ኮሮናቫይረስ፡ በብራዚል የሟቾች ቁጥር ከ50ሺህ ዘለለ

ብራዚል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በኮሮና ቫይረስ የሟቾች ቁጥር በላቲን አሜሪካዋ ትልቅ ሕዝብ ባላት አገር ብራዚል እየገሰገሰ ነው፡፡ ትናንት 50ሺ ማለፉ ይፋ ሆኗል፡፡

አገሪቱ በቫይረሱ የተያዙባት ሰዎች ቁጥር አንድ ሚሊዮን አልፏል፡፡

የማኅበረሰብ ጤና ባለሞያዎች እንደሚሉት ደግሞ በብራዚል በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር የወረርሽኝ ጣሪያውን እስኪነካ ገና ሳምንታት ይቀራሉ፡፡

ብዙዉን ጊዜ በወረርሽኝ ከፍተኛው የቁጥር ጣሪያ ከተመዘበ በኋላ የተያዦች ቁጥር እየቀነሰ የመምጣት ዝንባሌ ያሳያል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ትናንት በአንድ ቀን ብዙ ሰዎች በኮቪድ-19 የተያዙበት ዕለት ሆኖ መዝግቦታል፡፡

በአንድ ቀን መያዛቸው ከተመዘገቡ 183,000 የዓለም ሕዝቦች ውስጥ 60 ከመቶ የሚሆኑት ከሰሜን አሜሪካና ደቡብ አሜሪካ አገራት በተለይም ከአሜሪካና ብራዚል መሆናቸውን ድርጅቱ ይፋ አድርጓል፡፡

የሚገርመው ቫይረሱ በዚህ ፈጣን ግስጋሴው ውስጥ ሆኖም በብራዚል የአወዛጋቢው ፕሬዝዳንት ጃይ ቦልሴናሮ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች አደባባይ መውጣታቸው ነው፡፡

የጃይ ቦልሴናሮ ተቃዋሚዎች ፕሬዝዳንቱ በብራዚል ሕዝብ ላይ ባደረሱት የጤና ምስቅልቅል ፍርድ ቤት መከሰስ አለባቸው ሲሉ ድምጻቸውን ያሰሙ ሲሆን ደጋፊዎቻቸው ደግሞ የሕግ መምሪያው ምክር ቤት እና ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንታችንን ሊያሰሩት አልቻሉም፤ ሥልጣኑን እየገደቡ አስቸግረውታል ሲሉ ሰልፍ ወጥተዋል፡፡

ጃይ ቦልሴናሮ ዜጎች ወረርሽኙን ፈርተው ቤታቸው እንዳይቀመጡና ወጥተው መደበኛ ሥራቸው ላይ እንዲሰማሩ ሲቀሰቅሱ የአንዳንድ ከተማ ገዢዎች ግን ሐሳቡን በመቃወም የዜጎችን እንቅስቃሴ እየገደቡ ነው፡፡

ትናንትና እሑድ ብቻ በብራዚል የሞቱት 641 ሲሆኑ በዚያው ቀን ብቻ አዲስ የተያዙት 17ሺ ናቸው፡፡ ይህም በዚያች አገር በድምሩ የሞቱ ሰዎችን ቁጥር 50,617 አድርሶታል፡፡

በዓለም ላይ በቫይረሱ ምክንያት የሞቱ ቁጥርም ሆነ የተያዦች ቁጥር ብራዚልን የምትበልጥ አገር አሜሪካ ብቻ ናት፡፡

በዶናልድ ትራምፕ አገር አሜሪካ የተያዙት 2.2 ሚሊዮን ሲሆኑ የሞቱት ደግሞ 120,000 አልፈዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ጃይ ቦልሴናሮ እንደሚከራከሩት በብራዚል የእንቅስቃሴ ገደብ ቢደረግ ከቫይረሱ ይልቅ ምጣኔ ሀብታዊው ምስቅልቅል የብራዚልን ሕዝብ ይገድላል፡፡

በዚህም የተነሳ በብራዚል በብሔራዊ ደረጃ ቤት ውስጥ የመቀመጥ ግዴታ አልተጣለም፡፡

ሆኖም ክፍለ ግዛቶችና ከተሞች የራሳቸውን መመሪያ እያወጡ ነው፡፡

አንዳንድ ከተሞች የእንቅስቃሴ ገደብ ካደረጉ በኋላ ቀስ በቀስ በራቸውን መክፈት ይዘዋል፤ ምንም እንኳ የሟቾችና የተያዦች ቁጥር እያሻቀበ ቢሆንም፡፡

በሳውፖሎ እና ሪዮ ዴ ጀኔሮ ከተሞች አሁንም የተቃውሞና የድጋፍ ሰልፎች እንደቀጠሉ ናቸው፡፡

ኮሮና
Banner