ከባለቤቱ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት 4 ሰዎችን የገደለው ፖሊስ ተያዘ

ፖሊስ ወንጀሉ በተፈጸመበት ስፍራ ምርመራ ሲያደርግ

የፎቶው ባለመብት, Addis Ababa Police

የምስሉ መግለጫ, ፖሊስ ወንጀሉ በተፈጸመበት ስፍራ ምርመራ ሲያደርግ

ከባለቤቱ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት 4 ግለሰቦችን በጦር መሳሪያ ተኩሶ የገደለው የፖሊስ አባል በቁጥጥር ስር መዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

ተጠርጣሪው የግድያ ወንጀሉን የፈፀመው መስከረም 1 ቀን 2013 ዓ.ም ከምሽቱ 2፡30 በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ልዩ ቦታው ጨርጨር ጊርጎስ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነው ብሏል ኮሚሽኑ በፌስቡክ ገጹ ባሰፈረው መረጃ።

ተጠርጣሪው ረዳት ሳጅን መልህቁ መኪ የተባለ የፖሊስ አባል ሲሆን ከባለቤቱ ጋር በትዳር ለሁለት ዓመት አብረው ሲኖሩ በመካከላቸው በተፈጠረ አለመግባባት ከ15 ቀን በፊት ባለቤቱ ወደ ቤተሰቦቿ ቤት መሄዷን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የኮምኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ጄላን አብዲ ገልጸዋል።

ከባለቤቱና ከቤተሰቦቿ ጋር የተፈጠረውን አለመግባባት ምክንያት በማድረግ ተጠርጣሪው የፖሊስ አባል ለስራ የታጠቀውን መሳሪያ ይዞ ወደ ባለቤቱ ቤተሰቦች ቤት በመሄድ የሚስቱን እናት ፣የእንጀራ አባቷን፣ የእህቷን ባል እና የቤት ሰራተኛን በአጠቃላይ 4 ግለሰቦችን ተኩሶ በመምታት ህይወታቸው እንዲያልፍ አድርጓል ብሏል ፖሊስ።

ግለሰቡ ወዲያውኑ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን የተለያዩ ማስረጃዎችን በማሰባሰብ የምርመራ ሂደቱ የተጀመረ መሆኑን እና ምርመራውንም በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ለሚመለከተው የፍትህ አካል እንደሚላክ ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።

''የአዲስ ዓመት የበዓል አከባበር በሰላም እንዲከናወን መላው የፖሊስ አባላትና የፀጥታ ሃይሉ ሌት ከቀን ሃላፊነታቸውን በቁርጠኝነት ሲፈፅሙ ብለሹ ስብዕና ባለው አንድ የፖሊስ አባል የተፈፀመው ተግባር ኮሚሽኑን በእጅጉ ያሳዘነ ከመሆኑም ባሻገር የፖሊስ አባላቱን እና የፀጥታ ሃይሉን የማይወክል ነው'' ሲሉ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የኮምኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ጄላን አብዲ ገልጸዋል።