Got a TV Licence?

You need one to watch live TV on any channel or device, and BBC programmes on iPlayer. It’s the law.

Find out more
I don’t have a TV Licence.

ቀጥታ ዘገባ

የተጠቀሱት ሰዓቶቸ የዩናይትድ ኪንግደም ናቸዉ

  1. የቺችኒያው መሪ በኮሮናቫይረስ ተይዘው ሊሆን ይችላል እየተባለ ነው

    የቺችኖች መሪ ራምዛን ካድያሮቭ

    የቺችኒያው መሪ ራምዛን ካድያሮቭ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተጠርጥሮ ሆስፒታል መግባታቸውን የሩሲያ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    የ43 ዓመቱ ራምዛን ጉንፋል መሰል ምልክት በማሳየታቸው ረቡዕ ዕለት በአውሮፕላን ወደ ሞስኮ መምጣታቸውን ዘገባዎች ጠቁመዋል።

    ሌላ ግለሰብ በበኩሉ " ሞስኮ ሆስፒታል ውስጥ ናቸው" ማለቱን ሪያ ኖቮስቲ የተሰኘ የዜና ወኪል ዘግቧል።

    ራምዛን ካድያሮቭ ከዚህ ቀደም የቺቺኒያን ግዛት ከሩሲያ ነጻ ለማውጣት ጦር የተማዘዙ ሲሆን አሁን ግን የቭላድሚር ፑቲን ቁልፍ አጋር ናቸው።

    ራምዛን አሁን ያሉበት ሁኔታ የማይታወቅ ሲሆን በግል ሐኪማቸው ምክር ወደ ሞስኮ መሄዳቸው ተነግሯል።

    የመሪው መታመም ከተረጋገጠ በቅርብ ጊዜ በኮሮናቫይረስ ከተያዙ የሩሲያ ባለስልጣናት መካከል ተጨማሪ ይሆናሉ ።

  2. የናይጄሪያ ፖሊስ በጤና ባለሙያዎች ላይ የሚያደርገውን ትንኮሳ አቆማለሁ ብሎ ቃል መግባቱን ተከትሎ አድማቸውን ሰረዙ

    የናይጄሪያ ፖሊስ

    በናይጄሪያዋ የንግድ ማዕከል ሌጎስ የሚገኙ ዶክተሮች ከሰአት እላፊ ጋር ተያይዞ ፖሊስ ማስፈራሪያና ዛቻ አድርሶብናል በማለት ጠርተውት የነበረውን አድማ፣ ፖሊስ ማስፈራሪያዎቹም ሆነ ትንኮሳዎቹን እንደሚያስቀር ቃል መግባቱን ተከትሎ ሰርዘውታል።

    የኮሮናቫይረስን መዛመት ለመግታት በከተማዋ የሰአት እላፊ አዋጅ መተላለፉን ተከትሎ ቁልፍ የሚባሉት የህክምና ባለሙያዎች ተደጋጋሚ ትንኮሳ፣ ማስፈራሪያና ዛቻ ከፖሊስ እየደረሰብን ነበር ብለዋል።

    ፖሊስ አምቡላንስ አስቁሞ ህሙምተኛውን እንዲሁም የጤና ባለሙያዎቹን በቁጥጥር ስር ማዋሉ እንዲሁም የተለያዩ ክስተቶች የጤና ባለሙያዎቹን የገፋቸው መሆኑም ተገልጿል።

    የናይጄሪያ ህክምና ማህበር በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ አባላቱ በሙሉ ቤት የመቀመጥ አድማ እንዲያደርጉ ውሳኔ ላይ ደርሶ ነበር።

    ባለፈው ወር የሃገሪቷ ፕሬዚዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪ የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ ቁልፍ የሚባሉ ሰራተኞች የሰአት እላፊ አዋጁ አይመለከታቸውም ብለው ነበር።

    ማህበሩ በበኩሉ ፖሊስ ይህንን ችላ በማለት የጤና ባለሙያዎች አስገድዶ ወደ ቤት እንዲሄዱ አድርጓቸዋል ብሏል።

    የሌጎስ አስተዳዳሪ ባብጂዴ ሳንዎ ኦሉ ጣልቃ ገብተው ማስማማታቸው ችግሩን እንደፈታውም ተገልጿል።

  3. የኢትዮጵያ ብር

    በኢትዮጵያ ከባንኮችና ከማክሮ ፋይናንስ ተቋማት በሚወጣ የጥሬ ገንዘብ ላይ የተጣለው እገዳ ተግባራዊ መደረግ ጀምሯል። ብሔራዊ ባንክ ያወጣው መመሪያ ተቋማትና ግለሰቦች ከባንኮች በቀንና በወር ውስጥ በሚያወጡት የጥሬ ገንዘብ መጠን ላይ ገደብ ጥሏል። የመንግሥት ውሳኔ መነሻ ምክንያቶች ምን ሊሆኑ ይችላሉ? የምጣኔ ባለሙያዎች አስተየየታቸውን ለቢቢሲ አካፍለዋል።

    ተጨማሪ ያንብቡ
    next
  4. አሥመራ ከተማ

    በኤርትራ የሚገኙ አራት እስር ቤቶች በከፍተኛ ሁኔታ በመጨናነቃቸውና ንጽህናቸው የተጠበቀ አለመሆኑ ታራሚዎች እንደ ኮሮናቫይረስ ላሉ ተላላፊ በሽታዎች በቀላሉ ሊጋለጡ እንደሚችሉ አምነስቲ በሪፖርቱ አስታውቋል።

    ተጨማሪ ያንብቡ
    next
  5. የጤና ባለሙያ መመርመሪያ ይዞ

    ደቡብ አፍሪካ በአፍሪካ ከፍተኛ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የሚገኙባት ስትሆን ግብጽና አልጄሪያ ደግሞ በኮሮና ምክንያት በሞቱ ሰዎች ቁጥር 680 እና 568 በማስመዝገብ ይበልጣሉ። የደቡብ አፍሪካ ጤና ሚኒስትር በተጨማሪም እንደገለፁት በአገሪቱ ባለፉት 24 ሰዓታት ከተመዘገቡ 27 ሞቶች መካከል የሁለት ቀን ሕፃን ይገኝበታል።

    ተጨማሪ ያንብቡ
    next
  6. በአሜሪካ በቫይረሱ ምክንያት ስራ ያጡ ሰዎች ቁጥር ወደ 39 ሚሊዮን ደረሰ

    የኒውዮርክ ከተማ

    በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ክፉኛ እየተጎዳች ባለችው አሜሪካ ባለፈው ሳምንት 2.4 ሚሊዮን ሰዎች ስራ ማጣታቸው ተዘግቧል።

    ምንም እንኳን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ በቫይረሱ ቢያዝም አሜሪካ ኮሮናቫይረስ እንዳይዛመት የጣለቻቸውን ህጎች እያላላች መምጣቷ የምጣኔ ኃብት እንቅስቃሴውን እንዲያንሰራራ ይረዳዋል ተብሎ ታስቦ ነበር።

    በአጠቃላይ ከጎርጎሳውያኑ የካቲት አጋማሽ ጀምሮም በኮሮናቫይረስ ስራቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር 38.6 ደርሷል።

    ይህም ቁጥር የአገሪቷ ሩብ የስራ ኃይል እንደሆነም ተገልጿል።

    በአሜሪካ ባሉ ግዛቶች የፍሎሪዳና ጆርጂያ ግዛቶች በርካታ ሰዎች ከስራ መባረራቸውን ለመንግሥት በማመልከት ቀዳሚዎች ሆነዋል።

  7. በመርካቶ ጭምብል አጥልቀው የሚያወሩ ግለሰቦች

    በኢትዮጵያ በባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ 3747 የላብራቶሪ ምርመራ መደረጉን ተከትሎ አጠቃላይ ቁጥሩን 69 ሺህ 507 አድርሶታል። ሃገሪቷ አቅሟንም በመጨመር በቀን 10ሺህ ሰዎችን የመርመር እቅድ እንዳላት የጤና ሚኒስትሯ ማሳወቃቸው የሚታወስ ነው። በሃገሪቱ ውስጥ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 398 የደረሰ ሲሆን፣ 268ቱ በህክምና ላይ እንዲሁም 123ቱም አገግመዋል። ሃገሪቷ አምስት ዜጎቿን ስታጣ ሁለቱ ደግሞ ወደየሃገራቸው ተመልሰዋል። ስለወረርሽኙ የተለያዩ መረጃዎችን ለማግኘት የቢቢሲ አማርኛን የቀጥታ ዘገባ እዚህ ገጽ ላይ ይከታተሉ።

    Catch up
    next
  8. የላቲን አሜሪካ ሃገራት እንዴት ዋሉ?

    በፔሩ ጭምብል ያጠለቁ ሰዎች

    በላቲን አሜሪካ ባሉ ሃገራት ወረርሽኙ እየተዛመተ ነው የሚሉ ስጋቶች ጨምረዋል። ከሰሞኑ ካሉ አዳዲስ መረጃዎች መካከል፡

    • ሜክሲኮ ሳንቶስ ላጉና በተባለ አንድ እግር ኳስ ክለብ ውስጥ ስምንት ተጫዋቾች የኮሮናቫይረስ እንዳለባቸው ተረጋግጧል። ተጫዋቾቹ ምንም አይነት የኮሮናቫይረስ ምልክትም እያሳዩም አይደለም ተብሏል። ቀሪዎቹም የቡድኑ አባላትም የምርመራ ውጤታቸውን እየጠበቁ ነው። የእግር ኳስ ጨዋታዎች ለባለፉት ሁለት ወራት የታገዱ ሲሆን በቅርቡም ይጀመራሉ የሚል ተስፋም የለም ተብሏል።
    • የቦሊቪያ ጤና ሚኒስትር በሙስና ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለዋል። ሚኒስትሩ ማርሴሎ ናቫጃስ በተጋነነ ዋጋ ቬንትሌለተሮችን ከስፔን ኩባንያ ገዝተዋል በሚልም ምርመራ ሲደረግባቸው ነበር። ሚኒስትሩ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተከትሎ የሃገሪቷ ፕሬዚዳንት ከስራ አባረዋቸዋል። ፕሬዚዳንቷ እንዳሉት "ማንም ቢሆን ከቦሊቪያውያን እንዲሰርቅ አንፈቅድም" ብለዋል።
    • የአለም ጤና ድርጅት በኮሮናቫይረስ በተያዙ ሰዎች እንዲሁም በሟቾች ቁጥር አሜሪካና ላቲን አሜሪካ ቀዳሚ ናቸው በማለት አስጠንቅቀዋል። በቅርብ የተገኙ መረጃዎችም እንደሚያስረዱት በብራዚልፔሩሜክሲኮ በኮሮናቫይረስ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ ነው።
  9. ለሁለት ወራት በታይላንድ አየር ማረፊያ የቆዩት ናይጄሪያዊያን ወደ ሃገራቸው ሊመለሱ ነው

    ናይጄሪያውያን በታይላንድ አየር ማረፊያ

    ለባለፉት ሁለት ወራት በታይላንድ መዲና ባንኮክ ሱቫርናብሁሚ አየር ማረፊያ በኮሮናቫይረስ ምክንያት መውጫ አጥተው የቆዩት ሶስት ናይጄሪያውያን ወደ ሃገራቸው ሊመለሱ ነው።

    ናይጄሪያውያኖቹ ወደ ሃገራቸው መመለስ ቢፈልጉም የኮሮናቫይረስን መዛመት ለመካለከል አገራቱ ያወጡትን የጉዞ እግድ ተከትሎ በአየር ማረፊያው እንዲቆዩ ተደርጓል።

    ግለሰቦቹ በባንኮክ የሚገኘው የናይጄሪያ ኤምባሲ ጋርም እየተገናኙ እንደነበር የናይጄሪያ ዲያስፖራ ኮሚሽን አስታውቋል።

    ሁለቱ ግለሰቦች ወደ ላኦስ እንዲሁም ሶስተኛው ደግሞ ወደ ማይናማር ለመጓዝ ነበር የተሳፈሩት፤ ነገር ግን የሃገራቱ ድንበሮች በመዘጋታቸው በአየር ማረፊያው እንዲቆዩ ግዴታ ሆኖባቸዋል።

    ግለሰቦቹ ከአየር ማረፊያው ወጥተው ባንኮክ ከተማ ውስጥ እንዳይቆዩ የታይላንድ ቪዛም ስላልነበራቸው፤ ታይላንድም መሸጋገሪያቸው ስለነበረች አጣብቂኝ ውስጥ ገብተው ነበር።

    ወደ ሃገራቸው ናይጄሪያም መመለስ አልቻሉም ምክንያቱም መግሥታቸው የኮሮናቫይረስን መዛመት ለመግታት የሃገሪቷን አየር ማረፊያዎች የመዝጋት ውሳኔ በመተላለፉ።

    View more on twitter
  10. ወጣቶቹ

    አፍጋኒስታን ውስጥ ያለ አንድ ወጣት ሴቶች ብቻ ያሉበት ቡድን የመኪና መለዋወጫዎችን በመጠቀም በኮሮናቫይረስ በጽኑ የታመሙ ሰዎችን ለመርዳት የሚያገለግለውን የመተንፈሻ መሳሪያ [ቬንትሌተር] እየሰሩ ነው።

    ተጨማሪ ያንብቡ
    next
  11. አቶ ታደሰ ካሳ

    የባሕር ዳርና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአቶ ታደሰ ካሳ ላይ ስምንት ዓመት ከአምስት ወር ጽኑ እስር ፈርዷል።

    ተጨማሪ ያንብቡ
    next
  12. የክልሉ መንግሥት የኦሮሚያ ልዩ ፖሊስ አባላትን ባስመረቀበት ወቅት

    በጉጂ ዞን አስራ ሁለት የኦሮሚያ ክልል ልዩ ፖሊስ አባላት በታጣቂዎች መገደላቸውን አንድ የዞኑ ባለስጣን ለቢቢሲ ገለጹ። የጉጂ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ማሊቻ ዲቃ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በግጭቱ በሰው ህይወት እና በንብረት ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ተናግረዋል።

    ተጨማሪ ያንብቡ
    next
  13. የዋትፎርዱ ተከላካይ አድሪያን ማሪያፓ በኮሮናቫይረስ መያዙን አስታወቀ

    አድሪያን ማሪያፓ

    የዋትፎርድ ተከላካይ አድሪያን ማሪያፓ በአንግሊዝ ክለቦች ውስጥ በኮሮናቫይረስ ከተያዙት ሶስት ሰዎች መካከል አንዱ እሱ መሆኑን አስታውቋል።

    ተጫዋቹ ለቴሌግራፍ እንደተናገረው "ሙሉ ጤንነት እየተሰማህ እንዲሁም ሙሉ ጊዜህን ቤት ውስጥ እያሳለፍክ ቫይረሱ አለብህ መባል በጣም አስፈሪ ነው" ብሏል።

    "ወደ ስልጠና ባልመለስና ምርመራውንም ባላደርግ ቫይረሱ እንዳለብኝ መቼም አላውቅም ነበር" ማለቱንም ቴሌግራፍ ዘግቧል።

    በዚህ ሳምንት ማክሰኞ በሶስት ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ላይ በተደረገ ምርመራ ስድስት ተጫዋቾች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል ተብሏል።

    የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች የኮሮናቫይረስ እንዳይዛመት በሚል ከመጋቢት 4፣ 2012 ዓ.ም ጀምሮ ታግደዋል።

    የሊጎቹ ጨዋታ ሰኔ 5፣ 2012 ዓ.ም ይጀመራል ተብሎ እቅድ የተያዘ ቢሆንም አሁን ባለው ሁኔታ ግን ሳይገፋ አይቀርም ተብሏል።

  14. የቤት ኪራይ መክፈል ያልቻለችው ኬንያዊት ጣራና በሯ በአከራይዋ ተገነጠለ

    ኢስሊ አካባቢ

    ኬንያዊቷ የባለፈውን ወር የቤት ኪራይ መክፈል ባለመቻሏ በሯን እንዲሁም ጣራዋ በአከራይዋ መገንጠሉን የሃገሪቱ ሚዲያ ሲትዝን ቴሌቪዥን ዘግቧል።

    ተከራይዋ ሩት ሺኑዱ ትተዳደርበት የነበረው ያገለገሉ አንሶላዎችና ብርድ ልብሶችን መሸጥ ስራ ቦኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ሙሉ በሙሉ ቀጥ በማለቱ በየወሩ መክፈል የነበረባትን አራት ሺህ ብር የቤት ኪራይ መክፈል አልቻለችም።

    የአራት ልጆች እናት የሆነችው ሩት ወደ መዲናዋ ናይሮቢ ከመጣች አንድ አመትን ያስቆጠረች ሲሆን፤ ተከራይታም በምትኖርበት አንድ መኝታ ክፍልም ውስጥ ይህን ያህል ጊዜ ቆይታለች። በባለፈው አንድ አመት ውስጥም የቤት ኪራይዋን ሳታጓድል ትከፍል ነበር።

    ባለፈው ሰኞም አከራይዋ ከወጣቶች ጋር ሰብሰብ ብላ መጥታ የተከራይዋን በር እንዲገነጥሉ በሰጠችው ትዕዛዝ መሰረት በሩን ገንጥለው እንደወሰዱት ሩት ለቴሌቪዥን ጣቢያው ተናግራለች።

    ክዋንግዋሬ ተብሎ የሚጠራው አካባቢ አስተዳዳሪም ለማግባባት ቢሞክርም ሰሚ አላገኘም።

    በቀጣዩ ቀን አከራይዋ እንደገና ከወጣቶቹ ጋር መጥታ ጣራውንም መገንጠሏን ሩት አስረድታለች።

  15. ታንዛንያ ዩኒቨርስቲዎቿን ለመክፈትና ስፖርታዊ ጨዋታዎች እንዲጀመሩ ወሰነች

    ኳስ የሚጫወት ታንዛንያዊ

    የታንዛንያ ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፊሊ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ብሔራዊ ፈተና ወሳጅ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ውሳኔ አስተላልፈዋል።

    ዩኒቨርስቲዎቹም ከዘጠኝ ቀናት በኋላ የሚከፈቱ ይሆናል።

    ከዚህም በተጨማሪ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ለሁለት ወራት ተቋርጠው የነበሩ ስፖርታዊ ጨዋታዎችም እንዲጀመሩ ተወስኗል።

    ከአስራ ሁለተኛ ክፍል ውጭ ያሉ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች እንዲሁም አንደኛ ደረጃ ተማሪዎች መቼ ወደ ትምህርት ቤት እንደሚመለሱ የተባለ ነገር የለም።

    የፕሬዚዳንቱ ውሳኔ ሃገሪቷ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዋን ወደቀደመ ሁኔታ የመመለስ እቅድ የመጀመሪያ ምዕራፍ ነው ተብሏል።

    በርካታ ሃገራት ከሚያደርጉት በተፃራሪ ታንዛንያ በየቀኑ ምን ያህል ሰዎች በቫይረሱ እንደያዙ ተያዙ ለህዝቧ ማሳወቅ ካቆመች በርካታ ሳምንታት ተቆጠሩ፤ ሆኖም ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር አሽቆልቁሏል እያሉ ነው።

    ከዚህም በተጨማሪ በቀጠናው እንደሚገኙ ሃገራት ታንዛንያ አስገዳጅ የቤት መቀመጥም ሆነ እንቅስቃሴን የመገደብ ውሳኔዎችን አላስተላለፈችም። ነገር ግን ዜጎቿ አካላዊ ርቀታቸውን እንዲጠብቁ፣ የፊት ጭምብል እንዲያጠልቁ እንዲሁም እጃቸውን እንዲታጠቡ በተደጋጋሚ ከመንገር አልተቆጠበችም።

  16. አሜሪካ ቀድማ እንቅስቃሴ አለመዝጋቷ የ36 ሺህ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል

    US

    ዩናይትድ ስቴተስ አስቀድማ የሰዎች እንቅስቃሴ ላይ ማዕቀብ ጥላ ቢሆን ኖሮ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ይተርፉ ነበር ሲል አንድ የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የሠራው ጥናት አመልክቷል።

    ኒው ዮርክ ታይምስ የተሰኘው ጋዜጣ እንደዘገበው 36 ሺህ ያክል ሰዎች እንቅስቃሴ ቢገታ ኖሮ ህይወታቸው አያልፍም ነበር።

    ጥናቱ እንዳመለከተው አሜሪካ አንድ ሳምንት ቀድማ ቢሆኖ ኖሮ በርካታ ሕይወት መታደግ በተቻለ ነበር።

    አሜሪካ በበርከታ አካባቢዎች የእንቅስቃሴ ማዕቀብ የጣለችው መጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ ነበር። ነገር ግን የትራምፕ መንግሥት ከዚያ አንድ ሳምንት ቀድሞ ማሕበራዊ ርቀት እንዲጠበቅና እንቅስቃሴ እንዲገታ ቢያደርግን ኖሮ 83 በመቶ ያክል ሞት ሊቀረፍ ይችል ነበር ይላል ፅሑፉ።

    ጥናቱን የመሩት ጄፍሪ ሻማን አንድ ሳምንት በጣም ትልቅ ልዩነት አምጥቷል ይላሉ።

  17. ቁማር ተጫውተዋል የተባሉት አቃቤ ሕግ ሥራቸውን ለቀቁ

    Japan

    ጃፓን ውስጥ ካሉ ነባር አቃቤ ሐጎች መካከል አንዱ የሆኑት ሰው በሕገ-ወጥ መንገድ የመንቀሳቀስ ገደብን ጥሰው ቁማር ተጫውተዋል በመባላቸው ሥራቸውን ለቀዋል።

    ጃፓን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለመመከት በሚል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጇ አይዘነጋም። ነገር ግን አሁን የቫይረሱ ስርጭት እየቀነሰ በመምጣቱ አዋጁ ተነስቷል።

    ሂሮሙ ኩሮካዋ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጥሰው ከጓዶቻቸው ጋር ቁማር ተጫውተዋል በመባላቸው ምክንያት ዛሬ ሥራቸውን ለቀዋል።

    ሰውዬው የጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ቀኝ እጅ ናቸው ይባልላቸዋል። አልፎም አቤ ሰውዬውን ዋና አቃቤ ሕግ ሊያደርጓቸው ዕቅድ ነበራቸው ተብሎ ይወራል።

    ጃፓን ከ16 ሺህ በላይ ሰዎች በኮሮናቫይረስ እንደታዙባት አስታውቃለች። ነገር ግን ሃገሪቱ የመረመረቻቸው ሰዎች ትንሽ ናቸው የሚል ወቀሳ ይገጥማታል።

  18. ኢትዮጵያ፡ ተጨማሪ 9 ሰዎች ኮሮናቫይረስ ተገኘባቸው

    BBC

    በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓታት በተደረገው የላብራቶሪ ምርመራ 9 ሰዎች ኮቪድ-19 እንደተገኘባቸው ተገለጸ።

    የጤና ሚንስቴር እና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጋራ በሚያወጡት ዕለታዊ መግለጫ ላይ እንደተነገረው በቫይረሱ ከተያዙ መካከል 8 ወንዶችና አንዲት ሴት ናቸው።

    በዜግነት ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ ዕድሜያቸው ደግሞ ከ20-49 እንደሆነ ታውቋል።

    3 ሰዎች ከአዲስ አበባ፣ 2 ሰዎች ከአፋር ክልል፣ 2 ሰዎች ከአማራ ክልል፣ እንዲሁም ከሶማሌ እና ትግራይ አንድ አንድ ሰዎች መሆናቸው ተነግሯል።

    ከዘጠኙ መካከል አምስት የውጭ ሃገር ጉዞ ታሪክ ያላቸው፤ 2 ሰዎች በሽታው ካለበት ሰው ጋር ግንኙነት ያላቸው፤ የተቀሩት ደግሞ የዩዞ ታሪክም ሆነ ንክኪ የሌላቸው ናቸው።

    መሥሪያ ቤቶቹ በጋራ እንዳስታወቁት ባለፉት 24 ሰዓታት 2747 ሰዎች ምርመራ ተደርጎላቸዋል።

  19. የወባ በሽታ መድኃኒት

    የወባ በሽታ መድኃኒቶች ኮሮናቫይረስን ይከላከላሉ እንደሆን ለማረጋገጥ በዩናይትድ ኪንግደም ብራይተን እና ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ሙከራ ሊደረግ ነው። ክሎሮኪን፣ ሃይድሮክሲክሎሮኪን እንዲሁን በሕክምናው ፕላሴቦ ተብሎ የሚጠራ ምንም ዓይነት ጥቅምም ሆነ ጉዳት የሌለው ውህድ ከአውሮፓ፣ ከአፍሪካ፣ ከእስያና ከደቡብ አሜሪካ ለተውታጡ 40 ሺህ የጤና ባለሙያዎች ይሰጣል። ሁሉም ተሳታፊዎች የኮሮናቫይረስ ያለባቸው ወይም የነበረባቸው ናቸው ተብሏል። . . .

    ተጨማሪ ያንብቡ
    next
  20. የሁለት ቀን ጨቅላ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሞተ

    ደቡብ አፍሪካ

    በደቡብ አፍሪካ በተወለደ በሁለት ቀናት ሕይወቱን ያጣው ጨቅላ በኮቪድ-19 የሞተ በዕድሜ ትንሹ ተጠቂ ሆኗል።

    ጨቅላው ኮሮናቫይረስ ካለባት እናት የተወለደው ነው።

    የጤና ሚኒስትሩ ዝዌሊ ምኪዜ እንዳሉት ጨቅላው የሳንባ ችግር ነበረበት፤ በዚህም ምክንያት እንደተወለደ አጋዥ መተንፈሻ ማሽን አስፈልጎት ነበር።

    ሚኒስትሩ አክለውም ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ ሊተላለፍ መቻሉ ለነብሰ-ጡር እናቶች ምን ያክል ጥንቃዌ ልናደርግ እንደሚገባ የሚያሳይ ነው።

    ደቡብ አፍሪካ ትላንት [ረቡዕ] አመሻሹን 803 ተጨማሪ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ይፋ አድርጋለች። አጠቃላይ ቁጥሩም 18 ሺህ ደርሷል።