ትግራይ ፡ ደብረጽዮን (ዶ/ር) ለተፈጠረው ቀውስ ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲፈለግ ድጋሚ ጥሪ አቀረቡ

ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶክተር)

የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ለተፈጠረው ቀውስ ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲፈለግ ጥሪ አቀረቡ።

ርዕሰ መስተዳድር ትናንት ማታ በክልሉ ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው መግለጫ በሰጡበት ወቅት እንዳመለከቱት ጦርነቱ መቀጠሉን ጠቅሰው ለችግሩ ፖለቲካዊ መፍትሔ ሊገኝለት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ደብረጽዮን (ዶ/ር) አክለውም እየተካሄደ ባለው ወታደራዊ ዘመቻ በተደጋጋሚ በመቀለ፣ በአዲግራትና በአላማጣ የአየር ድብደባ እንደተፈፀመባቸው ገልፀው "የተከዜ ሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ረቡዕ ዕለት የአየር ድብደባ ተፈፅሞበታል፤ የትግራይ ከተሞችም ጨለማ ውስጥ እንዲቆዩ ተደርገዋል" ሲሉ ከስሰዋል።

ነገር ግን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ስር ሆኖ በትግራይ ላይ የተደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በተመለከተ መረጃዎችን የሚሰጠው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ የተከዜ ግድብ በቦንብ ተመታ መባሉ የሐሰት መረጃን ነው ብሏል።

ጨምሮም "በውሃ የተሞላ ግድብ በቦንብ ቢመታ ሊያስከትል የሚችለው መጥለቅለቅና ጥፋት ማንም ሊገምተው የሚችለው መሆኑ የመረጃውን ሐሰተኛነት በቀላሉ ለማረጋገጥ ያስችላል" ብሏል።

በአየር ድብደባው በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት ማድረሱን አክለው የገልጹ ሲሆን ስለደረሰው ጉዳት ዝርዝር ማብራሪያ አልሰጡም። ጨምረውም በተለያዩ የጦርነት ቀጠናዎች በከባድ መሳሪያዎች ጭምር ድብደባ እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል።

"በተጨማሪም አሁንም በተለያዩ አቅጣጫዎች የጦርነት ዝግጅቶች አሉ። ውጊያው ገና ነው፤ ገና ጅምር ነው " ሲሉ ተደምጠዋል።

በክልሉ የፀጥታ ኃይሎች የተማረኩ የኤርትራ ወታደሮች መኖራቸውን ገልፀዋል። የኤርትራ ወታደሮች ከፌዴራል የፀጥታ ኃይል ጋር ግንባር ፈጥረው እየወጉን ነው ሲሉ ነው የገለጹት ገለፁ።

ከዚህ በፊትም ክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተመሳሳይ ክስ አቅርበው የኤርትራ መንግሥት ተሳትፎ እንደሌለው ማስታወቁ ይታወሳል።

ደብረጽዮን (ዶ/ር) በክልሉ ውስጥ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ድል እያገኙ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህም "እስካሁን ከ10 ሺ በላይ ወታደሮች ማርከናል" ያሉት ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ የኤርትራ ወታደሮች እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

ነገር ግን ርዕሰ መስተዳደሩ ተማረኩ ያሏቸውን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ወታራደሮች በተመለከተ ያቀረቡት ማስረጃ የሌለ ሲሆን ከገለልተኛ ወገንም ለማረጋገጥ አልተቻለም።

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሻከረ የመጣው የፌደራልና የትግራይ ክልል መንግሥት ግንኙነት የማይታረቅ ደረጃ ደርሶ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ምሽት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ህወሓት በትግራይ በሚገኘው የመከላካያ ካምፕ ላይ ጥቃት ማድረሱን ገልፀው ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ማዘዛቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው የመከላከያ ሠራዊት በኮማንድ ፖስት እየተመራ "አገሩን የማዳን ተልዕኮውን እንዲወጣ ትእዛዝ ተሰጥቶታል" ካሉ በኋላ በተለያዩ ግንባሮች ሕግ ማስከበር ያሉት ዘመቻ እየተካሄደ ይገኛል።