Got a TV Licence?

You need one to watch live TV on any channel or device, and BBC programmes on iPlayer. It’s the law.

Find out more
I don’t have a TV Licence.

ቀጥታ ዘገባ

የተጠቀሱት ሰዓቶቸ የዩናይትድ ኪንግደም ናቸዉ

  1. በአፍሪካ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር 104 ሺህ 279 ደረሰ

    ማስክ አድርጎ ስልክ የሚያወራ ግለሰብ

    የአፍሪካ ህብረት የበሽታዎች መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው በ55ቱ የአፍሪካ ሃገራት እስካሁን 104ሺህ 279 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን ፤3ሺህ 185 ሰዎች በቫይረሱ ሞተዋል፡፡ 41ሺህ 717 ሰዎች ደግሞ ከበሽታው አገግመዋል፡፡

    • ደቡብ አፍሪካ፡ ደቡብ አፍሪካ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የጣለቻቸውን ገደቦች እያላላች ሲሆን በሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ 3ኛ ደረጃ ላይ ያስቀመጠችውን የእንቅስቃሴ ገደብ ወደ ማንሳት እንደምትሻገር አሳውቃለች፡፡ ውሳኔው ተግባራዊ ከሆነም የ7ኛ እና የ12 ክፍል ተማሪዎች ትምህርት ቤቶች ይከፈታሉ፡፡ አንዳንድ የንግድ ተቋማትም ወደ ስራ ይገባሉ፡፡
    • ናይጄሪያ፡ በርካታ የእስልምና እምነት ተከታዮች በሚኖሩባትት ናይጄሪያ፤የኢድ አልፈጥር በዓልን በቤታቸው ከቤተሰባቸው ጋር ብቻ እንዲያሳልፉ አዝዛለች፡፡ ሌሎች የአፍሪካ አገራትም ተመሳሳይ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
    • ሱዳን፡ የመንግስት ቃል አቀባይ የሆኑት ፋይሰል ሞሃመድ ሳለህ፤ ሰዎች የእንቅስቃሴ ገደቡን እየጣሱ ነው ሲሉ ይከሳሉ፡፡ቃል አቀባዩ ሕጉን የሚተላለፉ ሰዎች ላይ መንግሥት እርምጃ እንደሚወስድ ተናግረዋል፡፡ ፈቃድ ከሌላቸው ሰዎች በስተቀር ከግዛት ወደ ግዛት የሚደረግ እንቅስቃሴ አይፈቀድም፡፡
    • ዛምቢያ፡ የዛምቢያ የኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ከተረጋገጠ በኋላ ራሳቸውን እንዳገለሉ አስታውቀዋል፡፡ ሚኒስትሯ "ሁሉንም ጥንቃቄዎች ካደረኩ በኋላ ትናንት በኮሮናቫይረስ ተይዣለሁ" በማለት እስካሁን ግን የበሽታው ምልክቶች እንዳልታየባቸው ጠቅሰው በማህበራዊ ሚዲያ ላይ አስፍረዋል።
  2. የኮሮናቫይረስ ወረርሸኝና የኢድ አል ፈጥር አከባበር

    በቱርክም አስገዳጅ የቤት መቀመጥ ህግን ተከትሎ መስጊዶቹ በኢድ አል ፈጥርም ቀን ወና ሆነዋል። በኢስታንቡል ሱለይማን መስጊድ ኢማም የሆኑት ግለሰብም በኢድ አልፈጥር ቀን ብቻቸውን ፀሎት ለማድረግ ተገደዋል።
    Image caption: በቱርክም አስገዳጅ የቤት መቀመጥ ህግን ተከትሎ መስጊዶቹ በኢድ አልፈጥርም ቀን ወና ሆነዋል። በኢስታንቡል ሱለይማን መስጊድ ኢማም የሆኑት ግለሰብም በኢድ አል ፈጥር ቀን ብቻቸውን ፀሎት ለማድረግ ተገደዋል።

    በዛሬው ዕለት በመላው አለም በሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ የኢድ አል ፈጥር በዓል እየተከበረ ነው።

    የኢድ አልፈጥር በዓል በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ቅዱስ ተብሎ የሚጠራው የረመዳን ፆም ማብቂያንም አብስሯል።

    ለሰላሳ ቀናት ያህል ራሳቸውን ከምግብና ከውሃ አቅበው ያሳለፉ የእምነቱ ተከታዮችም የዛሬዋን እለት ከቤተሰብ፣ ከወዳጅ ዘመድ ጋር ተሰባስበው በምግብ፣ በጨዋታና ደስታ የሚያሳልፉበት ቀን ነበር።።

    ከዚህም በተጨማሪ ማልደው በመነሳትም ወደ መስጊዶች አቅንተው ፀሎታቸውንም ሆነ ስግደታቸውን የሚያቀርቡበት ቀን ቢሆንም ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ብዙዎች በዓሉን ለብቻችው በየቤታቸው ተከርችመው ለማሳለፍ ተገደዋል።

    የኮሮናቫይረስን መዛመት ለመከላከል ሳዑዲ አረቢያ አስገዳጅ የቤት መቀመጥ ህግ ያሳለፈች ሲሆን ለኢድ አልፈጥር በዓልም አላላም። በእስልምና አማኞች ዘንድ ቅዱስ ተብሎ በሚጠራውም መካ መስጊድ አንድ አማኝ  በዓሉን አስመልክቶ ለጠባቂዎቹ ጣፋጭ ሲያድሉ
    Image caption: የኮሮናቫይረስን መዛመት ለመከላከል ሳዑዲ አረቢያ አስገዳጅ የቤት መቀመጥ ህግ ያሳለፈች ሲሆን ለኢድ አል ፈጥር በዓልም ይህ መመሪያ አላላም። በእስልምና አማኞች ዘንድ ቅዱስ ተብሎ በሚጠራውም መካ መስጊድ አንድ አማኝ በዓሉን አስመልክቶ ለጠባቂዎቹ ጣፋጭ ሲያድሉ
    በአለም ላይ ከፍተኛ የእስልምና ተከታዮች ባሏት ኢንዶኔዥያም በኢድ አልፈጥር ቀን ጎዳናዎች ባዶ የሆኑ ሲሆን እነዚህ የኮሮናቫይረስን ህሙማን የሚንከባከቡ የጤና ባለሙያዎች በተቻለ መጠን በስራም ቢሆን በዓሉን ለማክበር እየሞከሩ ነው።
    Image caption: በአለም ላይ ከፍተኛ የእስልምና ተከታዮች ባሏት ኢንዶኔዥያም በኢድ አልፈጥር ቀን ጎዳናዎች ባዶ የሆኑ ሲሆኑ ፤እነዚህ የኮሮናቫይረስን ህሙማን የሚንከባከቡ የጤና ባለሙያዎች በተቻለ መጠን በስራም ቢሆን በዓሉን ለማክበር እየሞከሩ ነው።
    በኬንያም ከኮሮናቫይረስ ጋር ተያይዞ ስብሰባ የተከለከለ በመሆኑ ኬንያውያንም በቤታቸው አጠገብ በዓሉን እንዲህ አክብረውታል።
    Image caption: በኬንያም ከኮሮናቫይረስ ጋር ተያይዞ ስብሰባ የተከለከለ በመሆኑ ኬንያውያንም በቤታቸው አጠገብ በዓሉን እንዲህ አክብረውታል።
  3. ሰበርበኢትዮጵያ በቫይረሱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው 88 ሰዎች ተመዘገቡ

    በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓታት በተደረገው 4048 የላብራቶሪ ምርመራዎች 88 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

    ከነዚህም መካከል 51 ወንዶችና 37 ሴቶች ሲሆኑ፤ 55ቱ የውጭ ሃገር የጉዞ ታሪክም ሆነ በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር የታወቀ ንክኪ የሌላቸው መሆኑን የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጋራ በሚያወጡት ዕለታዊ መግለጫ ተገልጿል።

    ህሙማኑ ከስምንት እስከ 75 የዕድሜ ክልል ላይ የሚገኙ ሲሆን 73ቱም ከአዲስ አበባ ናቸው።

    በአዲስ አበባ ከተገኙትም መካከል 19ቱ በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት ያላቸው፣ አንድ ግለሰብ የውጭ ሃገር የጉዞ ታሪክ ያለውና፤ 53 ደግሞ የጉዞም ሆነ በበሸታው ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ የሌላቸው መሆኑ ተገልጿል።

    ከዚህም በተጨማሪ በትግራይ ክልል ስምንት የውጭ ሃገር የጉዞ ታሪክ ያላቸው፣ አራት ከኦሮሚያ ክልል ሁለቱ የውጭ ሃገር የጉዞ ታሪክ ያላቸውና ሁለቱ ደግሞ የውጭ ሃገር የጉዞ ታሪክ እንዲሁም ከህመምተኞች ጋር ንክኪ የሌላቸው መሆኑም ተገልጿል።

    አንዲት በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት ያላት በሃረሪና ሁለት የውጭ ሃገር የጉዞ ታሪክ ያላቸው የድንበር ተሻጋሪ መኪና አሽከርካሪዎች መሆናቸውም መግለጫው ጠቁሟል።

    በሃገሪቱ በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 582 የደረሰ ሲሆን፤ 152ቱ አገግመዋል።

    በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር
  4. በሆንግኮንግ የተደረገ የተቃውሞ ሰልፍ

    ቻይና ያወጣችው አዲሱ የደህንነት ህግ "የሃገር ክህደት፣ መገንጠል፣ ስልጣንን መተላለፍ" በሆንግኮንግ ግዛት ውስጥ የሚከለክል ነው።በሳምንቱ መጀመሪያም አካባቢ የተለያዩ ኃገራት የፖለቲካ ልኂቃን የቻይናን ረቂቅ ህግ በመተቸት መግለጫ አውጥተዋል።ፖለቲከኞቹ "የከተማዋን የራስ አገዛዝ ነፃነት ከመጣስ በተጨማሪ ህግን የተላለፈ እንዲሁም መሰረታዊ ነፃነትንም የሚጋፋ ነው" ብለውታል።

    ተጨማሪ ያንብቡ
    next
  5. ታሊባንና የአፍጋኒስታን መንግሥት የኢድ በዓልን ምክንያት በማድረግ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ደረሱ

    የአፍጋኒስታን ሰራዊት

    በዛሬው ዕለት በመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረውን የኢድ አልፈጥር በዓል ምክንያት በማድረግ ታሊባንና የአፍጋኒስታን መንግሥት የሶስት ቀናት የተኩስ ማቆም ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

    ስምምነቱም ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል።

    የሃገሪቱ ፕሬዚዳንት አሽራፍ ጋኒ "ስምምነቱ ደስ የሚያሰኝ ነው" ብለው ሰራዊታቸው ተግባራዊ እንደሚያደርግም ቃል ገብተዋል።

    ከሰሞኑ በታሊባን ታጣቂዎችና በመንግሥት ሰራዊት መካከል ስትበጠበጥ በነበረችው አፍጋኒስታንም የሶስት ቀናት ተኩስ ማቆም ስምምነቱም ለወደፊቱ ሙሉ በሙሉ ጦርነቱ ሊቀር ይችላል የሚለውን ተስፋ የፈነጠቀ ነውም ተብሏል።

    ሆኖም ከሁለት አመታት በፊት እንዲሁ በኢድ አልፈጥር በዓል የሶስት ቀናት የተኩስ አቁም አዋጅ ስምምነት ላይ ተደርሶ አልተራዘመም።

    "በጠላቶቻችን ላይ ምንም አይነት ጥቃት እንዳትፈፅሙ። ጥቃት ከተፈፀመባችሁ ግን ራሳችሁን ተከላከሉ" በማለት የታሊባን ቃለ አቀባይ ዛቡላህ ሙጃሂድ በትናንትናው ዕለት ተናግረዋል።

    ቃለ አቀባዩ አክለውም የተኩስ አቁም ስምምነቱ ለኢድ አልፈጥር በዓል ብቻ የሚቆይ መሆኑንም ተናግረዋል።

    ፕሬዚዳንት አሽራፍ ጋኒ በበኩላቸው መንግሥት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንደሚወስድና የታሊባን እስረኞችም እንደሚለቀቁ አስታውቀዋል።

  6. ኒውዮርክ ታይምስ የፊት ገፁን በኮሮናቫይረስ ህይወታቸውን የተነጠቁ ሰዎችን ለመዘከር አዋለ

    በኮሮና ክፉኛ እየተመታች ባለችው አሜሪካ በመቶ ሺህ የሚጠጉ ዜጎቿን በኮሮናቫይረስ ተነጥቃለች።

    የአሜሪካው ኒውዮርክ ታይምስም ከሞቱት መካከል የአንድ ሺህ ሰዎችን ስም በፊት ገፁ በማውጣት እየዘከራቸው ነው።

    የሞቱት ሰዎች በአብዛኛው በቁጥር ብቻ የሚገለፁ ሲሆን፤ ስማቸውንም በመዘርዘር ከቁጥር በላይ ማንነት፣ የነገን ተስፋ የሰነቁ ሰዎች እንደነበሩም በማስታወስ ላይ ይገኛል።

    የጋዜጣው ርዕሰ ገፅም ከጥር ወር ጀምሮ በኮሮና ህይወታቸውን ያለፉትን ዜጎች "በመጠን የማይለካ ኪሳራ" ብሎታል።

    በአሜሪካ ውስጥ ካሉ ግዛቶች የቫይረሱ ማዕከል በሆነችው ኒውዮርክ 28 ሺህ ሰዎች በኮሮናቫይረስ እንዳጣች ከጆንስ ሆፕኪንስ የተገኘ መረጃ ያሳያል።

    በአለም ላይ በኮሮናቫይረስ በተያዙ ሰዎች ቁጥርም ሆነ በሟች ቀዳሚ በሆነችው አሜሪካ 97ሺህ ሰዎች በኮቪድ-19 ህይወታቸው አልፏል። በሟች ቁጥር አሜሪካን የምትከተለው ዩናይትድ ኪንግደምም 37ሺህ ዜጎቿን በኮቪድ-19 አጥታለች።

    ከዚህ ቀደምም ቢቢሲ አማርኛ በአሜሪካ ውስጥ ባሉ የተለያዩ ግዛቶች በኮሮናቫይረስ የሞቱ ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ አንድ ዘገባ የሰራ ሲሆን ይህንን ለማንበብ ቀጣዩን ማስፈንጠሪያ ይጫኑ፦ በኮሮናቫይረስ ከተቀጠፉ ኢትዮጵያውያን መካከል ጥቂቶቹ

    የኒውዮርክ ታይምስ የፊት ገፅ
  7. የውሃን ላብራቶሪ ኮቪድ-19 ከማዕከሉ እንዳልወጣ አስታወቀ

    የኮሮናቫይረስ ምርመራ በቻይና

    የቫይረሱ መነሻ ናት በምትባለው የቻይናዋ ውሃን ከተማ የሚገኘው በቫይረስ ላይ ምርምር የሚያደርገው ተቋም ዳይሬክተር ሶስት አይነት የኮሮናቫይረስ አይነቶች በሌሊት ወፍ ላይ በማዕከሉ ውስጥ ቢገኙም፤ በአሁኑ ሰዓት የአለም ስጋት ከሆነው ኮቪድ- 19 ጋር ግን አንድ አይነት አይደለም ብለዋል።

    ዳይሬክተሯ ዋንግ ያኒ ከሃገሪቱ ሚዲያ ሲጂቲኤን ጋር ባደረጉት ቃለ - መጠይቅ በአሁኑ ወቅት አለምን ያጥለቀለቀው የኮሮናቫይረስ እርሳቸው ከሚመሩት ተቋም ወጥቷል መባሉን አጣጥለውታል ።

    "ይሄ የተፈበረከ መረጃ ነው" ያሉት ዳይሬክተሯ "ተቋማችን ታህሳስ 20፣ 2012 ዓ.ም ያልታወቀ አይነት የሳንባ ምች ናሙና ደረሰን። ናሙናውን ከመረመርን በኋላ አዲስ አይነት ኮሮናቫይረስ እንደተያዘ ተረዳን። ከዚያ በፊትም ቫይረሱን በምርምራችን አላገኘነውም። በማዕከላችንም ውስጥ የዚህ አይነት ቫይረስ አልነበረም፤ አሁን ካለውም ጋር አይመሳሰልም" ብለዋል።

    የኮሮናቫይረስ መነሻ ውሃን በሚገኝ የእንስሳት እርድ ቦታ እንደሆነ በሰፊው የሚታመን ሲሆን፤ ከሌሊት ወፍም እንደመጣ ይነገራል።

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቫይረሱ ከቻይና ላብራቶሪዎች ድንገት አምልጦ የወጣ ነው፣ ቻይናም መረጃውን ለመሸፋፈን እየሞከረች ነው ሲሉ በተደጋጋሚ ይሰማል። ቻይና በበኩሏ ውንጀላውን ውድቅ አድርጋለች።

  8. Police officers

    በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ማግስት በእንግሊዝ ፖሊሶችና ቁልፍ ሰራተኞች ላይ የሚደረገው የምራቅ መትፋት ወንጀል አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ተገለፀ።

    ተጨማሪ ያንብቡ
    next
  9. ስፔን በወረርሽኙ ክፉኛ ከተጠቁ አገራት አንዷ ናት

    በስፔን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የአገሪቷ መንግሥት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር እየሰራ ያለውን ተግባር በመቃወም የተቃውሞ ሰልፍ አካሂደዋል፡፡

    ተጨማሪ ያንብቡ
    next
  10. በኒውዮርክ በቀን በቫይረሱ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ100 በታች ሆነ

    ኒው ዮርክ
    Image caption: በግዛቷ ባለፉት 24 ሰዓታት በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 84 ነው

    በአሜሪካ ኒውዮርክ ከጎርጎሳውያኑ መጋቢት ወር መጨረሻ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በኮሮናቫይረስ ሳቢያ በአንድ ቀን የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ100 በታች መሆኑ ተገልጿል።

    በግዛቷ ባለፉት 24 ሰዓታት በአጠቃላይ 84 ሰዎች የሞቱ ሲሆን የግዛቷ አስተዳዳሪ አንድሪው ኮሞ፤ ቀደም ብሎ ካለው ቀን ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛው ነው ብለዋል፡፡ ቀደም ብሎ ባለው ቀን በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 109 ነበር፡፡

    በቫይረሱ ክፉኛ በተጠቃችው ኒውዮርክ ወረርሽኙ ከፍተኛ ጣሪያ ላይ በደረሰበት የጎርጎሳውያኑ ሚያዚያ ወር በአንድ ቀን ከ1ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሕይወታቸውን ያጡ ነበር፡፡

    አስተዳዳሪው በሰጡት ዕለታዊ መግለጫ፤ " ቁጥሩ ከ100 በታች እንዲሆን እፈልግ ነበር፤ ይህ በሃዘን ለተጎዱት ለ84ቱ ቤተሰቦች መልካም ስሜት አይፈጥርም፤ ነገርግን የሟቾቹ ቁጥር መቀነስ ያለውን መልካም ለውጥ ያሳያል" ብለዋል፡፡

    ኮሞ አርብ ዕለት በሰጡት መግለጫ፤ የኒውዮርክ ከተማን ጨምሮ በየትኛውም የግዛቷ አካባቢ ህጉ በሚፈቅደው መሰረት እስከ አስር የሚደርሱ ሰዎች አንድ ላይ መሰባሰብ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡

    አስተዳዳሪው አክለውም "ከአስር ሰዎች ጋር መሆን የማያስፈልጋችሁ ከሆነ አታድርጉት" ብለዋል፡፡

    የበአሜሪካ ውስጥ ካሉ ግዛቶች ኒውዮርክ የወረርሽኙ ማዕከል የነበረች ሲሆን፤ እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ ከ28 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡

    አሜሪካ ከዓለማችን አገራት ከፍተኛው የሟቾች ቁጥር ያለባት አገር ናት፤ እስካሁንም 96 ሺህ ዜጎቿን በኮሮናቫይረስ አጥታለች።

    ዩናይትድ ኪንግደም ከ36 ሺህ በላይ ሰዎችን በቫይረሱ ያጣች ሲሆን አሜሪካን በመከተል በሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

  11. Mercy Juma

    የኬንያ መንግሥት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዘመን ቀብር እንዴት መፈፀም እንዳለበት ሕግ አውጥቷል። በዚህ ሕግ መሠረት ቀብር ላይ መገኘት የሚችሉት 15 ሰዎች ብቻ ናቸው። ሥነ-ሥርዓቱ አጠር ያለ ነበር። ሁሉም ነገር አጠር እንዲል ተደርጓል። ክሪስ የቤተክርስትያን የሕብረ ዝማሬ (ኳየር) ቡድን ውስጥ ከበሮ ተጫዋች ነበር። በቀብሩ ላይ ግን ማንም የሙዚቃ መሣሪያ ሊጫወትለት አለመቻሉ ያሳዝናል። ወዳጅ ዘመዶቹ ማድረግ የቻሉት በፌስቡክ የቀጥታ ሥርጭቱ የአስተያየት መስጫ ሳጥን ላይ ስለ ክሪስ የሚያስታውሱትን መፃፍ ነው፤ የምትለው የቢቢሲዋ ጋዜጠኛ ሜርሲ ጁማ ስለቀብሩ የሚከተለውን ጽፋለች።

    ተጨማሪ ያንብቡ
    next
  12. ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለኢድ አልፈጥር በዓል አደረሳችሁ

    የኢድ አልፈጥር መልካም ምኞት

    እንደምን አደራችሁ!

    በዛሬው ዕለት 1441ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል በመላው አለም በሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ እየተከበረ ነው።

    የዛሬዋ ዕለት በእስልምና ተከታዮች ዘንድ ቅዱስ ተብⶀ የሚጠራው የረመዳን ፆም ማብቂያን ታበስራለች።

    ለሰላሳ ቀናት ያህልም አማኞች ራሳቸውን ከምግብና ከውሃ አቅበው በፀሎትና በስግደት ለአንድ ወራት ያህል አሳልፈዋል። የዘንድሮውን የረመዳን ፆምም የኮሮና ወረርሽኝ ለአለም ስጋት በሆነበት ወቅት ብዙዎች ከዚህ ቀደም እንደሚያደርጉት ወደ መስጊድ ሳይሆን በቤታቸው ሆነው አሳልፈውታል።

    ከዚህ ቀደም በኢድ አልፈጥር በዓል በዓል በርካታ አማኞች በጧት ተነስተው ስግደትና ፀሎት ወደሚደረግባቸው ቦታዎች ይተሙ ነበር።

    በአለማችን ከአምስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች በኮሮና ወረርሽኝ በተጠቁበት ሰዓት በሃገራችን እንዲሁም አምስት መቶ ሰዎች በኮሮና መያዛቸው ጋር ተያይዞ የበዓሉን መንፈስ እንደቀየሩት ብዙዎች እየተናገሩ ነው።

    ብዙዎች ከቤተሰብ፣ ዘመድ፣ ወዳጅ ጋር አብሮ መቋደስ፣ መጠያየቅም የበዓሉ አንድ አካል እንዳይሆንም ምክርም እየተለገሰ ነው። ቢቢሲ አማርኛ ለእስልምና እምነት ተከታዮች መልካም በዓል እንዲሆንላችሁ እየተመኘን፤ ከኮሮና ጋር ተያይዞ የምናደርገውን የቀጥታ ዘገባችንን ይከታተሉ።

  13. የዕለተ ቅዳሜ ዋና ዋና የኮቪድ-19 ጉዳዮች

    ሐኪም

    • በኢትዮጵያ በአንድ ቀን ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ላይ ቫይረሱ ሲገኝ በተመሳሳይ ከፍተኛው ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር ዛሬ [ቅዳሜ] ተመዘግቧል። በዚህም መሰረትበተደረገ ምርመራ 61 ሰዎችቫይረሱ ሲገኝባቸው፤ 23 ሰዎችደግሞ ከቫይረሱ አገግመዋል። በኢትዮጵያ እስካሁን 494 ሰዎች በበሽታው መያዛቸውተረጋግጧል።

    • በአፍሪካ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ከ100 ሺህ ማለፉ ተነግሯል። የዛሬ [ቅዳሜ] አሃዞች እንደሚያሳዩት በአፍሪካ ባሉ አገራት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 103 ሺህ 875 ነው። 3ሺህ 184 የሚሆኑት ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል።

    ·የዓለም ጤና ድርጅት ብራዚል በደቡብ አሜሪካ አዲሷ የኮሮናቫይረስ ስርጭት ማዕከል ሆናለች አለ። ድርጅቱ ከደቡብ አሜሪካ አገራት ብራዚል ክፉኛ በቫይረሱ የተመታች አገር ናት ያለ ሲሆን በዓለም በበሽታው በተያዙ ሰዎች ቁጥር ሦስተኛ ሆናለች።

    • ቻይና ለመጀመሪያ ጊዜ ወረርሽኙ ከጀመረ ወዲህ በግዛቷ በ24 ሰዓታት ውስጥ በቫይረሱ የተያዘ ሰው አላገኘሁም አለች።

    • ከስምንት ሳምንት በፊት በዓለም ዙሪያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር አንድ ሚሊዮን የነበረ ሲሆን፤ ከሁለት ወር ባለሰ ጊዜ አሁን አሃዙ ከ5.2 ሚሊዮን በላይ ደርሷል።

  14. የስፔን ላ ሊጋ ሰኔ 01/2012 ዓ.ም እንዲጀምር ተፈቀደ

    የስፔን ላ ሊጋ ጨዋታ

    የስፔን መንግሥት የአገሪቱ ከፍተኛው የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ውድድር ሊግ ሰኔ 01/2012 ዓ.ም ውድድሩን ሊጀመር እንደሚችል አስታወቀ።

    የስፔን ላ ሊጋ ውድድር መጋቢት ወር ላይ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተቋረጠ ቢሆንም ቡድኖቾች ጨዋታዎች በቅርቡ ይጀመራሉ በሚል ተስፋ በግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ በዝግ ቦታዎች ላይ ልምምድ ማድረግ ጀምረው ነበር።

    ስፔን በዓለም ላይ በወረርሽኙ ክፉኛ ከተጠቁት አገራት መካከል አንዷ ብትሆንም ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ጥላቸው የነበሩ ክልከላዎችን እያላለች ነው።

    በተመሳሳይ የጀርመን ከፍተኛው የእግር ኳስ ሊግ ቡንደስ ሊጋ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ውድድር በመጀመር በአውሮፓ ውስጥ ቀዳሚው ሆኗል።

  15. የኮሮናቫይረስን ለማከም ይችላል የተባለው የወባ መድኃኒት አደገኛ ነው ተባለ

    የወባ መድኃኒት

    የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የኮሮናቫይረስ በሽተኞች ቢጠቀሙት ይበጃል ያሉት የወባ መድኃኒት በሽታውን ከመከላከል ይልቅ የሞትን ዕድልን እንደሚያሰፋ ተመራማሪዎች ተናገሩ።

    ላንሴት የተሰኘው የሕክምና መፅሔት ላይ የወጣው የሳይንቲስቶች ጥናት እንደሚያሳየው የኮቪድ-19 በሽተኞችን በሃይድሮክሲክሎሮኪን ማከም ጉዳት እንጂ ጥቅም የለውም።

    ፕሬዝደንት ትራምፕ በሽታው ባይኖርብኝም በሽታው ገሸሽ ለማድረግ የወባ መድኃኒት እየወሰድኩ ነው ማለታቸው አይዘነጋም። ነገር ግን የሕክምና ባለሙያዎች መድኃኒቱን መውሰድ ጥቅም አልባ ከሆኑም በላይ ከልብ ሕመም ሊዳርግ ይችላል ሲሉ ያስጠነቅቃሉ። ዝርዝሩን እዚህ ያንብቡ፡ የወባ መድኃኒት የኮቪድ-19 በሽተኞች ከማዳን ይልቅ ለሞት እየዳረገ ነው

  16. የወባ ትንኝ

    በአማራ ክልል ውስጥ በሚገኙ ሃያ አምስት ወረዳዎች ውስጥ የወባ በሽታ በወረርሽኝ መልክ መከሰቱን የክልሉ የኅብረተሰብ ጤና ተቋም ገለጸ። በተለይ በቋራ መተማ፣ ምሥራቅ ደምቢያ፣ ጎንደር ዙሪያ፣ ጃዊ፣ ባህርዳር ዙሪያ፣ ደብረ ኤልያስ፣ ሸዋ ሮቢት፣ ራያ ቆቦ፣ ቃሉ እና አበርገሌን የመሳሰሉ ወረዳዎች በሽታው በጣም ከጨመረባቸው አካባቢዎች ጥቂቶቹ ናቸው። "ወባ ጠፍቷል በሚል የአጎበር አጠቃቀም ከጊዜ ወደ ጊዜ መቀነስ፣ ለወባ መራቢያ ምቹ የሆኑ አካባቢዎችን አለማጽዳት፣ የአየር ንብረት ለውጥና ከኮቪድ-19 ጋር ተያይዞ የጤና ኬላዎች ትኩረት መቀነስ" ለወባ በሽታ ክስተት መጨመር በምክንያትነት ተጠቅሰዋል።

    ተጨማሪ ያንብቡ
    next
  17. የማላዊ እግር ኳስ አፍቃሪዎች ኳስ ካልተጀመረ እያሉ ነው

    Malawi

    የማላዊ እግር ኳስ አፍቃሪዎች ተጫዋቾች ወደ ሜዳ እንዲመለሱ ጫና እያሳደሩ ነው።

    የአገሪቱ ሊግ በቫይረሱ ሰርጭት ምክንያት ተቋርጦ ይገኛል።

    በአገሪቱ የሚገኙ ሁለት አንጋፋ የእግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎች የአገሪቱ እግር ኳስ ማህበር ሊጉን እንዲያስጀምር ጫና እያሳደሩ ነው።

    የናይሳ ቢግ ቡሌት እና ቢ ፎርዋርድ ወንደረረስ ደጋፊዎች፤ 'ፖለቲከኞች በርካታ ሰዎችን በአደባባይ እየሰበሰቡ ባሉበት ወቅት እግር ኳስ የማይጀመርበት ምንም ምክንያት የለም' ሲሉ አቤቱታቸውን ለእግር ኳስ ማህበሩ አስገብተዋል።

    ማህበሩ በበኩሉ ሊጉ እንዲጀመር ከመወሰኔ በፊት ከሚመለከታቸው ባለስልጣናት ጋር እመክርበታለሁ ብሏል።

  18. ቆጵሮስ ከ20 አገራት ለሚነሱ በረራዎች ድንበሯን ከፍት ልታደርግ ነው

    Cyprus

    በመካከለኛው ምሥራቅ የምትገኘው እና የጎብኚዎች መዳረሻ የሆነችው ቆጵሮስ ከሰኔ 2 ጀምሮ ለመንገደኞች በረራ አየር መንገዶች ክፍት እንደምታደርግ አስታውቃለች።

    መነሻቸው ከ20 አገራት በላይ ያደረጉ አየር መንገደኞች ተሳፋሪዎቻቸውን ጭነው ወደ ቆጵሮስ ማቅናት ይችላሉ ተብሏል።

    በእነዚህ አገራት ዝርዝር ውስጥ ዩናይትድ ኪንግደም እና ሩሲያ አልተካተቱም። ምንም እንኳ ቆጵሮስ ቱሪዝም ገቢ ምንጭ ዩናይትድ ኪንግደም እና ሩሲያ ቢሆኑም የቆጵሮስ መንግሥት ግን በእነዚህ አገራት የቫይረሱ ስርጭት በቁጥጥር ሥር አልዋለም የሚል እምነት አለው።

    ወደ ቆጵሮስ መግባት የሚሹ መንገደኞች ባለፉት 72 ሰዓታት ውስጥ የተገኘ ከኮቪድ-19 ነጻ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ሰርተፊኬት መያዝ አለባቸው ተብሏል።

  19. የቱርክ አየር መንገድ በቀጣዩ ወር በረራ ማድረግ ይጀምራል ተባለ

    Turkish Airlines

    የቱርክ አየር መንገድ በቀጣዩ የፈረንጆቹ ወር ወደ ካዛኪስታን በረራ ማድረግ እንደሚጀምር ተነገረ።

    የካዛኪስታን እና ተርኪሽ አየር መንገዶች የመንገደኞች በረራን በሁለቱ አገራት መካከል ማድረግ እንደሚጀምሩ የካዛኪስታን የኢንደስትሪ እና መሠረተ ልማት ሚንስትር ለሬውተርስ ተናግረዋል።

    ሚንስትሩ እንዳሉት አየር መንገዶቹ በረራውን የሚጀምሩት የኖቬል ኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መቆጣጠር ከተቻለ ነው።

    በጉዳዩ ላይ የሁለቱ አገራት ባለስልጣናት መምከራቸው ተጠቅሷል።

    የካዛኪስታን አየር መንገድ ዜጎችን ከሌሎች አገራት ለማስወጣት ካልሆነ በቀር ወደ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎቹ በረራ ማድረጉን ካቆመ ሶስት ወራትን ለመድፈን ር ቀናት ናቸው የቀሩት።

    ካዛኪስታን በዚህ ወር ቀስ በቀ የአገር ውስጥ በረራዎችን አስጀምራለች።

  20. ሰበርበኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙና ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ከፍተኛው ቁጥር ተመዘገበ

    BBC logo

    በኢትዮጵያ ውስጥ የኮሮናቫይረስ በሽታ ከተገኘ ወዲህ በአንድ ቀን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ላይ ቫይረሱ ሲገኝ በተመሳሳይ ከፍተኛው ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር ተመዘገበ።

    የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ተቋም በጋራ በሚያወጡት መግለጫ በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓታት በተደረገ ምርመራ 61 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን አረጋግጠዋል።

    በተጨማሪም ከዚህ ቀደም ቫይረሱ እንዳለባቸው ተረጋግጦ በለይቶ ህክምና መስጫ ውስጥ ከነበሩ ህሙማን መካከል 23 ሰዎች ከቫይረሱ አገግመዋል።

    ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ 3757 ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎላቸው 43 ወንዶችና 18 ሴቶች በቫይረሱ መያዛቸው ተነግሯል።

    በዜግነት ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ሲሆኑ ዕድሜያቸው ደግሞ ከ15-70 ድረስ መሆኑን መግለጫው አትቷል።

    48 ሰዎች ከአዲስ አበባ፣ 7 ሰዎች ከሶማሌ ክልል፣ 3 ሰዎች ከአፋር ክልል፣ 2 ሰዎች ከኦሮሚያ ክልል እና 1 ሰው ከአማራ ክልል የተገኙ ናቸው።

    11 ሰዎች የውጭ ሃገራት የጉዞ ታሪክ እንዳላቸው ታውቋል። 5 ሰዎች ደግሞ በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ የነበራቸው ናቸው። የተቀሩቱ 45 ሰዎች ግን ንክኪም ሆነ የጉዞ ታሪክ የላቸውም ተብሏል።

    ቁጥሩ ኢትዮጵያ እስከዛሬ ካገኛቻቸው ከፍተኛው ነው።

    ኢትዮጵያ ውስጥ በተደረገ ምርመራ በአጠቃላይ 494 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጧል።