ኮሮናቫይረስ፡ በአሜሪካ በአንድ ቀን ብቻ 94 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ ተያዙ

በማሳቹስተስ እየተመረመረ ያለ ልጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአሜሪካ ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ 94 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለማካሄድ ቀናት በቀሯት አሜሪካ በተለያዩ ግዛቶችም በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር አሻቅቧል ተብሏል።

በዚህ ሳምንት ሃሙስ 91 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ከፍተኛ ቁጥር ነው በማለት ሪፖርት አድርጋ የነበረቸው አሜሪካ በተከታታይ ባሉት ቀናትም እንዲሁ ከዚህ በላይ ያለው ቁጥር በየቀኑ ተመዝግቧል።

ወረርሽኙ ከተከሰተ ጀምሮም እስካሁን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 9 ሚሊዮን መድረሱን ከጆንስ ሆፕኪንስ የተገኘው መረጃ ጠቁሟል።

ፕሬዚዳንታዊ ስልጣኑን ለመጨበጥ ዶናልድ ትራምፕና ጆ ባይደን እየተፋለሙ ባሉባት አሜሪካ ጥቅምት 24፣ 2013 ዓ.ም አሸናፊው የሚታወቅ ይሆናል።

አሁን ባለውም ሁኔታ 21 የአሜሪካ ግዛቶች በወረርሽኙ ክፉኛ የተመቱ ሲሆን አንዳንድ ግዛቶችም በዚህ ምርጫ ላይ ቁልፍ ሚና የሚጫወቱ ናቸው ተብሏል።

በምርጫው ወሳኝ ከሆነችው ግዛት አንዷ ዊስኮንሰን የሚገኙ ሆስፒታሎች አርብ እለት የነበረውን የዶናልድ ትራምፕ የምረጡኝ ቅስቀሳ ወረርሸኙን ያባብሰዋል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

"በአሁኑ ወቅት በተቻለ መጠን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ባይሰበሰቡ ይመረጣል። በተለይም በዊስኮንሰን ግዛት ግሪን ቤይ አካባቢ በአገሪቱ ካሉ ቦታዎች በከፍተኛ ፍጥነት ወረርሽኙ እየተዛመተ መሆኑን እያየን ነው" በማለት የግዛቲቱ ሆስፒታሎች በጥምረት መግለጫ አውጥተዋል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ አርብ ከነበረው የምርጫ ቅስቀሳቸው በፊትም "ከፍኛ ምርመራ ከፍተኛ ቁጥርን እያስመዘገበ ነው። ምርጥ የሆነ ምርመራ አለን። ሞት እየቀነሰ ነው" በማለት በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።

በቅርቡ የነበረው የትራምፕ የምረጡኝ ቅስቀሳ ዘመቻ ላይ ተሳታፊው ሙቀት ሲለካ ነበር እንዲሁም ጭምብልም እየታደለ ነበር።

በወረርሽኙ ምክንያት ትልልቅ ዝግጅቶችም ከአዳራሽ ውጭ እየተደረጉ ነው።

ሆኖም በነዚህ ስፍራዎች አካላዊ ርቀት ሲጠበቅ አይታይም እንዲሁም አንዳንድ ደጋፊዎች ጭምብል አናጠልቅም የሚል እምቢተኝነት አሳይተዋል።

ጆ ባይደንም የምረጡኝ ቅስቀሳ ዘመቻቸውን እያካሄዱ ሲሆን ዲሞክራቶቹ አካላዊ ርቀትን እያስጠበቁ ነው ተብሏል። ለምሳሌም ያህል ደጋፊዎች በየመኪኖቻቸው ሆነው እንዲከታተሉ አድርገዋል።