Got a TV Licence?

You need one to watch live TV on any channel or device, and BBC programmes on iPlayer. It’s the law.

Find out more
I don’t have a TV Licence.

ቀጥታ ዘገባ

የተጠቀሱት ሰዓቶቸ የዩናይትድ ኪንግደም ናቸዉ

  1. "ኮሮናቫይረስን አሜሪካ ለኢራን የሰራችው ነው" አያቶላህ አሊ ሃሚኒ

    አያቶላህ አሊ ሃሚኒ

    የኢራን ሐይማኖታዊ የበላይ መሪ አገራቸው የኮሮናቫይረስን ለመዋጋት ለምታደርገው ጥረት ከአሜሪካ የቀረበላትን እርዳታ የመስጠት ጥያቄ እንደማይቀበሉት አሳወቁ።

    አያቶላህ አሊ ሃሚኒ በቴሌቪዥን ቀርበው ባደረጉት ንግግር ላይ እንዳሉት አሜሪካ የኢራን "ከሁሉ የባሰች ጠላት" ናት በማለት ቀደም ሲል አሜሪካ ለወረርሽኙ መከሰት ተጠያቂ ናት ሲሉ አንዳንድ የቻይና ባለስልጣናት ያቀረቡትን የሴራ ትንተና ክስ ጠቀስ አድርገዋል።

    "ይህ ክስ ምን ያህል እውነተኛ መሆኑን አላውቅም ነገር ግን እየተነገረ ነው፤ ታዲያ አእምሮው በትክክል የሚሰራ ሰው መድሃኒት ይሰጡኛል ብሎ እምነት ይጥልባቸዋል?" ሲሉ የጠየቁት ሃሚኒ "ስለዚህም የምትሰጡን መድሃኒት ቫይረሱን የበለጠ ለማስፋፋት የምትጠቀበት መንገድ ነው" ሲሉ አሜሪካንን ከሰዋል።

    መሪው ጨምረውም ምንም ማስረጃ ሳያቀርቡ "የኮሮናቫይረስ የኢራናዊያንን የዘረመል መረጃ በተለያዩ መንገዶች በመውሰድ በተለየ ሁኔታ ለኢራን የተሰራ ነው" ሲሉ ጣታቸውን አሜሪካ ላይ ቀስረዋል። ሙሉውን ለማንበብ ይህንን ይቻኑ ኢራን ከአሜሪካ ቀረበላትን የህክምና እርዳታ አልቀበልም አለች

  2. የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማረረዎቹንና ሠራተኞቹን ከበሽታ ለመከላከል ውሳኔ አሳለፈ

    አርማ

    የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በተቋሙ ውስጥ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አማካይነት ሊከሰት የሚችልን የኮሮናቫይረስ በሽታ ስርጭትን ለመከላከል የሚያስችሉ ውሳኔዎችን ዛሬ አሳልፏል።

    በዚህም መሰረት በተማሪዎችና በዩኒቨርስቲው ሠራተኞች መካከል ያለውን ንክኪ ለማስወገድ የሚያስችሉ ውሳኔዎችን ያሳለፈ ሲሆን ተማሪዎች በዩኒቨርስቲው ጊቢ ውስጥ ብቻ እንዲቆዩ ወስኗል።

    ዩኒቨርስቲው እንዳለው ማንኛውም ተማሪ ከጊቢ መውጣት አይችልም ከወጣም ተምልሶ መግባት አይፈቀድለትም፤ ነገር ግን መግባት የሚፈልግ ከሆነም ምርመራ አድርጎ ከበሽታው ነጻ መሆኑ መረጋገጥ ይኖርበታል።

    በተጨማሪም ተማሪዎች የሚሰባሰቡበትን አጋጣሚዎች ለማስቀረት ስፖርታዊ ጨዋታዎችን በጋራ ማድረግና ቴሌቪዥን በጋራ መመልከት ተከልክሏል።

    የትምህርት ሂደቱን በተመለከተም ተማሪዎች ከቤታቸው ወይም ከመኝታ ክፍላቸው ሆነው በኢንትርኔት አማካይነት ትምህርታቸውን ይከታተላሉ ሲል፤ መምህራን ደግሞ በኢንትርኔት አማካይነት ከቤታቸው ሆነው ትምህርት መሰጠቱን ይቀጥላል ብሏል።

    በተጨማሪም ተማሪዎች በላይብረሪና ምግብ ቤት ውስጥ ቢያንስ የአንድ ሜትር ርቀት መጠበቅ እንዳለባቸዋል አመልክቶ፤ በዩኒቨርስቲው ውስጥ ያሉ ሙዚየሞችና የሚጎበኙ ስፍራዎች ቱሪስቶችን ጨምሮ ለሁሉም ዝግ ይሆናሉ ተብሏል።

  3. አፍሪካ ውስጥ በኮቪድ-19 ከተያዙ ሰዎች መካከል 108ቱ ዳኑ

    የእጅ ማጽጃ ሲሰጥ

    አፍሪካ ውስጥ በኮሮናቫይረስ ተይዘው ከነበሩ ሰዎች መካከል ከአንድ መቶ በላይ የሚሆኑት መዳናቸውን ተነገረ።

    የአፍሪካ የበሽታ መከላከያ ማዕከል እንዳለው እስካሁን በበሽታው ከተያዙት ሰዎች መካከል 108 ሰዎች ከኮሮናቫይረስ ድነዋል።

    ቢሆንም ግን ቅዳሜና እሁድ በወታ መረጃ መሰረት በአህጉሪቱ በኮሮናቫይረስ የተያዙት ሰዎች ቁጥር ከአንድ ሺህ ማለፉን የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል አስታወቀ።

    ስለዚህም በአሁኑ ጊዜ በአፍሪካ ውስጥ በኮቪድ-19 የተጠቁ ሰዎች ቁጥር 1198 እንደደረሰ ታውቋል።

    ኡጋንዳ የመጀመሪያውን ታማሚ ትናንት ስታገኝ ፕሬዝዳንቷ በርካታ ሰዎች የሚሰበሰቡባቸውን አጋጣሚዎች የሚያስቀሩ እርምጃዎች እንደሚወሰዱ ያሳወቁ ሲሆን በተጨማሪም ከዛሬ ዕኩለ ሌሊት ጀምሮ ሁሉንም በረራዎች አግዳለች።

    ሩዋንዳም በበኩሏ ባለፈው ሐሙስ ማንኛውንም እንቅስቃሴዎች ለመከልከል ያወጣችውን ውሳኔ ለተከታይ 14 ቀናት እንዲወጥል ልታደርግ እንደምትችል አሳውቃለች።

    ሩዋንዳ 17 በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎችን በማስመዝገብ በምሥራቅ አፍሪካ ክልል ውስጥ የመጀመሪያውን ቦታ ይዛለች።

    በዴሞክራቲክ ኮንጎ የመጀመሪያው በበሽታው የሞተ ሰው ተመዝግቧል። ግለሰቡ ዶክተር ሲሆን በቅርቡ ከፈረንሳይ ከተመለሰ በኋላ በድንገት ታሞ ነው ህይወቱ ያለፈው ተብሏል።

  4. በዓለም ዙሪያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ307 ሺህ በላይ ሆነ

    ከወራት በፊት በቻይናዋ ሁቤይ ግዛት ዉሃን ከተማ ተከስቶ ከአንድ መቶ ሃምሳ በላይ አገራትን ባዳረሰው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ307 ሺህ በላይ መድረሱ ተነገረ።

    በኮቪድ-19 ተይዘው የነበሩ ነገር ግን ባገኙት ህክምና የዳኑ ሰዎች ቁጥር ከ92 ሺህ በላይ የደረሰ ሲሆን ቁጥሩ እየጨመረ ነው ተብሏል።

    እስካሁን ከ13 ሺህ በላይ ሰዎች በኮሮናቫይረስ ሰበብ ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን በርካታ ሰዎች የሞቱባት አገርም ጣሊያን እንደሆነች ተነግሯል።

    የበሽታው ምልክቶች
  5. ኤርትራ በሸቀጦች ላይ ዋጋ የሚጨምሩ ነጋዴዎችን ንብረት እንደምትወርስ አስጠነቀቀች

    ከአሥመራ ገበያዎች አንዱ

    በኤርትራ ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ ‘ምክንያታዊ ያልሆነ’ የዋጋ ጭማሪ መታየቱን የሃገሪቱ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ።

    በተለይም በአሥመራ ከተማ በእህል፣ በዘይት፣ በስኳርና በጽዳት ዕቃዎች ላይ የዋጋ ጭማሪ መስተዋሉን የገለጸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፤ ድርጊቱ የሕዝቡን ኑሮ የሚጎዳ በመሆኑ “ከባድ እርምጃ” እንደሚወስድ ገልጿል።

    ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉና ዕቃዎችን በሚደብቁ ነጋዴዎች ላይ የንግድ ፍቃድን ከመንጠቅ አንስቶ እስከ ንብረት መውረስ የሚደርስ እርምጃን እንደሚወስድ አስታውቋል።

  6. ጃክ ማ እና አሉባባ ፋውንዴሽኖች 6 ሚሊዮን የህክምና መገልገያዎችን ለገሱ

    የህክምና መገልገያዎች ጭነት

    ከጃክ ማ እና አሊባባ ፋውንዴሽን የተለገሱ ለኮቪድ-19 [ኮሮናቫይረስ] ህክምና የሚውሉ የህክምና አቅርቦቶች ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን ድርጅቶቹ አስታወቀ።

    ዛሬ አዲስ አበባ የደረሱት እነዚህ ህክምና መገልገያ ቁሶች ከ6 ሚሊዮን በላይ የፊት መሸፈኛ ጭንብሎት፣ የመመርመሪያ መሳሪያዎችና የመከላከያ አልባሳት እንዲሁም የፊት መሸፈኛዎች ናቸው።

    በኢትዮጵያ አየር መንገድ የጭነት አውሮፕላን ከቻይናዋ ጓንግዡ አዲስ አበባ የገቡት እነዚህ መገልገያዎች በመላው አፍሪካ በተለይም ለበሽታው ተጋላጭ ናቸው ለተባሉ አገራት የሚከፋፈል መሆኑን ፋውንዴሽኖቹ ባወጡት መግለጫ ላይ አመልክተዋል።

    ከዚህ በተጨማሪም ሌላ ዙር የህክምና መገልገያዎች በሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ አዲስ አበባ ደርሰው ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገራት እንደሚሰራጩም ተነግሯል።

    ፋውንዴሽኖቹ ከዚህ ቀደም ብሎም የተለያዩ አይነት የህክምና መገልገያዎች በኮሮናቫይረስ ክፉኛ ለተጠቁት ቻይና፣ ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ አሜሪካ፣ ጣሊያንና ለሌሎች አገራትም መለገሳቸው በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።

  7. የኮሮናቫይረስን ለመቆጣጠር አፍሪካ ከእስያ አገራት ምን ትማራለች?

    የህክምና ባለሙያዎች

    በአውሮፓና በአሜሪካ በኮሮናቫይረስ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው። ይህንንም ተከትሎ አገራት የበረራ እገዳ፣ የትምህርት ቤት መዘጋትና የእንቅስቃሴ ገደብ አስተላልፈዋል።

    ከበርካታ ሳምንታት በፊት ግን ወረርሽኙ በርካታ የእስያ አገራትን አጥቅቶ ነበር። አንዳንዶቹ አገራት በቀላሉ ቫይረሱን በቁጥጥር ሥር ማዋል በመቻላቸው ተደንቀዋል።

    ከእነዚህም አገራት መካከል ሲንጋፖር፣ ሆንግ ኮንግ እና ታይዋን የሚገኙበት ሲሆን በአንጻራዊነት ለቻይና ካላቸው ቅርበት አንጻር ሲታይ በእነዚህ አገራት በቫይረሱ የተያዙና የሞቱ ሰዎች ቁጥር በጣም ትንሽ ነው።

    እነዚህ አገራት ምን የተለየ ነገር ቢያከናውኑ ነው የቫይረሱን ስርጭት በቀላሉ መቆጣጠር የቻሉት? አፍሪካ ከእነዚህ አገራትስ የምትማረው ይኖር ይሆን? ዝርዝሩን ለማንበብ ይህንን መስፈንጠሪያ ይቻኑ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን በመቆጣጠር ረገድ አፍሪካ ከእስያ አገራት ምን ትማራለች?

  8. በኮሮናቫይረስ ተጠርጥራ የነበረችው ተማሪ ነጻ ሆና ተገኘች

    የአክሱምዩኒቨርስቲ አርማ

    በኮረናቫይረስ ተጠርጥራ አክሱም ውስጥ በሚገኝ የለይቶ ማቆያ ክትትል ሲደርግላት የነበረች ተማሪ በተደረገላት የናሙና ምርመራ ከቫይረሱ ነፃ መሆኗ መረጋገጡን የአክሱም ዩኒቨርስቲ አስታወቀ።

    መንግሥት በመላው አገሪቱ የሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የበሽታውን መስፋፋት ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃዎችን በአግባቡ እንዲያከናውኑ አስፈላጊውን ሁሉ እያደረገ መሆኑ ተገልጿ።

    የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቱትዩት ጋር በመሆን በአገሪቱ ከሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች አመራሮች ጋር በሽታውን በተመለከተ ባደረጉት ውይይት ዩኒቨርሲቲዎቹ የሚጠበቅባቸውን እያከናወኑ መሆኑ ተነግሯል።

    በዚህም መሰረት የንጽህና መጠበቂያ ፈሳሾችን ለተማሪዎች ማቅረብ፣ ተማሪዎች ከግቢያቸው እንዳይወጡ ማድረግ፣ የሚያሰባሰቡባቸውን ነገሮች መቀነስና በየትኛውም ቦታ ተጠጋግተው እንዳይገኙ ለማድረግ አስፈላጊው ሁሉ ነገር እየተደረገ ነው ተብሏል።

  9. በኤርትራና በኡጋንዳ የመጀመሪያ ታማሚዎች ተገኙ

    እስከ ትናንት ምንም አይነት የተረጋገጠ በሽተኛ ሳይኖራቸው የቆዩት ኤርትራና ኡጋንዳ ትናንት በአገራቸው የመጀመሪያዎቹን የኮሮናቫይረስ ታማሚዎች ማግኘታቸውን አስታውቀዋል።

    የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረ መስቀል በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ የአገሪቱን ጤና ሚኒስቴር ጠቅሰው እንዳስታወቁት የመጀመሪያ በሽታው የተገኘበት ግለሰብ ከኖርዌይ በዱባይ በኩል ወደ አሥመራ የገባ ነዋሪነቱ ኖርዌይ የሆነ የ39 ዓመት ኤርትራዊ ነው።

    ኡጋንዳም የመጀመሪያውን ቫይረሱ የተገኘበትን ታማሚ ማግኘቷን ቅዳሜ ያሳወቀች ሲሆን ግለሰቡ የ36 ዓመት ጎልማሳና ከዱባይ ወደ ኡጋንዳ መምጣቱ ተገልጿል።

    ይህንንመ ተከትሎ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሳቬኒ ዓለም አቀፍ በረራዎችን ማገድና ከጭነት ተሽከርካሪዎች ውጪ በድንበር በኩል ወደ ግዛቷ መግባትን ከልክላለች።

    View more on twitter
  10. ሁለት ተጨማሪ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ተገኙ

    ሰበር ዜና

    በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጠ ተጨማሪ ሁለት ሰዎች መገኘታቸውን የአገሪቱ የጤና ባለስልጣናት አስታወቁ፤ በዚህም የህሙማኑ ቁጥር አስራ አንድ ደርሷል።

    በሽታው የተገኘባቸው እነዚህ ግለሰቦች ኢትዮጵያዊያን ሲሆኑ ሁለቱም ከውጪ አገራት የገቡ መሆናቸው ተገልጿል። አንደኛው የ28 ዓመት ወጣት ሲሆን ከቤልጂየም ወደ ኢትዮጵያ የመጣ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የ34 ዓመት ዕድሜ ጎልማሳና ከዱባይ ወደ አዲስ አበባ የገባ መሆኑ ተጠቁሟል።

    የሁለቱን ግለሰቦች ጨምሮ ቀደም ሲል የታወቁት ስምንቱ ታማሚዎች በጥሩ የጤንነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ያለመከተው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የ85 ዓመቷ ታማሚ ግን ከባድ የሚባል እንዳጋጠማቸውና ህክምናና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጿል።

    እስካሁን በሽታው እንዳለባቸው ከተረጋገጡት ሰዎች 4ቱ ጃፓናዊያን፣ 5ቱ ኢትዮጵያዊያን፣ 1ዷ እንግሊዛዊት እና 1ዱ ኦስትሪያዊ ናቸው።

    ከዛሬ ዕኩለሌሊት ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ሰዎች በተዘጋጁ የለይቶ ማቆያ ሆቴሎች ውስጥ ለሁለት ሳምንታት እንዲቆዩ የሚያስገድደው ትዕዛዝ ተግባራዊ ይሆናል።

  11. በጣሊያኗ ሎምባርዲ ግዛት የሰዎችን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ወታደሮች ተሰማሩ

    በጣሊያን ኮሮናቫይረስ የተቀሰቀሰባትና በቫይረሱ ክፉኛ እየተፈተነች ያለችው የሎምባርዲ ክልል ነዋሪዎች ከቤታቸው በምንም ምክንያት መውጣት እንደማይችሉ አስታወቀች።

    ሳምንታዊ የጎዳና ላይ ሰፋፊ ገበያዎችም ታግደዋል።

    ግዛቲቱ ትናንት ከሰዓት በኋላ ያወጣችው መመሪያ ነዋሪዎች ለግል ስፖርታዊ እንቅስቃሴም ሆነ ለአካል ብቃት ከቤታቸው ወጣ ማለትን ይከለክላል።

    ይህ ክልከላ በትናንትናው ዕለት ብቻ ጣልያን 800 የሚሆኑ ሰዎችን በኮሮናቫይረስ ማጣትዋን ተከትሎ ነው።

    በአገሪቱ በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 4825 በመድረስ የዓለም ከፍተኛው የኮሮናቫይረስ ሞት ሆኖ ተመዝግቧል።

    ጥብቅ መመሪያ በማውጣት ሰዎች ከቤት እንዳይወጡ ጎዳናዎቿ ላይ ወታደሮች ያሰማራችው የሎምባርዲ ከዚህ ሞት 3095 የሚሆነው የተመዘገባት የጣልያን ክልል ነች። ተጨማሪ ለማንበብ በኮሮናቫይረስ እየተናጠኝ ያለችው የጣሊያኗ ሎምባርዲ ግዛት ጥብቅ እገዳ ጣለች

    ወታደሮች
  12. ከዛሬ ሌሊት ስድስት ሠዓት ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ሰዎች ወደ ለይቶ ማቆያ ይገባሉ

    የኢትዮጵያ አውሮፕላን

    መንግሥት አርብ ዕለት ይፋ ባደረገው ውሳኔ መሰረት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ማናቸውም መንገደኞች ለ14 ቀናት ወደ በለይቶ ማቆያ እንዲገቡ የሚደረገው ከዛሬ ዕከለ ሌሊት ጀምሮ ነው።

    በዚህም መሰረት ከማናቸውም ከውጭ አገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ መንገደኞች በሆቴል ውስጥ ተለይተው ለ14 ቀናት እንዲያቆዩ የሚያስገድደው ውሳኔ ተግባራዊ መሆን ይጀምራል።

    በመሆኑም ከዕሁድ እኩለ ሌሊት ጀምሮ የሚገቡ ሁሉም መንገደኞች በስካይ ላይት ወይም በጊዮን ሆቴል ለ14 ቀናት በራሳቸው ወጪ ተለይተው ይቆያሉ ተብሏል።

    እንዲሁም ዲፕሎማቶች አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ በየአገራቸው ኤምባሲዎች እራሳቸውን ለ14 ቀናት ለይተው ይቆያሉ።

    የትራንዚት በረራ መንገደኞችም የትራንዚት በረራቸውን እስኪያገኙ ድረስ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት በሆነው በስካይ ላይት ሆቴል ተለይተው ይቆያሉ።