"ከማይግሪን የተፈወስኩት በበገና ድምጽ ነው"

ጀረሚ ቼቭሪየር

የፎቶው ባለመብት, Jeremy

የምስሉ መግለጫ, ጀረሚ ቼቭሪየር

ጀረሚ ቼቭሪየር ነጭ አሜሪካዊ ነው። ተወልዶ ያደገው ኒው ዮርክ ሲሆን የሕይወቱን ገሚስ ያሳለፈው በመንፈሳዊ ምሥጢራዊ ጥያቄዎች ውስጥ እየተንከላወሰ ነው።

ከልጅነቱ ጀምሮ አእምሮውን ሲቀውሩት ለነበሩ ለነዚህ ዘላለማዊ፣ ሰዋዊ፣ መንፈሳዊና ሁለተንተናዊ ጥያቄዎች ምላሽ ካገኘሁ በሚል በቀለም ጎዳና ሞክሯል።

ቦስተን ዩኒቨርስቲ ገብቶ ፍልስፍናን ከሥነ ልቡና ጋር አዋ'ዶ ተምሯል።

የዓለም ሃይማኖቶች ንጽጽርን የተመለከቱ ክፍለ ትምህርቶችን ቀስሟል፤ መርምሯል።

ከቀለሙ ጎን ለጎን ለዕለታዊ የሥርዓተ ጥሞና (Meditation) ብዙ ጊዜውን ይሰጥ ነበር።

ለሁለንተናዊ ጥያቄዎች ምላሽ ፍለጋ ሩቅ ምሥራቁንም፣ ቅርብ ምዕራቡን አስሷል።

"'ከየት መጣሁ? ለምን መጣሁ? ምድር ምንድን ናት? ሕይወትና ሞት ምንና ምን ናቸው?' እያልኩ ስጠይቅ ነው የኖርኩት።" ይላል።

አሁንም ጥያቄው እንደቀጠለ ነው። ድሮስ ይህ ጥያቄ ለቢሊዮን ዓመታት መቼ አባርቶ ያውቅና።

ሆኖም ጀረሚ ወደ አፍሪካ ከመጣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አንድ ነገር ቀልቡን ፋታ ሰጥቶታል።

በገና!

ጀረሚ ምዕራብ አፍሪካካን አስሷል። ወደ ሰሜን ማሊ ተጉዞ በባማኮ ኖሯል። ደቡብ ወርዷል። መንፈሱ በጉዞ ብዛት ምላሽ ታገኝ ይመስል።

"በአፍሪካ የሰው ለሰው ቅርርብ ማረከኝ፣ ለቁስ የሚሰጠው ያነሰ ቦታ ሳበኝ፣ ባለህ መደሰት እንደሚቻል አስተማረኝ" ይላል።

ነፍሱ ግን ከጉዞ አላረፈችም።

በተስተመጨረሻ ወደ ምሥራቅ አፍሪካ፣ በተለይም ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ግን ትንሽ እፎይታን አገኘ፤ በበገና።

አሁን ጀረሚ መኖርያ ቤት ብትሄዱ መኖርያው በአራት ይከፈላል። ሳሎን፣ መኝታና ማዕድ ቤት።

አራተኛዋ ክፍል ግን ምሥጢር ናት።

ይቺ ምሥጢራዊ እልፍኝ 'የበገና ቤት' ይላታል። መላ ቤተሰቡ ቅዱስት አድርጎ ነው የሚቆጥራት።

ሌሊት ሌሊት እየተነሳ ወደዚያች ክፍል ይዘልቅና በገና ይደረድራል። እሱ ከሌለ ደግሞ ሴራሊዮናዊቷ ባለቤቱ በገና ትደረድራለች።

"የበገና ንዝረት ነፍሴ ድረስ ዘልቆ ይሰማኛል" የሚለውም ለዚህ ነው።

"ቀና ልብ ካለህ በገና ይገራልሃል"

ጀረሚ ከበገና ጋር በፍቅር ከወደቀ ረዥም ጊዜ አልሆነውም።

በአንድ ዕውቅ ኢትዮጵያዊ አርቲስት አማካኝነት ከአንድ ወጣት የበገና መምህር ጋር ተዋወቀ።

መምህሩ በዚህ ሐተታ ማሳረጊያ ታሪኩን የሚተርክልን መምህር ኤርሚያስ የሚባል ሰው ነው።

ጀረሚ የዚህን መሣሪያ ምሥጢር ለመረዳት ተጣጥቦ ወደ መምህር ኤርሚያስ ቀረበ።

ምንም ነገር ሳይሆን "ቀና ልብና ጥልቅ ጉጉት" ይዤ ነው በገና ያነሳሁት ይላል።

ጣቶቹን ወደ በገና ክሮች ባሳረፈ ቅጽበት ነበር ስሜቱ መናወጥ የጀመረው።

መምህር ኤርሚያስ ጀረሚን "ሁልጊዜም የበለጠ ለማወቅ ጉጉት የማይበት ብርቁ ተማሪዬ ነው" ይለዋል።

አሜሪካዊው ጀረሚ፣ "ሕይወቴን ሙሉ ብዙ መንፈሳዊ ፍተሻ አድርጊያለሁ፤ ምሥራቃዊ ጥሞናንም ዘልቄበታለሁ። ለነፍሴ ቅርብ የሆነልኝ ግን በገና ነው" ይላል።

ቀደም ባለው ጊዜ ጀረሚ በቀን ለሦስት ሰዓታት ያህል በጥልቅ ጥሞና ውስጥ ይቆይ ነበር። በተለይ በዮጋና ሜዲቴሽን የምስጠት ሥርዓት ውስጥ።

ይሁንና በገና ስደረድር ነፍሴ ድረስ ዘልቆ የሚሰማኝ አንዳች ነገር አለ ይላል።

ለጀረሚ ያ የሚነዝረው የበገና ድምጽ ዝም ብሎ ድምጽ አይደለም።

"ነገሩ እንዲገለጥልህ ልበ ቀናነት ይሻ ይሆናል። በበጎ መንፈስ ልትማረው ይገባ ይሆናል፣ ብቻ እኔ'ንጃ።"

እንደሱ አገላለጽ በገና ደርዳሪውን ብቻ አይደለም ከዓለማዊ የስሜት ወጀብ የሚፈውሰው። አዳማጩም ከበረከቱ ተጋሪ ነው።

ጀረሚ፣ 'በጉዳዩ ላይ ሊቅ አይደለሁም፣ ነገር ግን በገና ከመንፈሳዊ ገጽታው ባሻገር ሳይንሳዊ ገጽታ እንዳለው እረዳለሁ' ይላል።

በተለይም የፊዚክስ ንዝረተ ድምጽ የፈውስ አቅም እንዳለው እንደሚታመን፣ በገናም ንዝረቱ በጆሮ ተንቆርቁሮ ወደ ነፍስ ሲሄድ ነፍስን በቂቤ የመታሸት ያህል እፎይታን እንደሚሰጠው ያብራራል።

"በኳንተም ፊዚክስ ሁሉም ነገር ንዝረት ነው ይላሉ። በበገና በንዝረቶች ውስጥ ከሰውነታችን አንዳች ነውጥ ቀስ እያለ ሲሰክን ነው የሚሰማኝ።"

በአእምሮ ውስጥ የስክነት ጅረት ከአንድ የሰውነት ክፍል ወደ ሌላው ሲፈስም ይሰማል።

ጀረሚ ነጭ አሜሪካዊ እንደመሆኑ 2 ሜትር በገና ተሸክሞ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ዘምበል ደፋ ሲል ሐበሾች ምን ይሉት ይሆን?

"What! You play Begena? [እንዴ! በገና ትደረድራለህ?] ይሉኛል፤ እነሱ የሚደነቁበት ደረጃ እኔኑ መልሶ ያስደንቀኛል" ይላል።

የአገሩ ሰዎች (ፈረንጅ ወዳጆቹ) ደግሞ ስለነገሩ ለማወቅ ይበልጥ ይጓጓሉ።

"ወደፊት በገና ለምዕራቡ ዓለም መንፈሳዊ እድሳት (Spritual awakening) ሊሰጥ የሚችል መሣሪያ ሆኖ ይሰማኛል። ቢያንስ አንድ መነሻ ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ" የሚለው ለዚሁ ነው።

ለዚህ እንደማጠናከሪያ የሚያነሳው ፋታ የሌለውን የከተሜነት ሕይወትን በማሰብ ነው።

"የምዕራቡ ዓለም ሕይወት በውክቢያ የተሞላች ነች። የነፍስ ስክነት ውዱና ተፈላጊው ጉዳይ ሆኗል። በገና ለዚህ ሁነኛው መድኃኒት አይሆንም ትላለህ?"

ጀረሚ ቼቭሪየር

የፎቶው ባለመብት, Jeremy

"ምርኩዝ ይዤ እስከምሄድ ከበገና አልለይም"

የሁለንተና ምሥጢርና አማሎሽ (Mysticism) ከልጅነቱ ጀምሮ ሲያንከራትተው የነበረው ጀረሚ ከዚህ ወዲያ ከበገና ጋር የሚለየው ምድራዊ ኃይል እንደሌለ ነው ደጋግሞ የሚገልጸው።

"በገና ውስጥ ያገኘሁትን ሰላም እኔ ነኝ የማውቀው። እውነቴን ነው የምልህ፣ ከዚህ ወዲህ በምርኩዝ እስከምሄድ ድረስ በገና መደርደርን አላቆምም።"

ለዚህ የነፍስ ከፍታ ያበቃውን ሰው ደጋግሞ ያመሰግናል። መምህር ኤርሚያስን። መምህር ኤርሚያስ ማን ነው?

በገናን በዙም (zoom) መደርደር ይቻላል?

መምህር ኤርሚያስ የኬብሮን የዜማ መሣሪያዎች ማሰልጠኛ ተቋም ባለቤትና መሥራች ናቸው።

'ናቸው' ከምንል ግን 'ነው' ብንል ይቀላል። በገና ደርዳሪነት ወደ አንቱታነት ካልወሰደው በቀር።

ገና በ18 ዓመቱ ነው ይህን ተቋም የመሠረተው። መምህር ኤርሚያስ አሁን ገና 21 አልደፈነም።

ለበገና ድርደራም፣ ተቋም ለመመሥረትም ይህ ዕድሜ ለጋ ይመስላል።

"ከበረቱ ምንም ነገር እንደሚቻል የተማርኩት ከበገና ነው" የሚለው ያለ ምክንያት አይደለም።

በገና እንዴት ብርታት እንደሆነው ኋላ ራሱ መጥቶ በአንደበቱ ያስረዳናል።

በጊዜ ለዚህ የተረጋጋ ሕይወት በመብቃቱ ግን ወላጆቹን ከወዲሁ ያመሰግናል።

ድሮ ልጅ ሳለ የመጀመርያውን በገና የገዙለት ወላጆቹ ነበሩ።

ወላጆቹን ብቻ ሳይሆን የበገና አባቶችንም ጭምር ለማክበር፣ ለመዘከር በብሔራዊ ቴአትር ዓመታዊ መርሐ ግብር ያሰናዳል።

"ዝክረ በገና" ይሰኛል መሰናዶው።

መምህር ኤርሚያስ የበገና አባቶች፣ የሚገባቸውን ክብር ሳያገኙ ነው ያለፉት ብሎ ያምናል።

እነሱንም ለማመስገን፣ በዚያውም የእሱን በገና ባዕድ የሆነውን ትውልድ ደግሞ ለማንቃት ነው ይህን መርሐ ግብር ሥራዬ ብሎ የሚያሰናዳው።

እሱ አሁን ሰመረላቸው ከሚባሉ ወጣት የበገና ደርዳሪዎች አንዱ ነው።

በኬብሮን ትምህርት ቤቱ ውስጥ ከሕጻናት እስከ አዋቂዎች፣ ከአገሬው እስከ ውጭ ዜጎች የበገና ደርዳሪ ተማሪዎች አሉት።

የቤት ለቤት የበገና ትምህርትም ይሰጣል።

"ከተማሪዎቼ በዕድሜ ትንሿ 5 ዓመቷ ነው። በዕድሜ ትልቁ ደግሞ 80 ዓመታቸው ነው" ሲለን እንዴት ሆኖ ማለታችን አልቀረም።

እንዴት ነው የ5 ዓመት ልጅ በገና የምትደረድረው?

የእሷ ቁመትና ባለ 2 ሜትሩ በገና የት ተገናኝተው?!

"ወላጆች ከጊታር በገናን ቢያስቀድሙ"

ብዙ ዘመናይ ወላጆች የልጆቻቸውን ያልጠኑ ጣቶችን ፒያኖ ቁልፎች ላይ ይጥዳሉ።

ከትከሻቸው ቶሎ ጊታር ያኖራሉ።

ጥቂት ወላጆች ደግሞ ልጆቻቸውን በገና ያስተምራሉ።

እንደነገርኳችሁ መምህር ኤርሚያስ ገና የ5 ዓመት የበገና ተማሪ አለችው። ዜማ ትባላለች።

ጣቶቿ እንዴት ይታዘዙላት እንደሆን እንጃ እንጂ እሱ አያያዟ ይበል የሚያሰኝ ነው ይላል።

ለመምህር ኤርሚያስ የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ወላጅ ወደ ምዕራብ አገራት የሙዚቃ መሣሪያዎች በአያሌው መሳብ ብዙ አይደንቀውም።

ቲቪዎቻችንን የሞላው ምን ሆነና? ይላል። ዘመናይ የሚባሉ መሣሪዎች የሰው አእምሮ ላይ ዘልቀዋል። "ዘመናዊነት መገለጫ አድርገን እንድናስበው ተደርገናል፤ አይፈረድብንም" ይላል።

ሆኖም ግን ከእነሱ መሣሪያዎች ይልቅ በበገና ውስጥ አያሌ ትሩፋቶች እንዳሉ ማስገንዘብን ይወዳል።

"እኔ ከማንኛውም መሣሪያ ጋር ጠብ የለኝም። ነገር ግን ወላጆች ወደ በገና ቢሳቡ ልጆቻቸው የዜማ መሣሪያ ብቻ አይደለም የሚማሩላቸው። ግብረ ገብም፣ መንፈሳዊነትም፣ ሥነ ምግባርም ጭምር ነው እንጂ" ይላል።

ኤርሚያስ በገና ሲደረድር

የፎቶው ባለመብት, Ermias

የምስሉ መግለጫ, ኤርሚያስ በገና ሲደረድር

'ዳያስፖራ' የበገና ተማሪዎች

የመምህር ኤርሚያስ ተማሪዎች አገር ቤት ብቻ አይደሉም ታዲያ።

የኑሮ ነገር ሆኖ በየዓለማቱ የተበተኑ ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎችንም ያስተምራል።

"ይህ ሊሆን ይቻለዋልን?" ያላችሁ እንደኹ በዘመናዊው የኢንተርኔት የቪዲዮ ግንኙነት የዙም (zoom) መተግበሪያ ታግዞ ይሆናል መልሱ።

እንዲሁ ላይ ላዩን ሲታይ በገናን በዙም (zoom) ማስተማር፣ ዋናን በርቀት ትምህርት ከመማር ጋር መሳ ይመስላል።

"ቀላል ነው አልልህም፤ ነገር ግን ይህ የተሞከረና የሚቻል ነው። ጥልቅ ፍላጎትን ርቀት አይገድበውም" ይላል መምህሩ።

በዱባይ፣ በጀርመን እና በተለያዩ የአሜሪካ ክፍለ ግዛቶች የዙም በገና ተማሪዎች አሉት። ኬብሮን በገናን አምርቶ ወደ ውጭ መላክ ብቻ ሳይሆን በርቀት ያስተምራልም።

ከኢትዮጵያዊያን ሌላ በርካታ የውጭ ዜጎችም ለበገና ጥልቅ ፍቅር እንዳላቸው ይመሰክራል።

ቤቱ ድረስ አንኳኩተው አስተምረን የሚሉት የውጭ ዜጎች ጥቂት አይደሉም።

ከአለባበስ ጀምሮ ትምህርቱ የሚፈልገውን መንፈሳዊነት እና ግብረ ገባዊ መስፈርቶች ማሟላት የግድ ስለሆነ ግን ጥቂቶችን ብቻ ተቀብሎ ያስተምራል።

በዚህ አጭር ቆይታ ጀርመኖችን፣ እንግሊዞችን፣ አሜሪካዊያንን ጭምር አስተምሯል።

መምህር ኤርሚየስ እንደሚለው ከሆነ ፈንጆቹ አንድ ጊዜ መማር ከጀመሩ የሚያቆማቸው ኃይል የለም። ነገሩ የእኛን ከእኛ በላይ እነሱ ዋጋ ይሰጡታል ለማለት ነው።

ትጋታቸውም ሁልጊዜ ይገርመዋል።

ከላይ ታሪኩን የነገረን አሜሪካዊው ጀረሚ ለዚህ በዋቢነት ያነሳል።

"…አንድ ቀን ስለ ጥንታዊ የበገና አባቶች ታሪክ ነገርኩት። ሌሊት 9፡00 ሰዓት ላይ በተመሳሳይ ሰዓት ነቅተው በገና ይደረድሩ እንደነበረ ተረኩለት። ያን ጊዜ ተአምራት ይገለጥላቸው እንደነበረ አወሳኹለት። ከዚያ በኋላ እሱም ሌሊት እየተነሳ በገና ይደረድራል። የሆነ ቀን መጣና፣ 'መምህር ሆይ! እውነትህን ነው፤ ሌሊት ሌሊት እኮ የበገናው ድምጽ ሁሉ ይለያል' አለኝ።"

በበገና ግርፍ መመረቅ እንዴት ያለ ነው?

የበገና ትምህት ቀላልም፣ ከባድም ነው ይላል መምህሩ። ለወደደውና ቅን ለሆነ ሰው ይገራለታል።

በበገና ግርፍ፣ 10 አውታር እንዴት እንደሚደረደር ብቻ ሳይሆን የበገና መሣሪያ አሠራር ጥበብ ራሱ የፍኖተ ትምህርቱ አካል ነው።

በበገና አንድ ሰው የሚመረቀው መቼ ነው? በቃ የሚባለውስ? ለሚለው ጥያቄ፣ መምህር ኤርሚያስ 'በገናን ተምሬ ጨረስኩ አይባልም' ይላል።

"የበገና አባት ቅዱስ ዳዊት ነው። በገናን መጨረስ ማለት ቅዱስ ዳዊትን መሆን ነው ብዬ አስባለሁ።"

ሆኖም መሠረታዊ ዕውቀት መጨበጥ ይቻላል። በ2 ዓመት ውስጥ።

የሚደንቀው ታዲያ፣ በበገና ትምህርት ጣት የማፍታታት ኮርስ አለ። ጣትን ለበገና ዝግጁ ለማድረግ ብቻ ድፍን አንድ ወር ይወስዳል።

"ከማይግሬን የተፈወስኩት በበገና ድምጽ ነው"

ወጣቱ መምህር ኤርሚያስ ከበገና ጋር የተዋወቀው እጅግ አስቸጋሪው ዕድሜ ላይ ሳለ እንደነበር ከላይ አውስተናል።

ጉርምስናን በገና እንደገራለት እሱም አበክሮ ያምናል። የጉርምስና ፈተናዎችን ብቻም ሳይሆን ጤናንም የተጎናጸፍኩት በበገና ድምጽ ነው ሲል ያስደምመናል።

ከዚህ ወዲያ የእሱን ታሪክ በስማ በለው ከምንነግራችሁ እሱው ታሪኩን ቢደረድርላችሁ አይሻልም? የተዋጣለት በገና ደርዳሪ ወጣት መሆኑን ሳንዘነጋ።

"አዲስ አበባ ነው ተወልጄ ያደኩት። በሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪ እያለሁ ወደ በገና ትምህርት በነጻ የመማር ዕድል አገኘሁ። ሳላስበው በፍቅሩ ወደቅ

በቀን እስከ 8፡00 ሰዓት ያህል እለማመድ ነበር። ከጊዜ በኋላ ከበገና ራሴን መለየት አቃተኝ። ሱስ ሆነብኝ።

በገናን መማር በጀመርኩ በ5 ወሩ ሌሎች ተማሪዎችን አስተምር ተባልኩ። በተለያዩ የዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች እየሄድኩ ማስተማር ጀመርኩ።

በገና ደርድሬ ስነሳ አእምሮዬ በጣም ንቁ ይሆናል። የበገናው ድምጽ እየጣፈጠ እያማረ ይመጣል። በበገና አለመመሰጥ አይቻልም። ከበገና መለየት ያቃተኝ።

በሕይወቴ ብዙ ነገር ማሳካት እንደምችል ማመን የቻልኩትም ከበገና በኋላ ነው።

ወላጆቼ ጠዋት ሥራ ሲሄዱ ከበገናው ጋር ነኝ። ማታ ሲመጡ ከበገና ጋር ነኝ። ነገሩ ሳያሳስባቸው የቀረ አይመስለኝም። ግን ደግሞ እኔ ላይ እምነትም ነበራቸው።

ስለ በገና ሰው ቢያውቅ ደስ የሚለኝ ትልቅ ምሥጢር ያለበት መሣሪያ መሆኑን ነው።

ከራሴ ከኖርኩት፣ ካየኹት ልመስክር?

ሰው ከራሱ ከተግባባ ሌላ ተጓዳኝ በሽታዎች ይኖሩበታል ብዬ አላስብም።

ሰው ለተፈጥሮ ደግ የሆነ ፍጡር ከሆነ ብዙ ችግሮች ወደርሱ አይመጡም።

ተፈጥሮን ሲያዛባ ተፈጥሮም እሱ ላይ ትዛባለች።

አንድ ሰው ሌላውን መውደድን ሲያቆም መጀመሪያ የራሱ ሰውነት ራሱን መክዳት ይጀምራል።

እውነቱን ልንገርህ፣ ድሮ ማይግሬን ነበረብኝ፤ ከበገና ወዲህ ግን ታምሜ አላውቅም። የከፋ በሽታ አሞኝ አያውቅም። ባለኝ መረዳት በገና ፈውሶኛል።

ብዙ ስም ላንተ መግለጽ አልችልም እንጂ የአእምሮ መረበሽ የነበረባቸው ሰዎች፣ ሲታወኩ የነበሩ ሰዎች በገና እንዲደረደርላቸው፣ ከቻሉም እንዲደረድሩ ጭምር በማድረግ ሰላማዊ እንቅልፍ እንዲያገኙ ሆነዋል። የኔን መረዳት ነው የምነግርህ። የበገና ምሥጢር ከምልህ በላይ ጥልቅ ነው።"