቀጥታ ዘገባ ገጽ
እንደምን አደራችሁ!
ዕለተ እሁድ ሰኔ 14/2012 ዓ.ም
ይህ ቢቢሲ አማርኛ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ላይ አተኩሮ ትኩስ ዜናና መረጃን የሚያቀርብበት የቀጥታ ዘገባ ገጽ ነው።
ባገኛችሁት አጋጣሚ ሁሉ ይህንን ገጽ እንድትጎበኙ እንጋብዛለን።
መልካም ዕለት!
በኮሮናቫይረስ የተያዙ ተጨማሪ 399 ሰዎች ተገኙ
ባለፉት 24 ሰዓታት ለ4848 ሰዎች በተደረገው የላብራቶሪ ምርመራ 399 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የጤና ጥበቃ እና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባወጡት ዕለታዊ መግለጫ ላይ ተገልጿል።
ይህም በአገሪቱ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 4469 ከፍ አድርጎታል።
በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎች ከ4 እስከ 85 የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው ተብሏል።
በሌላ በኩል ባለፉት 24 ሰዓታት ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ህይወታቸው ያለፈ የለም። 95 ሰዎች ደግሞ ማገገማቸው ተገልጿል።
ከባድ የጤና ችግር ኖሮባቸው ከኮቪድ-19 ያገገሙ ሰዎች ታሪክ
ሌሎች አሳሳቢ የጤና እክል ያለባቸው ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዝ በጣም አስፈሪ ነገር ሊሆንባቸው ይችላል። ምናልባትም ብዙዎች ስለዚህ ጉዳይ ሲያስቡ በጣም ሊጨነቁ ይችላሉ። ነገር ግን አስጊ የሚባል የጤና ሁኔታ ላይ ሆነው እንኳን ከቫይረስ እያገገሙ ያሉ ሰዎች አሉ። ብርዮኒ ሆፕኪንስም በከባድ የጤና ችግር ውስጥ ሆነው ቫይረሱን ማሸነፍ ከቻሉት መካከል አንዷ ስትሆን ታሪኳን እንዲህ ትናገራለች።
ተጨማሪ ያንብቡየዚምባብዌ ጤና ሚንስትር ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ በሙስና ክስ ፍርድ ቤት ሊቀርቡ ነው
የዚምባብዌ ጤና ሚንስትር ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ የሙስና ክስ ተመስርቶባቸው ዛሬ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ።
ሚንስትሩ የኮሮናቫይረስ መመርመሪያ መሣሪያ እና ከሌሎች የህክምና እቃዎች ግዢ ጋር በተያያዘ ነው የሙስና ክሱ የተመሰረተባቸው።
ኦባዲሃ ሞዮ አርብ ዕለት በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን፤ መንግሥት ከማህበራዊ ሚዲያዎች ተጠቃሚዎች እና ከተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ትችት እየደረሰበት ነው።
የ20 ሚሊዮን ዶላር እቃ ግዢ ሕጋዊ የሆነ የግዢ ስርዓትን ባልተከተለ መልኩ በሃንጋሪ አገር የተመዘገበ ድርጅት እቃዎቹን እንዲያቀርብ ውል ተሰጥቷል።
መንግሥት ከኩባንያው ጋር የተያዘውን ውል አፍርሷል።
በኤሜርሰን ምናንጋግዋ ካቢኔ አላባት ላይ የሙስና ክስ ሲመሰረት ይህ ሚንስትር ሁለተኛው ሰው ናቸው።
ዚምባብዌ እስካሁን 500 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ነው ያገኘሁት ብትልም በርካቶች ግን ቁጥሩ ከዛ ከፍ ያለ መሆኑ ይከራከራሉ።
ዩኬ ገቢ መንገደኞችን በክፍያ ልትመርመር አቅዳለች
ወደ ዩናይትድ ኪንግደም የሚገቡ መንገደኞች በአየር ማረፊያዎች በክፍያ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ለማድረግ ከተስማሙ ወደ አስገዳጅ ለይቶ ማቆያ መግባት ግድ ላይሆንባቸው ይችላል ተብሏል።
ለምርመራው ግን መንገደኞች 140 ፓውንድ ወይም 170 ዶላር መክፈል ይጠበቅባቸዋል።
በቅርቡ ተፈጻሚ እንደሚሆን በተጠበቀው አማራጭ፤ መንገደኞች የምርመራ ውጤታቸውን በ24 ሰዓታት ውስጥ ይቀበላሉ። የምርመራ ውጤቱ እስኪታወቅ ድረስ በለይቶ ማቆያ መቆየት ግዴት ነው።
ይህን እቅድ ያስፈጽማል የተባለው ስዊዝፖርት ዩኬ፤ ሰዎች ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው ከተረጋገጠ ለ13 ቀናት ወደ አስገዳጅ ለይቶ ማቆያ መግባት አይጠበቅባቸም ብሏል።
ይህ በአየር ማረፊያዎች ላይ ለገቢ መንገደኞች የኮሮናቫይረስ ምርመራ ማድረግ በሆንግ ኮንግ አየር ማረፊያዎች ላይ እየተተገበረ ይገኛል።
የዩኬ መንግሥት ገቢ መንገደኞች ወደ አስገዳጅ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ መወሰኑ ወደ አገሪቱ የሚደረጉ የበረራ ፍላጎቶች እንዲቀንስ ማድረጉ ተነግሯል።
ይህንን የመንግሥት ውሳኔ በርካታ የዩኬ አየር መንገዶች ተቃውመውታል።
የዩኬ መንግሥት ግን በአገሪቱ ኮሮናቫይረስ ለሁለተኛ ጊዜ እንዳይሰራጭ ከምወሰዳቸው ጥብቅ እርምጃዎች መካከል ገቢ መንገደኞች ወደ ለይቶ ማስገባት አንዱ ነው ብሏል።
ቫይረሱ ዳግም በመሰራጨቱ የአውስትራሊያዋ ግዛት በድጋሚ እንቅስቃሴ ላይ ገደብ ጣለች
በአውስትራሊያ ቪክቶሪያ ግዛት የኮሮናቫይረስ ስርጭት መጨመሩን ተከትሎ የግዛቷ አስተዳዳሪዎች የእንቅስቃሴ ገደቡ የሚላላበትን ጊዜ አራዝመዋል።
ቅዳሜ ዕለት 25 ተጨማሪ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸውን ተከትሎ ነው ግዛቷ ዳግም የእንቅስቃሴ ገደብ ያወጀችው።
የግዛቷ አስተዳዳሪ የሆኑት ዳንኤል አንድሩስ እንዳሉት ማህበራዊ ርቀት ላይ ተጥለው የነበሩት ገደቦች ሳይነሱ እስከ ሐምሌ መጀመሪያ ድረስ ይቆያሉ።
እስከ ሐምሌ 5 ድረስ በአንድ ቤት ውስጥ ከአምስት ሰዎች በላይ መሰባሰብ አይችሉም ብለዋል።
አስተዳዳሪው እንደሚሉት በቪክቶሪያ ግዛት ከግማሽ በላይ በቫይረሱ የተያዙት ሰዎች በቤተሰብ መካከል ቫይረሱ ተሰራጭቶ ነው።
አስፈላጊ ከሆነ ባለስልጣናት ''ቤት ለቤት'' እየተዟዟሩ የተጣሉ ገደቦች ተፈጻሚ መሆናቸውን ያረጋግጣሉ ብለዋል።
ኤርባስ በዩኬ እና ስፔን የሚገኙ ሰራተኞቹ ከሥራ ውጪ ሆነው ይቆያሉ አለ
አውሮፕላን አምራቹ ኤርባስ ትናንት እንዳለው በስፔን እና ዩናይትድ ኪንግደም የሚገኙ 5300 ሰራተኞቹን ከሥራ ውጪ ሆነው ለተጨማሪ ወራት ይቆያሉ።
ድርጅቱ ከዚህ ውሳኔ የደረሰው በኮሮናቫይረስ ምክንያት ከደረሰበት የገቢ ቀውስ ለማገገም ነው ብሏል።
እስከ መስከረም 30 ድረስ 3ሺህ 100 በስፔን የሚገኙ ሁሉም የኤርባስ ሰራተኞች ከሥራ ውጪ ሆነው እንደሚቆዩ የድርጅቱ ቃል አቀባይ ለሬውተርስ አሳውቀዋል።
በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኙ 2ሺህ 200 ሠራተኞች ደግሞ እስከ ሰኔ አጋማሽ ድረስ ከሥራ ውጪ ሆነው ይቆያሉ።
አውሮፕላን አምራቹ ኩባንያ ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኋላ የሚቀዛቀዘውን ገበያውን ከግምት በማስገባት በርካታ ሠራተኞቹን ሊያሰናብት የሚችል አዲስ መዋቅር እንደሚያስተዋውቅ ተናግሯል።
ከዚህ በተጨማሪም ኩባንያው የከፍተኛ ሥራ አስፈጻሚዎቹን ቁጥር ለመቀነስ ስለማቀዱም ተነግሯል።
የሟቾች ቁጥር 20ሺህ መድረሱን ተከትሎ ሜክሲኮ ሲቲ በሬን አልከፍትም አለች
በሜክሲኮ በቫይረሱ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች መጨመሩን ተከትሎ፤ መዲናዋ ሜክሲኮ ሲቲ የንግድ ተቋማት የሚከፈቱበትን ጊዜ አራዘመች።
የሜክሲኮ ሲቲ ከንቲባ የኮሮናቫይረስ ስርጭት እስኪቀንስ ድረስ የንግድ ቤቶች ተዘግተው ይቆያሉ ብለዋል።
በሜክሲኮ በአጠቃላይ በአገር ደረጃ የቫይረሱ ስርጭት እየጨመረ ይገኛል።
ሜክሲኮ ሲቲ ሆቴሎችን፣ ምግብ ቤቶች እና የገብያ ማዕከላትን ለመክፈት አቅዳ ነበር።
የከተማዋ ከንቲባ ክላወዲአ ሼኢንባኡም ከተማችን በከፍተኛ ተጠንቀቅ ላይ ሆና እስከሚቀጥለው ሳምንት እንቅስቃሴ አልባ ሆና ትቆያለች ብለዋል።
ትናንት በመዲናዋ የሚገኙ የሆስፒታል አልጋዎች 65 በመቶ ተይዘው ነበር።
የሟቾች ቁጥር 20ሺህ በተሻገረባት ሜክሲኮ፤ የቫይረሱ ስርጭት ገና ከጫፍ አለመድረሱን ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ሜክሲኮ እስካሁን 170ሺህ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ይገኙባታል። መዲናዋም በቫይረሱ ሰርጭት ክፉኛ ከተጎዱ አካበቢዎች መካከል ዋነኛዋ ናት።