የትግራይ ምርጫ ለፌዴራሊዝሙ ጥንካሬ እንጂ ስጋት አይሆንም፡ ጌታቸው ረዳ

ጌታቸው ረዳ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በትግራይ የሚካሄደው ምርጫ ለአገሪቱ ፌዴራሊዝም ጥንካሬ እንጂ ስጋት እንደማይሆን የህወሓት ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ጌታቸው ለቢቢሲው ኒውስዴይ ተናገሩ።

አቶ ጌታቸው እንዳሉት ክልሎች ምርጫ ማድረግ ያለባቸው "መብታችን ስለሆነ ነው። እኛ በዚህ ላይ አንደራደርም። ዋጋ ከፍለንበታል። ምርጫ እናድርግ ስንል አይቻልም የሚባል ምላሽን ከአራት ኪሎ አንቀበልም" ብለዋል።

እንደ እሳቸው አባባል ምርጫን የማራዘሙ ነገር በሁሉም ክልሎች ታምኖበት በቂ ምክንያት ኖሮ ቢሆን ኖሮ ነገሩን ለማጤን ድርጅታቸው እንደሚገደድ ተናግረው "ነገር ግን ይህ ውሳኔ በማዕከላዊ መንግሥት የተወሰደ የተናጥል እርምጃ ነው። ፍላጎቱን በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ ለመጫን የተደረገ ነው" በማለት እንደተቃወሙት አመልክተዋል።

ኒውስዴይ በትግራይ ፌዴራል መንግሥትን ውሳኔ ቸል ተብሎ የሚካሄደው ምርጫ ምን ፋይዳ እንደሚኖረው አቶ ጌታቸውን ጠይቆ በሰጡት ምላሽ "በጤናማ ሁኔታዎች ውስጥ ብንሆን መጠየቅ የነበረበት ጥያቄ ለምን ምርጫ አታካሄዱም ነበር። ነጻ ገለልተኛና ተዓማኒ ምርጫዎች የትም መሆን ያለባቸው ነገሮች ናቸው" በማለት ማዕከላዊው መንግሥት የሥልጣን ዘመኑን በግድ እያራዘመ መሆኑን ተናግረዋል።

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሰበብ በሌሎቹ የአገሪቱ ክፍሎች ምርጫው እንደማይካሄድ የታወቀ ሲሆን ትግራይ ለምን ተለይታ ከማዕከላዊ መንግሥቱ ጋር ቅራኔ ውስጥ እንደገቡ የተጠየቁት አቶ ጌታቸው "እኛ ብቸኞቹ ከሆንን መብታችንን ስለተነጠቅን ነው እምቢ ያልነው። ውድ ዋጋ የከፈልንበት መብት ነው። ሌሎች ክልሎች ውድ ዋጋ አልከፈሉም ማለቴ ግን አይደለም" ብለዋል።

ጨምረውም ሌሎች ክልሎች ምርጫው የመራዘሙን ነገር ሙሉ በሙሉ ተቀብለውታል ማለት እንዳልሆነ ጠቅሰው "ኦሮሚያ በአፈና ውስጥ ነው ያለው። ሰዎች እዚህና እዚያ እየተገደሉ ነው። በኦሮሚያም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ማለቴ ነው። መንግሥት ሕዝቡን መስማት አይፈልግም" ብለዋል።

ኒውስዴይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት ምሽት ለብሔራዊ ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለ ምልልስ ክልሉን ለማስተዳደር ሙሉ መብት እንዳላቸው መግለጻቸው ውጥረቱን ያረግበው እንደሆነ አቶ ጌታቸውን ጠይቆ "ችግሩ ዐብይ የሚናገውን የሚያደርግ ሰው አለመሆኑ ነው። ከመጣ ጀምሮ ሲያደርጋቸው የነበሩ አብዛኛዎቹ ነገሮች በሙሉ ችግር ፈጣሪ ነበሩ" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ ማክሰኞ ምሽት ከብሔራዊው ቴሌቪዥን ጋር ባካሄዱት ቃለ ምልልስ ላይ ምርጫው ሕጋዊ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።

"ሕጋዊ አይደለም፤ ምክንያቱም በኢትዮጵያ ምርጫ ማከናወን የሚችለው የምርጫ ቦርድ ብቻ ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ "አሁን በዚህ ሰዓት የሚደረጉ የእቁብ ስብስቦች ወይም ጉባኤዎች የእኛ ትልቅ እራስ ምታት መሆን የለባቸውም" በማለት ምርጫው መንግሥታቸውን እንደማያሳስብ ተናግረዋል።

ጨምረውም በዚህ ሳቢያ መንግሥታቸው ግጭት እንደማይገባ አረጋግጠዋል "በእኔ በኩል ለኢትዮጵያ ውጊያ ያስፈልጋል ብዬ አላምንም። እኔ በፍጹም ውጊያ ከሚደግፉ ሰዎች ጎን መመደብ አልፈልግም። እኔ የምፈልገው ለትግራይ አንድ ጥይት መላክ ሳይሆን፣ ለኮሮና መከላከሉ አንድ የአፍ መሸፈኛ ነው መላክ የምፈልገው" ሲሉ ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንት አስቸኳይ ስብሰባ ያደረገው የፌዴሬሽን ምክር ቤት በትግራይ ክልል የሚካሄደው ምርጫ ከአገሪቱ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን በመሆኑ "እንዳልተደረገ የሚቆጠር፣ የማይጸናና ተፈጻሚነት የሌለው ነው" ሲል በሙሉ ድምጽ መወሰኑ ይታወሳል።