ከታሰሩ ፖለቲከኞች ውስጥ ‘የተደበደበ’ እና ‘በረሃብ አድማ’ ላይ ያሉ መኖራቸው ተነገረ

እስክንድርና ጃዋር

የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ እስክንድር እንደተደበደቡ ጠበቃቸው ሲናገሩ አቶ ጃዋር መሐመድና አቶ በቀለ ገርባ የረሃብ አድማ ላይ መሆናቸውን አንድ የፓርቲያቸው ኃላፊ ተናግረዋል።

የአቶ እስክንድር ነጋ ጠበቃ የሆኑት አቶ ሔኖክ የሸዋሉል ለቢቢሲ እንደተናገሩት ደንበኛቸው በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ለማግኘት እንዳልቻሉ ገልጸው፤ ዛሬ ፖሊስ በእስክንድር ቤት ላይ ፍተሻ ለማድረግ ይዘዋቸው እንደሄዱና ድብደባ እንደተፈፀመባቸው ቤተሰቦቻቸው እንዳሳወቋቸው ጠበቃው ገልፀዋል።

አቶ እስክንድር ከማንም ሰው ጋር እንዳይገናኙ መከልከላቸውን የሚገልጹት አቶ ሔኖክ፤ ጠበቃ በመሆናቸው ዝርዝር ለመጠየቅ ቢሞክሩም ሳይሳካላቸው መቅረቱን ተናግረዋል።

በሌላ ዜና ከኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራሮች አንዱ የሆኑት አቶ አዲሱ ቡላላ ምግብና ልብስ ለማድረስ ወደ እስር ቤት የሄደችውን የጃዋር እህትን በመጥቀስ እንደገለጹት "ምግብ አልቀበልም የረሃብ አድማ ላይ ነኝ" ሲሉ ልብስ ብቻ መቀበላቸውን ገልጸው አቶ በቀለም የረሃብ አድማውን መቀላቀላቸውን እንደሚያውቁ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የሁለቱ ፖለቲከኞች ፓርቲ የሆነው ኦፌኮ ጠበቆችን አነጋግሮ ታሳሪዎቹን እንዲያነጋግሩና አሁን ያሉበትን ሁኔታ እንዲያውቁ ተልከው ነበር የሚሉት አቶ አዲሱ፤ "አርብ ስለሆነ ዛሬ ማግኘት አትችሉም፤ ማክሰኞ ተመልሳችሁ ኑ" መባላቸውን ተናግረዋል።

አቶ አዲሱ የግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር መዋል አግባብነት የሌለውና በሕግ ቁጥጥር ስር ከዋሉ ጊዜ ጀምሮም ከቤተቦቻቸው፣ ከጠበቆቻቸውና ከሐኪሞቻቸው ጋር የመገናኘት ሕጋዊ መብት ቢኖራቸውም ይህ እየተጠበቀላቸው አይደለም ሲሉ ከስሰዋል።

የአቶ እስክንድር ነጋ ጠበቃ አቶ ሔኖክ አክለውም ዛሬ ጠዋት ወደ የባልደራስ ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሲያመሩ፤ ትናንት ምሽት ተዘግተው የነበሩት የቢሮው በሮች ተከፍተው ንብረቶች በየቦታው ወድቀው ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

ባደረጉት ማጣራትም ማንም ታዛቢ ባልተገኘበት ፖሊስ ወደ ፓርቲው ጽህፈት ቤት መጥቶ እንደነበርና ቢሮው ውስጥ ፍተሻ እንደተደረገበት እዚያ አካባቢ ከነበሩ የዓይን እማኞች ማረጋገጣቸውን ገልፀዋል።

ከአቶ እስክንድር ጋር አቶ ስንታየሁ ቸኮል ታስረው እንደሚገኙ የገለጹት ጠበቃው ሁለቱ የፓርቲው አመራሮች በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ወይም በተለምዶ ሦስተኛ በሚባለው ጣቢያ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በፖሊስ ቁጥጥር ስር ስለሚገኙበት ሁኔታ በተመለከተ ማብራሪያ ለማግኘት የፌደራል ፖሊስ ቃል አቀባይ የሆኑትን አቶ ጄይላን አብዲን አናግረን ስለተባሉት ጉዳዮች የደረሳቸው መረጃ እንደሌለ ተናግረዋል።

ከዚህ ባሻገርም ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪዎቻችን ምላሽ ባለማግኘታቸው ሊሳካ አልቻለም። ፖሊስ የሚሰጠው ምላሽ ካለ ለማስተናገድ ሙከራችንን እንቀጥላለን።

አቶ እስክንድር ነጋ፣ አቶ በቀለ ገርባና አቶ ጃዋር መሐመድ ለእስር የተዳረጉት ባለፈው ሰኞ ምሽት አዲስ አበባ ውስጥ ባልታወቁ ሰዎች የተገደለውን ታዋቂ ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ሞት ተከትሎ ከተከሰተው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ ነው።

የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ እስክንድር ነጋ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሁከት ለመቀስቀስ በመሞከር ተጠርጥረው እንደታሰሩ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ መግለጹ ይታወሳል።

አቶ ጃዋር መሐመድን ጨምሮ 35 ሰዎች ለእስር የተዳረጉት ደግሞ ከድምጻዊው አስክሬን ሽኝት ጋር በተያያዘ በተፈጠረ ግርግርና ባጋጠመ ሞት ምክንያት እንደሆነ የፌደራል ፖሊስና የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሸኖች በጋራ በሰጡት መግለጫ ማስታወቃቸው ይታወሳል።