በፊንላንድ አውሮፕላን ማረፊያ ውሾች በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎችን በሽታ መለየት ጀመሩ

ኮቪድ-19 የሚያነፈንፉ ውሾች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በመላው ዓለም በሚገኙ አውሮፕላን ማረፊያዎች ውስጥ አነፍናፊ ውሾችን መመልከት የተለመደ ነገር ነው።

እነዚህ ውሾች ሕገ-ወጥ ቁሶችን እና ኮንትሮባንድ አነፍንፈው ይጠቁማሉ።

በፊንላንዱ ሄልሲንኪ-ቫንታ አውሮፕላን ማረፊያ ግን ለአነፍናፊ ውሾች የተሰጣቸው ኃላፊነት ለየት ይላል።

አነፍናፊ ውሾች በኮሮናቫይረስ የተያዘን ሰው አሽትተው እንዲለዩ ለሙከራ ሥራ ተሰማርተዋል።

10 አሰልጣኞች 15 ውሾችን በአውሮፕላን ማረፊያው የሙከራ ሥራ አስጀምረዋል።

የዚህ ግብረ ኃይል መሪ የሆኑት አና ሄለም-በጆርክማን፤ ውሾቹ ሰዎች በኮሮናቫይረስ ተይዘው ምልክት ከማሳየታቸው ከአምስት ቀናት በፊት በበሽታው መያዛቸውን ይለያሉ ብለዋል።

“በበሽታ የተያዙ ሰዎችን በመለየት ረገድ አስደናቂ ውጤት አስመዝገበዋል። ወደ 100 ፐርሰንት ተጠግተናል” ብለዋል።

ኮቪድ-19 የሚያነፈንፉ ውሾች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ውሾቹ መንገደኞችን የሚመረምሩት እንዲህ ነው። መንገደኞች በአውሮፕላን ማረፊያው እንደደረሱ አንገታቸውን በጨርቅ ይጠርጋሉ። ከዚያም ያ ጨርቅ በኒኬል ኩባያ ውስጥ ተደርጎ ውሾቹ እንዲያሸቱት ይደረጋል።

በዚህም ውሾቹ ጨርቁን በማሽተት አንድ መንገደኛ በሽታው ይኑርበት፤ አይኑርበት በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ መለየት ይችላሉ።

በአየር መንገዱ እስካሁን ሲተገበር የቆየው ይህ ሙከራ አመርቂ ውጤት ቢያሳይም በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎችን ለመለየት አነፍናፊ ውሾችን የመጠቀሙ ጉዳይ ተጨማሪ ምርመራ ያስፈልገዋል ተብሏል።

በአሁኑ ወቅትም መንገደኞች አነፍናፊ ውሾቹ ቫይረሱ እንዳለባቸው ወይም እንደሌለባቸው ቢጠቁሙም ለተጓዦች የኮሮናቫይረስ ምርመራ እየተደረገላቸው ይገኛል።

የአገሪቱ ባለስልጣናት ግን ውሾቹ በቅርቡ ልክ ሕገ-ወጥ ቁሶችን አነፍንፈው እንደሚለዩት ሁሉ፤ በኮቪድ-19 የተያዘን ሰው ለመለየት እንደሚሰማሩ ተስፋ አላቸው።