Got a TV Licence?

You need one to watch live TV on any channel or device, and BBC programmes on iPlayer. It’s the law.

Find out more
I don’t have a TV Licence.

ቀጥታ ዘገባ

የተጠቀሱት ሰዓቶቸ የዩናይትድ ኪንግደም ናቸዉ

  1. የኦክስፎርዱ ክትባት ውጤታማ መሆኑ የሚታወቀው በጥቅምት መሆኑ ተገለጸ

    በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ እየተሠራ ያለው የኮቪድ-19 ክትባት ውጤታማ መሆኑ የሚታወቀው በቀጣዩ ዓመት ጥቅምት ላይ ነው ተባለ።

    አስትራዜንካ የተባለው የመድኃኒት ድርጅት በሚቀጥለው ዓመት መጨረሻ ሁለት ቢሊዮን ክትባት የማምረት እቅድ ይዟል።

    በዩናይትድ ኪንግደም፣ በአሜሪካ፣ በብራዚል እና በደቡብ አፍሪካ የተጀመሩ ሙከራዎች ውጤታማ መሆናቸው የሚታወቀውም በቀጣዩ ዓመት ነው።

    ድርጅቱ ለቢቢሲ እንዳለው፤ ቢያንስ ለ12 ወራት የሚቆይ በሽታ የመከላከል አቅም እንደሚያዳብር ያምናሉ። ከዚህ በተጨማሪም ለ24 ወራት ወይም ከዚያ በላይ በሽታ መከላከል ያስችላል ብለው ተስፋ ያደርጋሉ።

    ጥናቱ አሁን ባለበት ደረጃ፤ ክትባቱ በሽታ የመከላከል አቅምን እንደሚያለምድ ቢታወቅም፤ ሙሉ በሙሉ ውጤታማ መሆኑ ገና አልተረጋገጠም።

    ከአንድ ጠብታ ይልቅ ሁለት ጠብታ የተሻለ ውጤታማ እንደሆነ ጥናቱ አሳይቷል።

    ሆኖም ግን ክትባቱ ለምን ያህል ጊዜ በሽታ እንደሚከላከል አልታወቀም። በተጨማሪም ለበሽታው በዋነኛነት ተጋላጭ የሆኑ አረጋውያን ላይ ምን ያህል ውጤታማ እንደሚሆን አልታወቀም።

    ክትባት
  2. የቀድሞው የአሜሪካ እጩ ፕሬዘዳንት በኮሮናቫይረስ ሞቱ

    ኸርመን ኬይን
    Image caption: ኸርመን ኬይን

    በ2012ቱ የአሜሪካ ምርጫ የሪፐብሊካን ተወዳዳሪ የነበሩት ኸርመን ኬይን በኮሮናቫይረስ ሳቢያ ሕይወታቸው አለፈ።

    የ74 ዓመቱ ኸርመን በበሽታው ተይዘው ሆስፒታል የገቡት በወሩ መባቻ ላይ ነበር።

    በድረ ገጻቸው ላይ “አለቃችን፣ ጓደኛችንና ለብዙዎቻችን እንደ አባት የነበሩት ኸርመን ኬይን አርፈዋል” የሚል መልዕክት ተለጥፏል።

    የፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደጋፊ የነበሩ ሲሆን፤ አሜሪካ ውስጥ በቫይረሱ ከሞቱ እውቅ ፖለቲከኞች አንዱ ናቸው።

    ሆስፒታል ሳሉ ስለሚገኙበት ሁኔታ በማኅበራዊ ሚዲያዎቻቸው ላይ መረጃ ሲሰጥ ነበር።

    ሐምሌ 7 የኦክስጅን መጠናቸው ትክክለኛ መሆኑን ሀኪሞች እየመረመሩ መሆኑ ተገልጾ፤ “ከባድ ቫይረስ ነው። መጸለያችሁን አታቋርጡ” የሚል መልዕክት በትዊተር ገጻቸው ተላልፎ ነበር።

    የተወለዱት በቴንሲ ሲሆን፤ ቤተሰቦቻቸው የጽዳት ሠራተኞች ነበሩ። በሒሳብ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በኮምፒውቲንግ ሁለተኛ ዲግሪ አግኝተዋል።

    የቤተ ክርስቲያን አጥማቂ፣ የሬድዮ መርሀ ግብር አዘጋጅና ነጋዴም ነበሩ።

  3. አውሮፓ እና ኮሮናቫይረስ

    ኮቪድ-19 በአውሮፓ አገራት በስፋት እየተሰራጨ ይገኛል። ከተለያዩ የአውሮፓ አገሮች የተውጣጡ ዜናዎች ተከታዮቹ ናቸው።

    ·ፖላንድ እና ሮማንያ- በአንድ ቀን ቫይረሱ የተገኘባቸው በርካታ ሰዎችን ካስመዘገቡ አገሮች መካከል ናቸው። ሮማንያ እንቅስቃሴ እንዲገታ ወስናለች።

    ·አይስላንድ- ለሦስት ወራት ቀስ በቀስ የእንቅስቃሴ ገደብ ሲላላ ነበር። ነገር ግን የቫይረሱ ስርጭት እየጨመረ በመምጣቱ በድጋሚ እርምጃ ሊወሰድ ነው።

    ·ስፔን- በመዲናዋ ማድሪድ አዲስ የጥንቃቄ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው። ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች አካላዊ ርቀት መጠበቅ ቢቻልም ባይቻልም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግ ግዴታ ነው።

    ·ፈረንሳይ-የበሽታው ስርጭት እየጨመረ ቢሆንም፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዣን ካስቴክስ ለሁለተኛ ጊዜ እንቅስቃሴ ላይ ገደብ እንዳይጣል አስፈላጊው ሁሉ መደረግ አለበት ብለዋል።

    ዩናይትድ ኪንግደም- በበሽታው በተያዙ ሰዎች ቁጥር ከአውሮፓ ቀዳሚዋ ኢንግላንድ ናት። ከዚህ ቀደም ስፔን ሁለተኛ፣ ስኮትላንድ ደግሞ ሦስተኛ ነበሩ።

    ጭምብል
  4. ከዚምባብዌ ዜጎች ሁለት ሦስተኛው የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተገለጸ

    በዚህ ዓመት መጨረሻ ከዚምባብዌ ዜጎች ሁለት ሦስተኛው የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ተባለ።

    የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ተቋም በዚምባብዌ ሊከሰት የሚችለውን ሰብዓዊ ቀውስ ለመግታት ተጨማሪ የ250 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ እንደሚያስፈልገው ገልጿል።

    የዓለም የምግብ ፕሮግራም እንዳለው በዓመቲ መጨረሻ ላይ ከአገሪቱ ዜጎች ሁለት ሦስተኛው የምግብ እርዳታ ይፈልጋሉ።

    በአገሪቱ ይጠበቅ የነበረው የእህል ምርት አልደረሰም። የኑሮ ውድነት እና የኮሮናቫይረስ ስርጭትም ፈተና ሆነዋል።

    ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ የሥራ አጦችን ቁጥር ጨምሮታል። በከተማ ረሀብ ከመስፋፋቱም በላይ ለተሻለ ሕይወት ወደ ከተማ የተጓዙ የገጠር ሰዎች ወደ ትውልድ ቀያቸው እየተመለሱ ነው። ገጠር ውስጥ ደግሞ የምግብ እጥረት አለ።

  5. በኢትዮጵያ በአንድ ቀን 805 በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ተገኙ

    አሃዝ

    በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓታት 9786 ናሙናዎች ላይ በተደረገ የላብራቶሪ ምርመራ 805 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋገጠ። ይህም ወረርሽኙ ያለባቸው ሰዎች ኢትዮጵያ ውስጥ እንደተገኙ ከተገለጸ ወዲህ ከፍተኛው ቁጥር ነው።

    እስካሁን በበሽታው የተያዙ ሰዎች አጠቃላይ ቁጥር 16 ሺህ 615 ሆኗል።

    የጤና ሚንስቴር እና የሕብረተሰብ ጤና ተቋም ባወጡት መግለጫ እንደተመለከተው፤ 10 ተጨማሪ ሰዎች በቫይረሱ ሳቢያ ሕይወታቸው አልፏል። ይህም የሟቾችን ቁጥር 263 አድርሶታል።

    78 ተጨማሪ ሰዎች ከህመሙ ያገገሙ ሲሆን፤ ይህም እስካሁን ከኮቪድ-19 ያገገሙ ሰዎች ቁጥርን 6763 አድርሶታል።

    በአሁን ወቅት በአገሪቱ 134 በጽኑ የታመሙ ሰዎች አሉ።

    ኢትዮጵያ እስከ አሁን 413 ሺህ 397 የላብራቶሪ ምርመራ አካሂዳለች።

  6. በበርካታ የአፍሪካ አገራት የኮሮናቫይረስ ምርመራ አነስተኛ ነው

    እስካሁን ድረስ ከአፍሪካ አገራት ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ሕዝቧን የመረመረችው ደቡብ አፍሪካ ነች

    በአፍሪካ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር የየአገራቱ ጤና ሚኒስትሮች ከሚገልጹት ሊልቅ እንደሚችል በሰብዓዊ እርዳታ ላይ የተሰማራው አይ አር ሲ ገለፀ።

    አይ አር ሲ በቂ ምርመራ ማድረግ አለመቻልና ተገቢውን መረጃ አለማግኘት "በሽታውን በጨለማ እንደመዋጋት" ነው ሲል አስቀምጦታል።

    ድርጅቱ በሚንቀሳቀስባቸው 20 የአፍሪካ አገራት " የምርመራው መጠን ከዓለም ጤና ድርጅት መመሪያ እጅጉን የወረደ" ሲል ገልጾታል።

    በመላው አፍሪካ በሐምሌ ወር በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በእጥፍ መጨመሩን በመጥቀስም እናም ይህ "የችግሩ ጫፍ ሊሆን ይችላል" ሲል ስጋቱን ገልጿል።

    በአፍሪካ በአሁኑ ሰዓት 890,000 በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች መኖራቸውን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል።

    የዓለም ጤና ድርጅትም በአፍሪካ የሚካሄደው ምርመራ አነስተኛ በመሆኑ አንዳንድ በቫይረሱ የሚያዙ እና በዚሁ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ሳይመዘገቡ ይቀራል ሲል ገልጿል።

    ይሁን እንጂ የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር ዶ/ር ማትሺዲሶ ሞይቲ በዝምታ ሕዝቡን እየገደለ ያለ ወረርሽኝ አለ ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል።

    እንደ አፍሪካ በሽታ መከላከልና መቆጣጣር ከሆነ ደግሞ አህጉሪቱ ካላት 1.3 ቢሊየን የሕዝብ ብዛት ውስጥ 8.3 ሚሊየኑ ተመርምረዋል።

  7. ሙምባይ

    የዳሰሳ ጥናቱ ከሶስት ወር በኋላ የሚደገም መሆኑ የተገለፀ ሲሆን በዚህም ወቅት ስርጭቱ መስፋፋቱ አልያም መቀነሱ የሚታይ ይሆናል። ይህም በከተማዋ የቫይረሱ ስርጭት ያለበት ሁናቴ ማወቅ ያስችላል ተብሏል።

    ተጨማሪ ያንብቡ
    next
  8. ካሪ ላም

    የሆንክ ኮንግ መሪ ካሪ ላም ትላንት በሰጡት መግለጫ፤ የሆንክ ኮንግ ማሕበረሰብ ውስጥ ቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ የሚሰራጭበት ነጥብ ላይ ደርሷል ብለዋል።

    ተጨማሪ ያንብቡ
    next
  9. በርካቶች ብዝበዛ መንጓጠጥ እንደሚደርስባቸው ተናግረዋል

    የሴኤንኤን የምርመራ ዘገባ በሊባኖስ በቤት ሰራተኝነት የሚሰሩ ኬንያውያን በአገራቸው ቆንስላ ባለስልጣን እና ረዳቱ የሚደርስባቸውን ብዝበዛ ወይንም ጥቃት ይዞ ቀርቧል።

    ተጨማሪ ያንብቡ
    next
  10. በቻይና በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ቀጥሏል

    አሃዝ

    በቻይና ላለፉት ሰባት ቀናት በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ቀጥሏል። የአገሪቱ ብሔራዊ ጣቢያዎች፤ ዜጎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እንዲያደርጉና በአንድ ቦታ እንዳይሰበሰቡ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

    ባለፉት 24 ሰዓታት የበሽታው ምልክት ያልታየባቸው 105 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።

    በቻይና የበሽታውን ምልክት የሚያሳዩና የማያሳዩ ሰዎች በተለያየ መዝገብ ስለሚያዙ፤ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ይፋ ከተደረገውም በላይ ሊሆን ይችላል።

    አብዛኞቹ ቫይረሱ የተገኘባቸው ኡሩምኪ የተባለች ከተማ ነዋሪዎች ናቸው። በከተማው ሐምሌ 15፣ የ20 ዓመት ወጣት ቫይረሱ ከተገኘባት በኋላ የጅምላ ምርመራ እየተደረገ ነው። ባለፉት 24 ሰዓታት 96 የበሽታው ምልክት የታየባቸው ሰዎች፤ ኮቪድ-19 እንዳለባቸው ተረጋግጧል።

    ዴሊያን ሌላው በቫይረሱ በስፋት የተጠቃ ከተማ ቢሆንም፤ ዋነኛ ስጋት የሆነው የሆንክ ኮንግ ጉዳይ ነው።

    እስካሁን ከ3,000 በላይ ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል። የመተንፈሻ አካል ተመራማሪው ዦንግ ናንሻን ሆንክ ኮንግ ውስጥ የጅምላ ምርመራ ያስፈልጋል ብለዋል።

    ራስ ገዟ ሆንክ ኮንግ የቻይናን ጥብቅ እንቅስቃሴ የማቆም ውሳኔ አልተገበረችም።

  11. የኬንያ ትምህርት ቤቶች እስከ ዓመቱ መጨረሻ አይከፈቱም ተባለ

    የኬንያ ትምህርት ሚንስትር ኮሌጆችና ዩኒቨርስቲዎች እስከ መጪው የፈረንጆች አዲስ ዓመት ድረስ ዝግ ሆነው እንደሚቆዩ አስታወቀ።

    ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈው፤ ተቋማቱ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የሚረዱ እርምጃዎችን መውሰድ ባለመቻላቸው ነው።

    የትምህርት ሚኒስትሩ ጆርጅ ማጎሄ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፤ ተቋማቱ የድረ ገጽ ኮርሶችን፣ ፈተናዎችንና የምረቃ መርሃ ግብሮችን መስጠታቸውን ይቀጥላሉ።

    መሥሪያ ቤታቸው ኮሌጆችና ዩኒቨርስቲዎች ለመጪው ዓመት እንዲከፈቱ ኮቪድ-19ን ለመከላከል የወሰዷቸውን እርምጃዎች መቆጣጠሩን እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

    በኬንያ ትምህርት የተቋረጠው አገሪቱ የመጀመሪያውን በኮቪድ-19 የተያዘ ሰው ካገኘችበት መጋቢት ወር ጀምሮ ነው። መንግሥት የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችንም ሙሉ በሙሉ መዝጋቱ ይታወሳል።

  12. በጣልያን ጭምብል ያጠለቁ ግለሰቦች

    የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን አውሮፓ ሁለተኛ ዙር የኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ እንደሚያሰጋት ተናግረው ነበር። ነገር ግን ለዚህ ግምት ማስረጃ ሊሆን የሚችል ነገር አለ?

    ተጨማሪ ያንብቡ
    next
  13. በፓራጓይ በድጋሚ የተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ ተቃውሞ አስነሳ

    በፓራጓይ የተነሳው ተቃውሞ

    በፓራጓይ መንግሥት በአንዳንድ አገሪቱ ክፍሎች የእንቅስቃሴ ገደብ ማስቀመጡን ተከትሎ ከባድ ተቃውሞ መቀስቀሱ ተሰምቷል።

    በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሲዩዳድ ዴል ኤስቴ በተባለችው ከተማ በሚገኙ ጎዳናዎች በመውጣት ቁጣቸውን ገልጸዋል።

    በርካታ ሱቆች ስለመዘረፋቸውና አንዳንዶቹም ስለመቃጠላቸው ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች እየጠቆሙ ነው።

    ጥቂት የማይባሉ የፖሊስ አባላትም ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሏል።

    ፓራጓይ በመላው አገሪቱ ያለውን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ5 ሺ እንዳይበልጥ በሰራችው ስራ ከፍተኛ ምስጋና ተችሯት ነበር።

    ነገር ግን ረቡዕ ዕለት የአገሪቱ የጤና ባለስልጣናት አንዳንድ የጤና አገልግሎት መስጫዎች ከአቅማቸው በላይ እየሞሉ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

  14. የሳምሰንግ ስልክ

    የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ስርጭት ለመግታት የወጡት መመሪያዎችን ተከትሎ ሚሊዮኖች ከቤት ሆነው ስራቸውን ማከናወን እንዲሁም በርቀት ለመማር ተገደዋል።ይህም ሁኔታ የኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶች አምራች ለሆነው ሳምሰንግ ትርፉ እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል።

    ተጨማሪ ያንብቡ
    next
  15. ናንሲ ፔሎሲ

    በአሜሪካ ጭምብል የመልበሱ ነገር ብዙ ሲያጨቃጭቅ ነው የሰነበተው፡፡ ግማሾች አለመልበስ መብታችን ነው ይላሉ፡፡ ትራምፕም ቢሆን ጭምብል ማጥለቅ ይቀፋቸዋል፡፡ እምብዛምም ይህን ሲያበረታቱ አይታዩም፡፡

    ተጨማሪ ያንብቡ
    next
  16. የሕክምና ባለሙያዎች

    ጥናቱ ከዚህ በፊት በዩናይትድ ኪንግደም ባዮባክን ፕሮጀክት የተወሰዱ የግማሽ ሚሊዮን ሰዎችን የዘረመል ናሙና፣ የሽንትና የምራቅና ደም ቅንጣቶች በስፋት ይመረምራል፣ ውጤቱንም ይተነትናል ተብሏል፡፡

    ተጨማሪ ያንብቡ
    next
  17. ሃና

    የበሽታው ምልክት የጀመረኝ ሰኔ 23 [ጁን 30] ገደማ ነው። ከዚያ በፊት ባሉት ሳምንታት የተለያዩ ተቃውሞዎች ላይ ስሳተፍ ነበር። ነገር ግን በዚህ ወቅት ምንም ዓይነት የቫይረሱ ምልክት አልታየብኝም። ሁሌም የአፍና አፍንጫ ጭምብል እጠቀም ነበር። ሳኒታይዘርም ይዤ ነበር የምንቀሳቀሰው።ሃና ጆይ ገብረሥላሴ የተወለደችው በአሜሪካዋ ካሊፎርኒያ ደቡባዊ ግዛት ነው። ከቤተሰቦቿ ጋር ወደ አትላንታ ያቀናችው የአራት ዓመት ልጅ ሳለች ነበር። ሃና ከጥቂት ሳምንታት በፊት በኮሮናቫይረስ የቅርብ ዘመዷን እንዳጣች በትዊተር ገጿ ላይ አስፍራ ነበር። ከዚህም አልፎ እሷም ተመርምራ ኮቪድ-19 እንዳለባት ማወቋን በይፋ በመናገር ሌሎች በእሷ ዕድሜ ያሉ ወጣቶች ራሳቸውን እንዲጠብቁ በተደጋጋሚ መክራለች።

    ተጨማሪ ያንብቡ
    next
  18. ፍሎሪዳ የኮሮናቫይረስ መመርመሪያ ማዕከላትን ልትዘጋ ነው

    ፍሎሪዳ

    በአሜሪካ በእጅጉ በኮሮናቫይረስ ከተጠቁ ግዛቶች አንዷ የሆነቸው ፍሎሪዳ ወደ ግዛቲቱ እየመጣ ባለው ዝናብ የቀላቀለ አውሎ ንፋስ ምክንያት የኮቪድ-19 የምርመራ ማዕከላትን ልትዘጋ እንደሆነ አስታውቃለች።

    ''ሁሉም ማዕከላት ወደውስጥ ያልተቀበሩ መደገፊያዎችና ድንኳኖች የሚበዙባቸው በመሆናቸው የሚመጣውን አደጋ መቋቋም አይችሉም፤ በዚህ በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ'' ብለዋል የግዛቲቱ ድንገተኛ አደጋዎች መቆጣጠሪያ ቢሮ ኃላፈዎች።

    መመርመሪያ ማዕከላቱ ከዛሬ ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ ተዘግተው እንደሚቆዩም ተገልጿል።

    የአሜሪካ ኃላፊዎች እንዳስጠነቀቁት አውሎ ነፋሱ በሰአት 80 ኪሎሜትር የሚጓዝ ሲሆን በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ፍሎሪዳ ሊደርስ ይችላል።

    21 ሚሊዮን ነዋሪ የሚገኝባት ፍሎሪዳ እስካሁን 450 ሺ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ያረጋገጠች ሲሆን 6300 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል።

    ከነዚህ ሰዎች መካከል ደግሞ አንድ አራተኛን ቁጥር የሚእዙት ሰዎች ማያሚ ውስጥ ነው የሚገኙት።

  19. የጋምቢያው ፕሬዝዳንት ለይቶ ማቆያ ውስጥ እንደገቡ ገለፁ

    የጋምቢያው ፕሬዚዳንት አዳማ ባሮው

    የጋምቢያው ፕሬዚዳንት አዳማ ባሮው ራሳቸውን ለይቶ ማቆያ ውስጥ አስገብተዋል። ይህም የሆነው ምክትል ፕሬዚዳንቱ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው መረጋገጡን ተከትሎ ነው።

    ፕሬዚዳንቱ ለሁለት ሳምንት ያህል ከሰዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ያቋርጣሉ፤ በመንግሥታዊ ተግባርም አይሳተፉም ተብሏል።

    ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት ፅህፈት ቤት የወጣው መግለጫ እንደሚያመለክተው ምክትል ፕሬዚዳንት ኢሳቱ ቱራይ በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ነው።

    ኢሳቱ ቱራይ "ጤንነታቸው በደህና ሁኔታ ላይ እንደሆነና ለይቶ ማቆያ እገባለሁ" ብለዋል።

    በጋምቢያ እስካሁን ድረስ 326 ሰዎች በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሲሆን ስምንት ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

    መንግሥትም ዜጎች ጭምብል እንዲያጠልቁና አካላዊ ርቀታቸውን በመጠበቅ የቫይረሱን ስርጭት እንዲገቱት ጥሪ እያደረገ ነው።

  20. እንዴት አደራችሁ ውድ የቢቢሲ አማርኛ ቤተሰቦች!

    አበቦች

    እንደምን አደራችሁ የቢቢሲ አማርኛ ወዳጆች?

    ኮሮረናቫይረስን በተመለከተ ወደናንተ የተለያዩ መረጃዎችን የምናቀርብበት ዕለታዊ የቀጥታ ዘገባ ገጻችን ተጀምሯል።

    በዓለማችን ላይ በኮሮረናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 17 ሚሊየን እየተጠጋ ሲሆን ከ600 ሺ በላይ ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

    እናንተም እራሳችሁን እና ወዳጆቻችሁን ከቫይረሱ ለመከላከል በመንግስት የተቀመጡ የጥንቃቄ እርምጃዎችን እንድትከሉ ለማሳሰብ እንወዳለን።

    አብራችሁን ቆዩ!