ኮሮናቫይረስ: እውን በጉጉት የተጠበቀው የኮሮናቫይረስ ክትባት ተገኘ?

ክትባት የያዘ ሰው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዓለም በጉጉት ሲጠብቅ የቆየው የኮሮናቫይረስ ክትባት ሙከራ አዎንታዊ ውቴት አስመዝግቦ "ወሳኝ ምዕራፍ" ላይ መድረሱ ተዘግቧል።

በፒፊዘር እና ባዮኤንቴክ የተሠራው ክትባት የመጀመሪያ ግኝቶች እንዳሳዩት ክትባቱ ከ90% በላይ የሚሆኑ ሰዎች በኮቪድ -19 እንዳይያዙ ሊያደርግ ይችላል።

በፒፊዘር እና ባዮኤንቴክ ምን አሳኩ?

ደረጃ 3 ሙከራ በመባል በሚታወቀው የክትባት የመጨረሻው ዙር ሙከራ መረጃን በማጋራት የመጀመሪያዎቹ ሆነዋል።

ይህ በክትባት ፍለጋ ውስጥ አንዳንድ የሙከራ ክትባቶች የማይሳኩበት ወሳኝ ደረጃ ላይ ነው፡፡

ክትባቱ ሙሉ በሙሉ የሙከራ አካሄድን ያልፋል። በዚህም የቫይረሱን የጄኔቲክ ኮድ በከፊል ለሰዎች በመስጠት ሰውነት ቫይረሱን የሚከላከልበትን ስርዓት እንዲፈጥር የሚያሰለጥን ዘዴ ነው።

ክትባቱ ወደ 43 ሺህ ለሚጠጉ ሰዎች የተሰጠ ሲሆን ምንም የደህንነት ስጋትም አልተነሳበትም፡፡

ክትባቱ ለገበያ የሚቀርበው መቼ ነው?

ፒፊዘር በፈረንጆቹ ዓመት መጨረሻ 50 ሚሊዮን ብልቃጦችን እንዲሁም በ2021 መጨረሻ 1.3 ቢሊዮን ያህል ለማቅረብ እችላለሁ ብሎ ያምናል።

እንግሊዝ ቀድም 30 ሚሊዮን ብልቃጦችን ያዘዘች ሲሆን እ.ኤ.አ. በ2020 መጨረሻ 10 ሚሊዮን ብልቃጦችን ታገኛለች ተብሎ ይጠበቃል።

መጀመሪያ 'ማን ይከተባል?' የሚለው የሚወሰነው ክትባቱ በሚቀርብበት ጊዜ ኮቪድ-19 ካለው የስርጭት ሁኔታ እና ክትባቱ ለነማን በጣም ውጤታማ ይሆናል በሚለው ይወሰናል፡፡

ለምሳሌ እንግሊዝ በጣም ተጋላጭ ከሆኑ የጤና ባለሙያዎች እና በሽታው የበልጥ ይጸናባቸዋል ከሚባሉት ለእነማን ቅድሚያ መስጠት እንዳለበት አልወሰነችም፡፡

ሰፋ ተደርጎ ከታየ ዕድሜያቸው ከ80ዎቹ በላይ የሆኑ፣ ቤት ውስጥ አንክብካቤ ለሚደረግላቸው እና ለጤና ሠራተኞች ቅድሚያ ይሰጣል የሚል ግምት አለ፡፡

ዕድሜ ለኮቪድ ትልቁ ተጋላጭነት እስካሁን ድረስ ነው ፣ ስለሆነም ዕድሜዎ እየጨመረ በሄደ መጠን በፍጥነት ክትባት ሊወስዱ ይችላሉ።

እንደ ባለሙያዎች ከሆነ ክትባቱ እስከ 2021 አጋማሽ ድረስ በስፋት ላይገኝ ይችላል፡፡

ሌሎች የሚዘጋጁ ክትባቶችስ አሉ?

በሌሎች ድርጅቶች የሚሠሩ እና በሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ክትባቶች ሙከራ ተጨማሪ ውጤቶች በሚቀጥሉት ሳምንታት እና ወራቶች ይወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በመጨረሻው የሙከራ ደረጃ ላይ የሚገኙ 10 ተጨማሪ ክትባቶች አሉ።

ቀዳሚዎቹ ተፎካካሪዎቹ የሚከተሉት ናቸው

* የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ እና አስትራዜኔካ ክትባት- እንግሊዝ

* ሞደርና- አሜሪካ

* ካንሳይኖ በቻይና ከሚገኘው የቤጂንግ የባዮቴክኖሎጂ ተቋም ጋር- ቻይና

* ጋማሊያ ምርምር ተቋም-ሩሲያ

* ጆንሰን

* ቤጂንግ የባዮሎጂካል ምርቶች ተቋም እና ሲኖፋርማ- ቻይና

* ሲኖቫክ እና ኢንስቲዩቶ ቡታንታን- ብራዚል

* የውሃን የባዮሎጂካል ምርቶች ተቋም እና ሲኖፋርማ- ቻይና

* ኖቫቫክስ- አሜሪካ

አራት ኮሮናቫይረስ ዓይነቶች በሰው ልጆች ውስጥ እንደተዘዋወሩ ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ሌሎቹ የተለመዱ የጉንፋን ምልክቶችን የሚያስከትሉ ሲሆን ለየተውኛውም ክትባት አልተገኝም፡፡

የተለያዩ የክትባት ዓይነቶች አሉ?

የክትባት ዋናው ዓላማ የቫይረስን የተወሰኑ ክፍሎች ለሰውነት በሽታን የመከላከል ስርዓት በማሳየት እንደ ወራሪ ቆጥሮ እንዴት መዋጋት እንደሚቻል ማስተማር ነው፡፡

ሆኖም ይህንን ለማድረግ የተለያዩ መንገዶች አሉ። ተመራማሪዎችም የተለያዩ አካሄዶችን እየተጠቀሙ ነው፡፡

የፕፊዘር እና የሞደርና ክትባቶች የኮሮናቫይረስ የጄኔቲክ ኮድ ቁርጥራጮችን ወደ ሰውነት በማስገባት የሚሠሩ ናቸው፡፡ አንዴ ወደ ሰውነት ከገባ በኋላ ሰውነትን በማሰልጠን የቫይራል ፕሮቲኖችን ማዘጋጀት ይጀምራል። ዘዴው ሙሉ በሙሉ አዲስ ነው።

የኦክስፎርድ እና የሩሲያው ክትባቶች ደግሞ ቺምፓንዚዎችን የሚይዝ እና ጉዳት የሌለው ቫይረስ በመውሰድ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በማመሳሰል ምላሽ ለማግኘት ተስፋ እያደረጉ ነው፡፡

ሁለቱ በቻይና የሚሞከሩት ታላላቅ ክትባቶች ዋናውን ቫይረስ ቢጠቀሙም ቫይረሱ በሽታ እንዳያስከተል በማድረግ ይጠቀሙበታል፡፡

የትኛው ዘዴ የተሻለ ውጤት እንደሚያስገኝ መረዳቱ ጠቃሚ ነው። ሰዎች ሆን ብለው በበሽታው የሚያስይዙ ሙከራዎች ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ሊሰጡ ይችላሉ፡፡

አሁንም ምን መደረግ አለበት?

* በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ክትባቶችን በከፍተኛ ደረጃ ለማምረት የሚያስችል መንገድ መዘጋጀት አለበት

* ተቆጣጣሪዎች ክትባቱን ከመሰጠቱ በፊት ይሁንታ መስጠት አለባቸው

* በመጨረሻም አብዛኛዉን የዓለም ህዝብ ክትባቱን መከተብ ትልቅ የሎጅስቲክ ፈተና ይሆናል

ምን ያህል ሰዎች መከተብ አለባቸው?

የክትባቱ ውጤታማነት ሳይታውቅ ምን ያህል ሰዎች መከተብ እንዳለባቸው ማወቅ ከባድ ነው።

ቫይረሱ በቀላሉ እንዳይሰራጭ ለማቆም ከ60-70% የሚሆነው የዓለም ህዝብ ቫይረሱን የመከላከል አቅም ሊኖረው ይገባል ተብሎ ይታሰባል (ኸርድ ኢሙኒቲ በመባል ይታወቃል)፡፡

በሌላ አባባል ክትባቱ ከሠራ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መከተብ አለባቸው።

ክትባት ለምን ያስፈልገናል?

ሕይወትዎ ወደ መደበኛ ሁኔታ እንዲመለስ ከፈለጉ ክትባት ያስፈልገናል፡፡

አሁንም ድረስ እጅግ በጣም ብዙ ሰዎች ለኮሮቫይረስ ተጋላጭ ናቸው፡፡ እየተጣሉ ያሉ ገደቦች ናቸው ብዙዎች እንዳይሞቱ እያገዘ የሚገኘው፡፡

ክትባቶች ሰውነታችን በሽታውን እንዲቋቋም ያስተምሩታል፡፡ በመጀመሪያ በኮሮናቫይረስ መያዝን ሊያስቆም ወይም ኮቪድ-19ን ገዳይነት ዝቅ ሊያደርገው ይችላል፡፡

ክትባቱ ከተሻሻሉ ህክምናዎች ጋር ጎን ለጎን ሲሰጥ ከችግሩ ‹የመውጫ› ጥሩ ስትራቴጂ ይሆናል፡፡