Got a TV Licence?

You need one to watch live TV on any channel or device, and BBC programmes on iPlayer. It’s the law.

Find out more
I don’t have a TV Licence.

ቀጥታ ዘገባ

የተጠቀሱት ሰዓቶቸ የዩናይትድ ኪንግደም ናቸዉ

  1. ሕንድ ከ2 ሚሊየን በላይ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙባት ሦስተኛዋ አገር ሆነች

    የበሽታውን መከላከያ የለበሰ ግለሰብ

    በሕንድ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ2 ሚለየን መሻገሩ ተገለፀ።

    በአገሪቷ ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ 58 ሺህ 168 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን፤ ይህም አጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር 2 ሚሊየን 21 ሺህ 407 አድርሶታል።

    በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም በ20 ቀናት ውስጥ እጥፍ የሆነ ሲሆን ከፍተኛ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በተመዘገበባቸው በአሜሪካ ወይም ብራዚል ከታየው የቫይረሱ ሥርጭት እጅግ የፈጠነ ነው ተብሏል።

    በአገሪቷ ከ40 ሺህ በላይ በቫይረሱ ሳቢያ ሕይወታቸው ማለፉም ተገልጿል።

    ይህም በኣለማችን ካሉ አገራት በ5ኛ ደረጃ ላይ እንድትቀመጥ አድርጓታል።

    ሕንድ 1.3 ቢሊየን የሕዝብ ብዛት ያላት አገር ናት።

  2. በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ወደ 21 ሺህ ተጠጋ

    ግራፊክስ

    በዛሬው ዕለት ለ9 ሺህ 68 ሰዎች የላብራቶሪ ምርመራ ተከናውኖ 564 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል። በዚህም መሰረት በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 20 ሺህ 900 መድረሱን የጤና ሚኒስትርና የህብረተሰብ ጤና ተቋም እለታዊ መግለጫ አመላክቷል።

    በዛሬው ዕለት ዘጠኝ ሰዎችም ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን አገሪቱ በቫይረሱ ያጣቻው ዜጎችን 365 አድርሶታል።

    መግለጫው ተጨማሪ 429 ሰዎች ማገገማቸውን የጠቆመ ሲሆን በአጠቃላይ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎችም 9 ሺህ 27 ነው።

    አገሪቷ እስካሁን ድረስ 468 ሺህ 814 የላብራቶሪ ምርመራዎችን አከናውናለች።

  3. "ክርስቲያኖች የኮሮናቫይረስ በሽታ አይዛቸውም" ያሉት ካናዳዊ ፓስተር በማይናማር ታሰሩ

    ካናዳዊው ፓስተር

    "ክርስቲያኖች በሙሉ የኮሮናቫይረስ በሽታ አይዛቸውም" ብለው የሰበኩት ካናዳዊ ፓስተር በማይናማር ለእስር ተዳረጉ። ፓስተሩ ከሦስት ወር እስራት በተጨማሪ በእስርም ከባድ ሥራ እንዲሰሩ ተወስኖባቸዋል።

    ዴቪድ ሊህ የተባሉት ካናዳዊው ፓስተር ያንጎን በተባለው ስፍራ ከፍተኛ ህዝብ ሰብስበው በመስበካቸውም ማይናማር የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመግታት ያወጣችውን መመሪያ ጥሰዋልም ተብለዋል። ጉባኤውን ያደረጉት ሚያዝያ ወር ላይ ነበር።

    ከጉባኤው በኋላም እሳቸውን ጨምሮ 20 ተሳታፊዎች በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሲሆን በማይናማር ላለው የበሽታው ስርጭትም ይህ ጉባኤ ዋነኛ መንስኤ ነው ተብሏል።

    ጉባኤውን ከማካሄዳቸው በተጨማሪ ሃሰተኛ ነገር በመስበካቸውም ብዙዎችን አስቆጥቷል።

    "ልባችሁ ውስጥ ክርስቶስ ካለ በሽታው አይዛችሁም" በማለትም በጉባኤው ላይ ተናግረዋል።

    የ43 አመቱ ሰባኪ ትውልዳቸው ማይናማር ሲሆን በዜግነታቸውም ካናዳዊ ናቸው።

    በማይናማር በአሁኑ ወቅት 357 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን ስድስት ሰዎችም እንደሞቱ ከጆንስ ሆፕኪንስ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

  4. ጀርመን በኮቪድ ከተጠቁ አገራት የሚገቡ መንገደኞችን ምርመራ አስገዳጅ አደረገች

    ምርመራ ሲደረግ

    ጀርመን የቫይረሱ ሥርጭት ከፍተኛ ከሆነባቸው አገራት ወደ አገሪቷ የሚገቡ መንገደኞችን ምርመራ አስገዳጅ አደረገች። ምርመራው የሚደረግላቸው ተመርምረው ከሁለት ቀናት ያልበለጠ ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸውን የሚያሳይ ውጤት ለሌላቸው እንደሆነ የአገሪቷ የጤና ሚኒስተር አስታውቀዋል።

    ምርመራው የሚደረገው በነፃ ሲሆን ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ፈቃደኛ የሆኑ መንገደኞች ምርመራ ሲደረግላቸው ነበር።

    አሁን ላይ ግን ይህ በፈቃድ ላይ የተመሰረተ ምርመራ አስገዳጅ ሆኗል ተብሏል።

    ውሳኔው የተላለፈው በአገሪቷ ባለፉት ሦስት ወራት ውስጥ ያልተመዘገበ 1 ሺህ 45 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጠ በኋላ ነው።

    ሕጉ ከአውሮፓ ህብረት አገራት ውጭ ያሉ አገራትን እንዲሁም ከስፔንና ሉክዘምበርግ የሚገቡ መንገደኞችን የሚመለከት ሲሆን ዩናይትድ ኪንግደምን ግን አይጨምርም ተብሏል።

    "ሕጉ የግለሰቦችን መብት የሚጥስ ቢሆንም ምክንያታዊ ነው" ሲሉ የጤና ሚኒስትሩ ጀንስ ስፓን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

  5. በሃዘን ያለችው ሊባኖስ ወረርሽኙ ስጋት ሆኖባታል

    በፍንዳታው አደጋ የደረሰበት ሆስፒታል

    በሊባኖስ መዲና ቤይሩት ባጋጠመው ፍንዳታ 137 ዜጎቿን ተነጥቃለች፤ ከአምስት ሺህ በላይ ሰዎችም ቆስለዋል።

    ሊባኖስ የዜጎቿን በድንገተኛ ፍንዳታ ህይወት ማለፍን እያዘነችበት ባለበት ወቅት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝም ሌላ ስጋት ሆኖባታል።

    በትናንትናው ዕለት አገሪቷ በአንድ ቀን መዝግባው የማታውቀውን በበሽታው የተያዙ ሰዎችንም አግኝታለች።

    ከጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በትናንትናው ዕለት 335 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል።

    በአጠቃላይ በአገሪቷ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 5 ሺህ 417 ሲሆን 68 ዜጎቿንም አጥታለች።

    የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እንደ በርካታ አገራት የሊባኖስንም የጤና ስርአት አቃውሶታል። በተለይም ከአገሪቷ የኢኮኖሚ መሽመድመድ ጋር ተያይዞ ወረርሽኙ ሌላ አጣብቂኝ ውስጥ ይከታታልም እየተባለ ነው።

  6. ቤተሰቦች ሆስፒታል ውስጥ ተቃቅፈው ሃዘናቸውን ሲገልፁ

    አንድ የሆስፒታሉ ባልደረባ የበሽታ መከላከያ መሳሪያ በኤሌክትሪክ ችግር ሳቢያ በእሳት ከተያያዘ በኋላ እሳቱ መዛመቱ ተነግሯል።።

    ተጨማሪ ያንብቡ
    next
  7. የአፍሪካ በሽታ መቆጣጠር በታንዛንያ ያለው የቫይረሱ ስርጭት ሁኔታ አሳስቦታል

    ከዚህ ቀደም ጆን ማጉፉሊ ታንዛንያውያን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ እንዳያደርጉ ተናግረው ነበር

    የአፍሪካ በሽታ መቆጣጠር ማዕከል ዳይሬክተር ታንዛንያ ኮሮናቫይረስን የያዘችበት መንገድ ላይ ያላቸውን ስጋት ገለፁ።

    ዶ/ር ጆን ንኬንጋሶንግ ከቢቢሲ ኒውስዴይ ጋር በነበራቸው ቆይታ በታንዛንያ ያለውን የቫይረሱ ስርጭትን ለመናገር የሚያስችል በቂ መረጃ እንደሌለ ገልፀዋል።

    ኃላፊው አክለውም ማዕከሉ አህጉሪቱ በጥምረት ለኮሮናቫይረስ መከላከል ምላሽ መስጠት የሚያስችላትን ስልት መቅረጻቸውን ተናግረዋል።

    " ታንዛንያ በአገሯ ያለውን የቫይረሱ ስርጭት መጠንን ይፋ እንደምታደርግና፤ ከአህጉሪቱ ቫይረሱን ጠራርጎ ለማውጣት በትብብር እንሰራለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን" ያሉት ኃላፊው አክለውም፣ አፍሪካውያን የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከልም ሆነ ለማስቆም በትብብር መስራት እንደሚያስፈልጋቸው አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

    " ከታንዛንያ ምላሽ ለማግኘት በተደጋጋሚ ሙከራ አድርገናል፤ ነገር ግን የምንጠብቀውን ምላሽ እያገኘን አይደለም" ብለዋል።

    የታንዛንያ ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊ አገራቸውን ፈጣሪ ከቫይረሱ "መታደጉን" በመግለጽ ነፃ መሆኗን ማወጃቸው ይታወሳል።

    ታንዛንያ በመጪው ጥቅምት ምርጫ ለማካሄድ እየተዘጋጀች ሲሆን ዜጎቿም አካላዊ ርቀታቸውን ሳይጠብቁ እንዲሁም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ የዕለት ተዕለት ህይወታቸውን መቀጠላቸው እየተገለፀ ነው።

  8. ኮሮና

    ከቻይናዋ ሁቤይ ግዛት ተነስቶ ሰው ከማይኖርበት አንታርክቲክ ውጪ ሁሉንም የዓለማችንን አህጉራትን ያዳረሰው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በአሁኑ ወቅት የምድራችን ዋነኛ የጤና ስጋት ሆኗል። ኮቪድ-19 በመባል የሚታወቀው ይህ ወረርሽኝ የመተንፈሻ አካልን የሚያጠቃ ሲሆን፤ መጀመሪያ ትኩሳት ቀጥሎም ደረቅ ሳል ከሳምንት በኋላ ደግሞ የትንፋሽ ማጠርን ያስከትላል። እስካሁን በቫይረሱ ከ18 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የተያዙ ሲሆን ከ690 ሺህ በላይ የሚሆኑ ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል። እስካሁን ባለው ሁኔታ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የሚያስችል ክትባትም ሆነ መድኃኒት አልተገኘም።

    ተጨማሪ ያንብቡ
    next
  9. ቦትስዋና የአልኮል ሽያጭ ላይ እገዳ ጣለች

    ቦትስዋና

    የቦትስዋና መንግሥት በየትኛውም የሃገሪቱ ክፍል የአልኮል ሽያጭ እንዲቆም አዟል።

    መንግሥት አልኮል መሸጫ ሱቆች የሥራ ፈቃዳቸው ለጊዜው ከጥቅም ውጭ እንዲሆን ትዕዛዝ አስተላልፏል።

    በጋዜጣ የታወጀው አዋጅ እንደሚጠቁመው መንግሥት እገዳውን እስካላነሳ ድረስ አልኮል መሸጥ ፈፅሞ የተከለከለ ነው። አልኮል መሸጫ ሱቆችም ተዘግተው ይቆያሉ።

    ለእገዳው እንደምክንያት የተቀመጠው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ነው። አልኮል መጠቀም ሰዎች የኮሮናቫይረስ ሕግጋት እንዳይጠብቁ ያደርጋል ይላል የቦትስዋና መንግሥት።

    ባለፈው ሳምንት ቦትስዋና በዋና ከተማዋ ጋቦሮን የእንቅስቃሴ ገደብ እንደ አዲስ መጣሏ አይዘነጋም። ገደቡ ለሁለት ሳምንታት ይቆያል።

    ቦትስዋና እስከዛሬ ድረስ 804 ሰዎች በቫይረሱ እንደተያዙባት ይፋ ስታደርግ 2 ሰዎች ሞተውባታል።

  10. ሕንድ ውስጥ የኮሮናቫይረስ በሽተኞች ሆስፒታል የእሣት አደጋ ደረሰበት

    ሕንድ

    ሕንድ ውስጥ ለኮሮናቫይረስ ታካሚዎች በተዘጋጀ አንድ ሆስፒታል ውስጥ በደረሰ የእሣት አደጋ ቢያንስ ስምንት ሰዎች መሞታቸውን ባለሥልጣናት አሳውቀዋል።

    በምዕራባዊ ሕንድ፤ አህመዳባብ በተሰኘች ግዛት የተከሰተው የእሣት አደጋ በሃገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ለሊት 9 ሰዓት እንደተነሳ ታውቋል።

    የእሣት አደጋ ባለሥልጣኑ ራጄሽ ባት ለቢቢሲ እንደተናገሩት አደጋው የተከሰተው የኤሌክትሪክ ገመድ የፈጠረው እሣት ከሕክምና ልብስ ጋር በመያያዙ ምክንያት ነው።

    ፖሊስ የሆስፒታሉን ዳይሬክተር በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያከናወኑ መሆኑን አሳውቋል።

    ሕንድ በኮሮናቫይረስ ከ1.9 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የተያዙባት ሲሆን 40 ሺህ ገደማ ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

  11. ጋምቢያ የኮሮናቫይረስ ስርጭቱ እየጨመረ በመምጣቱ የእንቅስቃሴ ገደብ ዳግም ጣለች

    ምን ግዜም እሁድ እሁድ የገበያ ስፍራዎች ለፀረ ተህዋሲያን ርጭት ዝግ እንደሚሆኑ ተገልጿል

    የጋምብያ ፕሬዝዳንት አዳማ ባሮው በአገራቸው፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ለ21 ቀናት የሚቆይ የሰዓት እላፊና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደነገጉ።

    ፕሬዝዳንቱ የአገሪቱ ድንበሮችና የአየር ክል ለከባድ ጭነት፣ ለዲፕሎማቶች እና ባህር ማዶ ሕክምና ለሚያስፈልጋቸው ካልሆነ በስተቀር ዝግ መሆኑን ገልፀዋል።

    ፕሬዝዳንቱ እየጨመረ ያለው ወረርሽኝን “ አሳሳቢ” መሆኑን ተናግረዋል።

    አገሪቱ እስካሁን ድረስ 700 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን በምርመራ ስታረጋግጥ 16 ሰዎች መሞታቸውን ደግሞ መዝግባለች።

    በኮቪድ-19 ከተያዙት ሰዎች መካከል የአገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት እና ሶስት ሚኒስትሮች ይገኙበታል።

    ሰኞ እለት ፕሬዝዳንት አዳማ ባሮው ምርመራ አድርገው ነፃ መሆናቸው ተረጋግጧል።

    በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ የአምልኮ ስፍራዎች፣ ትምህርት ቤቶች ዝግ እንደሚሆኑ ተገልጾ የመጨረሻ አመት ተማሪዎች ብቻ ለማጠናቀቂያ ፈተና ከ10 ቀን በኋላ እንዲቀመጡ እንደሚደረግ ተገልጿል።

  12. ድምጻዊ ኢቲቃ ተፈሪ

    ድምጻዊው ሃጫሉ ሁንዴሳ፣ በተገደለበት እለት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርግ ከጓደኞቹ ጋር በሆስፒታል ውስጥ ከወዲያ ወዲህ ሲሯሯጡ እንደነበር ያስታውሳል። አምቦ በነበረው የቀብር ስነስርዓት ላይም አብዛኛው ሰው በሐዘን ስሜት ውስጥ ሆኖ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አልተጠቀመም ነበር።

    ተጨማሪ ያንብቡ
    next
  13. Video content

    Video caption: ኬንያ የኮሮናቫይረስ ተንከባካቢ ነርሶቿን በዳንስ እያነቃቃች ነው

    ኬንያ የኮሮናቫይረስ ተንከባካቢ ነርሶቿን በዳንስ እያነቃቃች ነው

  14. ሞዛምቢክ ዳግም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደነገገች

    የሞዛምቢክ ፕሬዝዳንት ፍሊፔ ኒዩሲ

    የሞዛምቢክ ፕሬዝዳንት ፍሊፔ ኒዩሲ የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመቀነስ ከአርብ እኩለ ለሊት ጀምሮ የሚፀና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለቀጣዮቹ 30 ቀናት አወጁ።

    ከመጋቢት ወዲህ ሞዛምቢክ የጤና ጊዜ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስትደነግግ ይህ ለሁለተኛ ጊዜዋ ነው።

    ረቡዕ እለት ፕሬዝዳንቱ በአገሪቱ ቴሌቪዥን ቀርበው በሂደት የተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ ስለሚነሳበት ሁናቴ ተናግረዋል።

    የእንቅስቃሴ ገደቡ መላላት የሚጀምረው ከአስር ቀን በኋላ ሲሆን በቅድሚያ የከፍተኛ ትምህርት፣ ወታደራዊ እና የቴክኒክና የሙያ ተቋማት እንደሚከፈቱ ተናግረዋል።

    ሃይማኖታዊ መሰባሰቦችም እንደሚፈቀዱ ቢገለፅም እስከ 50 ሰዎች ብቻ የተገደኑ እንደሚሆኑ ተነግሯል።

    ቀብር ላይ የሚገኙ ሰዎች ብዛትም ከ20 ወደ 50 ከፍ እንደሚል ተገልጿል። ነገር ግን ሟች በኮቪድ-19 የሞተ ከሆነ በቀብሩ ላይ መገኘት የሚችሉት 10 ሰዎች ብቻ ናቸው ተብሏል።

    ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ መስከረም ላይ እንደሚሆን ገልፀው ሲኒማ ቢቶች፣ ቁማር ቤቶች፣ እና ስፖርት ማዘውተሪያዎች ይከፈታሉ ብለዋል።

    ሶስተኛው ዙር በጥቅምት ወር የመጨረሻ አመት ተማሪዎችና ትምህርት ቤቶች በአጠቃላይ ይከፈታሉ ተብሏል።

    ነገር ግን መጠጥ ቤቶች እንደተዘጉ ይቆያሉ።

    ሞዛምቢክ እስካሁን ድረስ 2,079 ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸውን ስታረጋገጥ 15 ሰዎች ደግሞ ሞተዋል።

  15. ፈረንሳይ፣ ስፔንና ግሪክ ጭንቀት ገብቷቸዋል

    ኮሮና

    ፈረንሳይ፣ ስፔንና ግሪክ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እንደአዲስ ማገርሸቱ ጭንቀት ሆኖባቸዋል።

    ሃገራት በአውሮፓ እንደ አዲስ የጎመራው የቫይረሱ ወረርሽኝ ጎልቶ ከታየባቸው ሃገራት መካከል ናቸው።

    ፈረንሳይ በ24 ሰዓታት ብቻ 1695 ሰዎች በቫይረሱ እንደተያዙባት ይፋ አድርጋለች። ሃገሪቱ እስከ ዛሬ ድረስ 228 ሺህ 576 ሰዎች በቫይረሱ እንደተያዙባት ይታወቃል።

    ስፔን ደግሞ 1772 ሰዎች በ24 ሰዓታት ውስጥ በቫይረሱ ተይዘው እንደተገኙባት ይፋ አድርጋለች። ጠቅላላው ቁጥርም 305 ሺህ ተሻግሯል።፥

    ሌላኛዋ አውሮፓዊት ሃገር ግሪክ ደግሞ 124 ሰዎች በአንድ ቀን ውስጥ እንደተያዙባት ነው ያሳወቀችው።

    ሃገራት የእንቅስቃሴ ገደባቸውን ማላላት ከጀመረ ወዲህ ወረርሽኙ እየጎመራ ነው።

  16. የቀጥታ ዘገባ ገፃችን ሥራውን ጀምሯል

    Covid-19

    የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን የተመለከቱ ዘገባዎችን ወደናንተ የምናደርስበት ገፅ ሥራውን ጀምሯል።

    በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የተያዙት ሰዎች ቁጥር ወደ 20 ሺህ 336 ደርሷል። የሟቾች ቁጥርም ከ350 በላይ ሆኗል።

    በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የምንኖር የቢቢሲ አማርኛ ቤተሰቦች የሆንን ሁሉ ራሳችንንም ሆነ ወዳጆቻችንን ለኮሮናቫይረስ ላለማጋለጥ አካላዊ ርቀታችንን መጠበቅ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግና እጃችንን በውሃና በሳሙና በሚገባ መታጠብ እንዳለብን አንርሳ።

    ከኮሮናቫይረስ ጋር የተያያዙ ዋና ዋና መረጃዎችን በዚህ የቀጥታ ዘገባ ገፃችን ላይ እናቀርብላችኋለን።

  17. የአሜሪካ መንግሥት 100 ሚሊዮን ክትባቶችን ማዘዙ ተሰማ

    ክትባት

    አሜሪካ በሙከራ ላይ ያለን የኮሮናቫይረስ ክትባት፣ 100 ሚሊዮን ክትባቶችን ለመግዛት አዘዘች።

    ጆንሰን ጆንሰን የተሰኘው ኩባንያ ክትባቱ ላይ ሙከራ እያደረገ ሲሆን፣ የአሜሪካ መንግሥት ጋር ወደፊት 200 ሚሊዮን ክትባቶችን እጨምራለሁ በማለት አሁን የአንድ ቢሊዮን ዶላር ስምምነት መፈረሙ ተገልጿል።

    በሙከራ ላይ ያለው ክትባት፣ ኩባንያው የኢቦላን ክትባት ለመስራት የተጠቀመውን ቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ መሆኑ ተገልጿል።

    የአሜሪካ መንግሥት በኮሮናቫይረስ ክትባት ላይ ጆንሰን ጆንሰን የሚያደርገውን የሙከራ ክትባት ብቻ አይደለም ለመግዛት ውለታ የፈረመው።

    ባለፈው ሳምንት ሳኖፊ እና ፍላክሶስሚዝክሊን እየሰሩት ያለውን ክትባት 100 ሚሊዮን ክትባቶች ለመግዛት ስምምነት የፈረመ ሲሆን፣ በሐምሌ ወር ደግሞ ከፋይዘር እና ባዮንቴክ ጋርም ተመሳሳይ ስምምነት ደርሷል።

    የአሜሪካ ባለስልጣናት አሜሪካ ቢያንስ በ2021 አንድ ደህንነቱ የተረጋገጠ ክትባት እንደምታገኝ ተስፋ አድርገዋል።

    በዓለም ላይ በአሁኑ ሰዓት 140 ክትባቶች ላይ ምርምር እየተደረገ ሲሆን፣ ነገር ግን ስድስቱ ብቻ የመጨረሻ ሙከራ ደረጃ ላይ ደርሰዋል።

  18. የዓለም ጤና ድርጅት ለወጣቶች- መዝናናቱን በልክ አድርጉት

    ምሽት ክበብ

    ወጣቶች የመዝናናት ባህሪያቸውን የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመቀነስ ሲሉ ዳግም ሊያጤኑት እንደሚገባ አንድ ከፍተኛ የዓለም ጤና ድርጅት ባለሙያ ተናገሩ።

    አክለውም አንዳንድ አገራት የእንቅስቃሴ ገደቡን ካላሉ በኋላ መጀመሪያ ታይቶ ያልነበረ አሁን በወጣቶች መካከል ከፍተኛ የሆነ ስርጭት መታየቱን ጠቅሰዋል።

    የዓለም ጤና ድርጅት የአስቸኳይ ጊዜ የጤና ቡድን ኃላፊ ዶ/ር ማይክ ራያን "ወጣቶች ኃላፊነት እንዳለባቸው ሊያውቁ ይገባል" ሲሉ ተናግረዋል።

    "ወደዚህ የመዝናኛ ስፍራ መሄድ ይኖርብኛል? በቤት ውስጥ የተዘጋጁ ጭፈራዎች ወይም ምሽት ክበቦች መሄድ አለብኝ? በማለት ራሳችሁን ጠይቁት"

    የኃላፊው አስተያየት የድርጅቱ ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም ከዚህ ቀደም ወጣቶች የሚያደርጉት ምርጫ " ለአንዳንዶች የሞትና የህይወት ነው" ካሉት ጋር የተስማማ ነው።

  19. ከአፍጋኒስታን ህዝብ አንድ ሶስተኛው በኮቪድ-19 ሳይያዝ አይቀርም

    በአፍጋኒስታን በሰኔ ወር ላይ በሄራት ከተማ ለኮሮናቫይስ ህሙማን አዲስ ሆስፒታል ተከፍቷል
    Image caption: በአፍጋኒስታን በሰኔ ወር ላይ በሄራት ከተማ ለኮሮናቫይስ ህሙማን አዲስ ሆስፒታል ተከፍቷል

    ከአፍጋኒስታን ህዝብ አንድ ሶስተኛው ወይንም 10 ሚሊዮን ያህሉ በኮሮናቫይረስ ሳይያዝ እንዳልቀረ የአገሪቱ ጤና ሚኒስትር ለናሙና የተሰራ ጥናትን ጠቅሰው አስታወቁ።

    የዳሰሳ ጥናቱ ውጤት የተገኘው በዓለም ጤና ድርጅትና በጆንስ ሆፕኪንስ ድጋፍ፣ በመላ አገሪቱ ከሚገኙ 9 ሺህ 500 ሰዎች ላይ በተደረገ የአንቲቦዲ ምርመራ ነው

    የጤና ሚነስትሩ አህመድ ጃዋድ ኦስማኒ በርካታ ቫይረሱ እንዳለባቸው የተረጋገጡ ሰዎች የተገኙት በከተሞች ሲሆን ይህ ደግሞ በዋና ከተማዋ ካቡል የባሰ መሆኑን ገልፀዋል።

    አብዛኛዎቹ ግለሰቦች ምልክት የማያሳዩ እንደሆነም ጨምረው ገልፀዋል።

    በአፍጋኒስታን 36 ሺህ ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸው በምርመራ ሲረጋገጥ ከእነዚህ መካከል 1 ሺህ 200 ሰዎች ሞተዋል።

    አፍጋኒስታን በከፋ ድህነት ውስጥ ስትሆን የጤና ተቋማቷም ለአስርታት በዘለቀው ግጭት የተነሳ ደካማ ነው።

  20. ደቡብ አፍሪካ ኮሮናቫይረስን በቁጥጥር ስር እያዋለችው ይሆን?

    በደቡብ አፍረካ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 500 ሺህ ያለፈው ባለፈው ሳምንት ነበር
    Image caption: በደቡብ አፍረካ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 500 ሺህ ያለፈው ባለፈው ሳምንት ነበር

    የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ከአፍሪካ በትልቅነቱ የተጠቀሰውን የአገሪቱን የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በሚገባ እየተቆጣጠረው መሆኑን ገለፀ።

    ባለፈው ሳምንት በደቡብ አፍሪካ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 500 ሺህ አልፎ ነበር።

    ነገር ግን በመላው ደቡብ አፍሪካ በወረርሽኙ አዲስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ ሲሆን በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ እጅግ በተሻለ ሁኔታ መቀነሱ ተነግሯል።

    የጤና ሚኒስትሩ ዝዌሊ ማክሂዜ እንዳሉት፣ መንግስት ተግዳሮቶች እና እንቅፋቶች ቢገጥሙትም ስርጭቱን መቆጣጠር ችሏል።

    ሆስፒታሎች ሙሉ በሙሉ በህሙማን አልተጨናነቁም። የጽኑ ህሙማን ክፍሎችም ቢሆኑ እንደ ቀድሞው በሁለት እጥፍ የሰዎችን ህይወት ለማዳን እየሰሩ ነው።

    ባለሙያዎች ግን በደቡብ አፍሪካ ያለው የኮሮናቫይረስ ስርጭት ያለበት ሁናቴ በሁለት ሳምንት ውስጥ ግልጽ ይሆናል እያሉ ነው።

    ደቡብ አፍሪካ ሁለተኛው ዙር ወረርሽኝን ማስወገድ ፈተና ሊሆንባት እንደሚችል ተጠቅሷል።

    የደቡብ አፍሪካ ምጣኔ ሃብት ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ሲሆን በርካታ ዜጎች ጥብቅ የሆነውን የእንቅስቃሴ ገደብ እንዲላላ አልያም እንዲነሳ እየጠየቁ ነው።