ኮሮናቫይረስ፡ ከቫይረሱ ያገገሙ ሰዎች የመድኃኒት ፍንጭ ይሰጡ ይሆን?

ከቫይረሱ ያገገሙ ሰዎች የመድኃኒት ፍንጭ ይሰጡ ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዩናይትድ ኪንግደም ሳይንቲስቶች በኮሮናቫይረስ ምክንያት እጅግ የታመሙ ሰዎችን ይረዳል የተባለ መድኃኒት ላይ ጠለቅ ያለ ጥናት እያካሄዱ ነው።

በኮቪድ-19 ምክንያት ክፉኛ የታመሙ ሰዎች እጅግ ጥቂት በእንግሊዝኛው ቲ-ሴል ተብለው የሚጠሩ የሰውነት መከላከያዎች ነው ያሏቸው።

ቲ-ሴሎች በሽታ አምጪ ተሕዋስን ከሰውነት ማስወገድ ነው ስራቸው።

ሳይንቲስቶቹ የሚያጠኑት ኢንተርሉኪን የተሰኘው መድኃኒት ክፉኛ የታመሙ ሰዎችን ቲ-ሴል በማብዛት ቶሎ እንዲድኑ ያደርጋል የሚል እምነት ተጥሎበታል።

60 የኮቪድ-19 በሽተኞችን ያጠኑት ተመራማሪዎች ህሙማኑ የቲ-ሴል መጠናቸው እጅጉን የወረደ መሆኑን መመልከት ችለዋል።

ፕሮፌሰር አድሪያን ሄይደይ የክሪክ ኢኒስቲትዩት ተመራማሪ ናቸው። "በበሽተኞቹ ላይ ያስተዋልነው የመከላከል አቅም መዳከም በጣም የሚያስደንቅ ነው" ይላሉ።

"ሴሎቹ እኛን ለመከላከል እየተጣጣሩ ነው። ነገር ግን ቫይረሱ እጅግ አድርጎ እንደጎዳቸው ማየት ይቻላል። ቁጥራቸውም እየቀነሰ መጥቷል።"

በአንድ ጤናማ ሰው ሰውነት ውስጥ በማይክሮሊትር [0.01 ሚሊ ሊትር] ደም ውስጥ ከ2 ሺህ እስከ 4 ሺህ ቲ-ሴሎች ይኖራሉ።

ነገር ግን በጥናቱ ላይ እየተሳተፉ ያሉት በኮቪድ-19 ክፉኛ የተጠቁት ህሙማን ያላቸው የቲ-ሴል መጠን ከ200 እስከ 1200 ነው።

በጣም አበረታች

አጥኚዎቹ የደረሱባቸው ግኝቶችን መሠረት አድርገው በጣት አሻራ ብቻ በሰዎች ደም ውስጥ ያለውን የቲ-ሴል መጠን መለየት እንዲችሉ እንደሚረዳቸው ይናገራሉ። ይህ ደግሞ በበሽታው ክፉኛ ሊጎዱ የሚችሉ ሰዎችን አስቀድሞ ለማወቅ ይረዳል ይላሉ።

ሐኪሞች ይህን አወቁ ማለት ደግሞ በሽተኞችን አስቀድመው እንዲንከባከቧቸው ይረዳል።

ማኑ ሻንካር-ሃሪ በጋይስ ኤንድ ሴይንት ቶማስ ሆስፒታል ባለሙያ ናቸው። በኮቪድ-19 ምክንያት ወደ ፅኑ ሕሙማን ክፍል ከገቡ በሽተኞች መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት ከ400-800 ቲ-ሴሎች ነበሯቸው ይላሉ። ነገር ግን በሽተኞቹ ማገገም ሲጀምሩ የቲ-ሴል መጠናቸውም መጨመር ይጀምራል።

ኢንተርሉኪን 7 የተሰኘው መድኃኒት ሴፕሲስ ባለባቸው ሰዎች ላይ ተሞክሮ ውጤታማ ሆኗል። መድኃኒቱ የቲ-ሴል መጠንን በመጨመር ረገድም አዎንታዊ ለውጥ አሳይቷል።

መርማሪዎቹ በኮቪድ-19 ምክንያት ከሦስት ቀናት በላይ በፅኑ የታመሙ ሰዎችን መርጠው የመድኃኒት ሙከራ ያደርጉባቸዋል።

ሻንካር፤ መድኃኒቱ የቲ-ሴሎችን አቅም በመጨመር ቫይረሱን ያጠፋዋል የሚል እምነት አለን ይላሉ።

ጥናቱ ቫይረሱ እንዴት አድርጎ የመከላከል አቅምን እንደሚጎዳ ለመለየት ይረዳልም እየተባለ ነው። ይህ ደግሞ በዓለም ዙሪያ ላሉ ተመራማሪዎች ጠቃሚ የሆነ መረጃ ይሰጣል ይላሉ ፕሮፌሰር ሄይደይ።

ኮሮና