ኮሮናቫይረስ፡ በኤርትራ አራት እስር ቤቶች ያሉ ታራሚዎች በተጨናነቀ ሁኔታ መታሰራቸው አስጊ እንደሆነ ተገለፀ

አሥመራ ከተማ

የፎቶው ባለመብት, DEA / A. TESSORE

የምስሉ መግለጫ, አሥመራ ከተማ

በኤርትራ የሚገኙ አራት እስር ቤቶች ከአቅማቸው በላይ በእስረኞች መጨናነቃቸው ታራሚዎች በኮሮናቫይረስ በቀላሉ ሊጋለጡ እንደሚችሉ አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ድርጅት አምነስቲ አስታውቋል።

በአራቱ እስር ቤቶች ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ታራሚዎች እንዳሉ የጠቆመው አምንስቲ፣ እነዚሀም አዲ አቤይቶ፣ ማይ ሰርዋ፣ ማይ ሰርዋ ማቆያ ካምፕ እና አላ ሲሆኑ ሁሉም ከአስመራ በቅርብ ርቀት እንደሚገኙ እንዲሁም ወንዶች ብቻ የታሰሩባቸው መሆኑን ሪፖርቱ አመላክቷል፥

አዲ አቤይቶ እስር ቤት ስምንት መቶ ሰዎች የመያዝ አቅም ቢኖረውም በአራት እጥፍ ከአቅሙ በላይ እስረኞችን መያዙን፣ አላ የተሰኘው እስር ቤት ደግሞ 1200 ሰው የመያዝ አቅም ቢኖረውም ሶስት እጥፍ የሚበልጡ እስረኞች እንደሚገኙበት፣ ማይ ሳዋ 230 እስረኞችን የመያዝ አቅም ቢኖረውም በእጥፍ ታራሚዎች መኖራቸውም ተገልጿል።

ከእነዚህ ታራሚዎች መካከል አብዛኞቹ ፍርድ ቤት ቀርበው ክስ እንዳልቀረበባቸው የገለፀው ሪፖርቱ መቼ እንደሚቀርቡ አልያም የእስር ጊዜያቸው መቼ እንደሚያበቃ እንደማያውቁ በመግለጫው ላይ አስፍሯል።

ከዚህም በተጨማሪ ታራሚዎቹ በጣባብ ክፍሎች፣ በኮንቴይነሮች ውስጥ እንዲሁም መለስተኛ አዳራሽ ውስጥ ታስረው እንደሚገኙና በዚህ በኮሮናወረርሽኝ ወቅት አካላዊ ርቀትን ለመጠበቅም ሆነ ንጽህናቸው ለመጠበቅ አስቸጋሪ መሆኑን አመልክቷል።

ለታራሚዎቹ መንግሥት ከሚያቀርበው መደበኛ የምግብ አቅርቦት ባሻገር ቤተሰቦቻቸው በሚያመጡላቸው ስንቅ የሚደጎሙ ቢሆንም አሁን በተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ ምክንያት ግን ጠያቂ በመቅረቱ እስረኞቹን ለምግብ እጥረት፣ ለሕመምና ለበሽታ እንደተጋለጡ አስታውቋል።

አምንስቲ አገኘሁት ባለው መረጃ በሺዎች የሚቆጠሩ ታራሚዎች ገላቸውን ለመታጠብ፣ መጸዳጃ ቤት ለመሄድ ተከልክለው ታጉረው ይገኛሉ ብሏል።

በእነዚህ እስር ቤቶች ውስጥ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ቢከሰት በፍጥነት እንደሚሰራጭ እና የበርካቶች ጤና ለአደጋ እንደሚያጋልጥ የጠቀሰው ሪፖርቱ በአራቱ እስር ቤቶች ያለው ሕይወት ፈታኝ መሆኑን አስቀምጧል።

ድርጅቱ በእነዚህ እስር ቤቶች የታሰሩ ሰዎች በቂ የንጽህና መጠበቂያ፣ የጤና አገልግሎት፣ ምግብ በሌለበት ሁኔታ የታሰሩ በመሆኑ፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ሕይወታቸው አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደወደቀ አስታውቋል።

" ማንም ለአእምሮውም ሆነ ለአካሉ ጤንነት አደገኛ በሆነ ሁኔታ ተይዞ መቆየት የለበትም" ያለው መግለጫው በአዲ አቤይቶ የሚገኙ 2500 ያህል እስረኞች ልብሳቸውን ማጠብ እና ገላቸውን መታጠብ የሚፈቀድላቸው በሳምንት ሁለት ጊዜ ብቻ ነው።

ነገር ግን በሌሎቹ ሶስት እስር ቤቶች እስረኞች ንጽህናቸውን ለመጠበቅ የሚፈቀድላቸው አልፎ አልፎ መሆኑ በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።

የአገሪቱ ባለሰልጣናት የግል ንጽህና መጠበቂያ ሳሙና፣ እንደማይሰጡ መግለጫው ጠቅሶ ታሳሪዎች ከቤተሰቦቻቸው የሚመጣላቸውን የንጽህና መጠበቂያ ብቻ እንደሚጠብቁ አስታውቋል።

ታራሚዎች በሽቦ አጥር ላይ ዘልለው እንዳያመልጡ በማለት ሽፍን ጫማም ሆነ ነጠላ ጫማ ማድረግ እንደሚከለከሉ ተገልጿል።

የድርጅቱ የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ኃላፊ የሆኑት ዴፕሮሴ ሙቼና " በኤርትራ የሚገኙ ታራሚዎች በተጨናነቀ እና ንጽህናው ባልተጠበቀበት ስፍራ ታስረው ስለሚገኙ ተላላፊ በሽታ በቀላሉ ሊያዙ ይችላሉ" ብለዋል።

ለአምንስቲ እማኝነታቸውን የሰጡ ግለሰቦች እንደተናገሩት በአራቱ አስር ቤቶች የሚገኙ ታራሚዎች ለአእምሮ ህመም፣ ደም ግፊት፣ ስኳር፣ የልብ ድካም፣ አኒሚያ፣ ተቅማጥ፣ አስም፣ ቲቢ ፣ የአይንና ጆሮ ኢንፌክሽን፣ የጨጓራ ኢንፌክሽን ይጠቃሉ።

እነዚህ ታራሚዎች የመጀመሪያ ሕክምና እርዳታ ብቻ በሰለጠኑ የሕክምና ባለሙያዎች እንደሚታከሙ የገለፀው ሪፖርቱ፣ በእስር ቤቶቹ ውስጥ እንደ የሙቀት መለኪያ ያሉ ቀላል የሕክምና መሳሪያዎች ጭምር እጥረት መኖሩንም መግለጫው አመላክቷል።

ኮሮና
Banner

.