የመቀሌ የሰሞኑ ውሎ

የመቀሌ ከተማ

የትግራይ ክልልና የፌደራል መንግሥት ወታደራዊ ግጭት ውስጥ ከገቡ ሶስተኛ ቀናቸውን አስቆጥረዋል። ግጭቱን ተከትሎ በመቀሌ ከተማና በክልሉ ተቋርጦ የነበረው የኤሌክትሪክና የትራንስፖርት አገልግሎት ተጀምሯል።

የኤሌክትሪክ አገልግሎት ትናንት ጥቅምት 26/2013 ዓ.ም የተመለሰ ሲሆን የትራንስፖርት አገልግሎት ደግሞ በዛሬው ዕለት ጥቅምት 27/2013 ዓ.ም መጀመሩን የመቀሌ የቢቢሲ ዘጋቢ ገልጿል።

ምንም እንኳን ትራንስፖርት ቢጀመርም ከመቀሌ ከተማ ወደተለያዩ ክፍሎች የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች በሙሉ ከከተማው ፖሊስ ልዩ ፍቃድ ያስፈልጋቸዋል ተብሏል።

ግጭቱን ተከትሎ የተቋረጠው የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት አሁንም እንደተቋረጠ ነው።

ከቀናት በፊት ተኩስ የተሰማባት የመቀሌ ከተማ በአንፃራዊ ሁኔታ የተረጋጋ ሁኔታ ላይ ብትገኝም ማህበረሰቡ ግን ጦርነቱ በፈጠረው ውጅንብር ስጋት ላይ መሆኑንም የቢቢሲ ዘጋቢ ይናገራል።

በትናንትናው እለት በመቀሌ ከተማ የጦር አውሮፕላን ሲያንዣብብ የነበረ መሆኑን የታዘበው የቢቢሲ ዘጋቢ በድምፁም በርካቶች መደናገጥና ፍራቻ ውስጥ እንደገቡ አክሎ ገልጿል።

በዛሬው ዕለት ነዋሪው የእለት ተእለት ኑሮውን የተመለሰ ይመስላል።

በከተማዋ ውስጥ ያሉ ባንኮችም ዝግ ሲሆኑ ነዋሪው ከትናንት በተሻለ ሁኔታ ከተማዋ ውስጥ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ታዝቧል።

ከዚህም በተጨማሪ መቀሌ የሚገኙ የንግድ ተቋማትና የገበያ ማዕከላትም አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ ብሏል።

የአማራን ክልል በሚያዋስነው የምዕራብ ትግራይ ድንበር በኩል ግጭቶች እንዳሉና ውጊያው መቀጠሉን የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት ደብረፅዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) በትናንትናው ዕለት ገልፀዋል።

የአማራ ልዩ ኃይልና የፌደራል ሰራዊቱ በጥምረት በመሆን የትግራይ ኃይል ጋር መዋጋታቸውን ተናግረዋል።

የመቀሌ ከተማ

በዛሬውም እለት በምዕራብ ትግራይ በኩል ጦርነቱ የቀጠለ መሆኑ መረጃዎች የወጡ ቢሆንም የፌደራል መንግሥቱም ሆነ የትግራይ ክልል ዝርዝር መረጃዎችን ከመስጠት ተቆጥበዋል።

በአሁኑ ወቅት ወቅት በከተማዋ አንዳንድ የነዳጅ ማደያ ጣብያዎች አገልግሎት እየሰጡ ቢሆንም በከተማዋ የቤንዚን እጥረት መኖሩም ተገልጿል።

የመማር ማስተማር ሂደቱን ለመታዘብ የሞከረው የቢቢሲ ዘጋቢ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት የስምንተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና እንዲወስዱ የሚጠብቁ ተማሪዎች በአፄ ዮሃንስ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ቀጥለዋል።

ግጭቱ ከመጀመሩ በፊት በትምህርት ገበታቸው ላይ የነበሩት የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ግን ትምህርታቸው እንደተቋረጠም ዘጋቢያችን ያገኘው መረጃ ያስረዳል።

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሻከረ የመጣው የፌደራልና የትግራይ ክልል መንግሥት ግንኙነት የማይታረቅ ደረጃ ደርሶ ከቀናት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ህወሃት በትግራይ የሚገኘው የመከላካያ ካምፕ ላይ ጥቃት ማድረሱን ገልፀው ጦርነት መከፈቱን አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው የመከላከያ ሠራዊት በኮማንድ ፖስት እየተመራ "ሀገሩን የማዳን ተልዕኮውን እንዲወጣ ትእዛዝ ተሰጥቶታል" ብለዋል።

የትግራይ ክልል በበኩሉ በክልሉ የሚገኙት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰሜን ዕዝ ሰራዊት አባላትና አዛዦች ከትግራይ ክልል መንግሥት ጎን ለመሰለፍ ወስነዋል ብሏል።