ኮሮናቫይረስ፡ የሩሲያ የኮቪድ-19 ክትባት በሽታ የመከላከል አቅምን ከፍ ያደርጋል ተባለ

የሩሲያው ክትባት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የሩሲያ ሳይንቲስቶች ለኮሮረናቫይረስ በተሰራው ክትባት ዙሪያ የመጀመሪያ ሪፖርታቸውን አቅርበዋል።

በክትባቱ ላይ የተደረጉ ምርምሮችን መሠረት በማደረግ ክትባቱ የሰዎችን የበሽታ የመከላከል አቅምን ከፍ እንደሚያደርግ ደርሰንበታል ብለዋል ተመራማሪዎቹ።

ሪፖርቱ ዘ ላንሴት በተሰኘው ሜዲካል ጆርናል ላይ ነው የወጣው።

በሪፖርቱ ላይም ሁሉም የጥናቱ ተሳታፊዎች ክትባቱ ከተሰጣቸው በኋላ ቫይረሱን ለመዋጋት የሚያስችላቸው አንቲቦዲ ማዳበራቸውን እና የከፋ የጎንዮሽ ጉዳት እንዳልታየባቸው ተገልጿል።

ሩሲያ በአገሯ ለተመረተው ክትባት ለሰዎች ጥቅም እንዲውል ባሳለፍነው ወር ፈቃድ የሰጠች ሲሆን እስካሁን ድረስ ከሩሲያ በስተቀር ለኮሮናቫይረስ የሚሆን ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል የፈቀደ ሌላ አገር የለም።

አሁን የዓለም ሳይንቲስቶችን እያነጋገረ ያለው ነጥብ የትኛውም መድኃኒት ወይም ክትባት ሲፈጠር ሦስት ጥብቅ ምዕራፎችን ማለፍ እያለበት ፑቲን በሁለት ምዕራፍ ክትባቱ ጥቅም ላይ እንዲውል ማዘዛቸው ነው።

ሪፖርቱ ምን ይላል?

'ስፑትኒክ ቪ' የሚል ስያሜ በተሰጠው ክትባት ላይ ባሳለፍነው ሰኔ እና ሃምሌ ወራት ላይ ሁለት ሙከራዎች ተከናውነውበታል።

ዘ ላንሴት ላይ የወጣው ሪፖርት እንዳመላከተው በሁለቱም ሙከራዎች 38 ጤናማ በጎ ፈቃደኛ ተሳታፊዎች ክትባቱ ተሰጥቷቸዋል።

እድሜያቸው ከ18 እስከ 60 የሆኑት ተሳታፊዎች ለ42 ተከታታይ ቀናት በተመራማሪዎች ጥብቅ ክትትል ሲደረግባቸው ነበር ተብሏል። በሶስተኛው ሳምንት ደግሞ ሁሉም የጥናቱ ተሳታፊዎች ቫይረሱን ለመዋጋት የሚያስችል አንቲቦድ ሰውነታቸው ማዳበሩ ተጠቅሷል።

በተሳታፊዎቹ ላይ ምንም አይነት ከባድ የጎንዮሽ ህመም ያልተስተዋለ ሲሆን አብዛኛዎቹ ግን ራስ ምታት እና የመገጣጠሚያ ህመም እንደተሰማቸው ተመዝግቧል።

በሚቀጥሉት ሳምንታት ደግሞ 40 ሺ ጤናማ በጎ ፈቃደኞችን የሚያካትት ሶስተኛ ዙር ሙከራ የሚደረግ ሲሆን ይበልጥ ተጋላጭ በሆኑ የእድሜ ክልሎች የሚገኙ ሰዎች በብዛት እንዲካተቱ ይደረጋልም ተብሏል።

ክትባቱን በበላይነት የሚቆጣጠረው የሩሲያ ኢንቨስትመንት ፈንድ ዋና ኃላፊ የሆኑት ኪሪል ድሜትሪቭ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ሪፖርቱ ''የሩሲያን ክትባት በጥብቅ ሲተቹ ለነበሩ ሰዎች ምላሽ ይሆናል'' ብለዋል።

አክለውም ለቀጣይ ዙር ሙከራ እስካሁን ድረስ 3 ሺ ሰዎች መመረጣቸውን ገልጸዋል።

የአገሪቱ የጤና ሚኒስትር የሆኑት ሚካይል ሙራሽኮ በበኩላቸው ሩሲያ ከሕዳር እስከ ታህሳስ ባለው ጊዜ ውስጥ ለቫይረሱ ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች ክትባቱን መስጠት እንደምትጀምር አስታውቀዋል።

ኮሮና
Banner